ለኅብረተሰቡ ፈተና የሆነው የአዋሽ – ሚሌ የፀጥታ ስጋት

በተደጋጋሚ ጸጥታ ስጋት የሚስተዋልበት ከአዋሽ ወደ ሚሌ በሚወስደው መንገድ ላይ የታጠቁ አካላት ለመንገደኞች ብሎም ለነዋሪዎች ስጋት መሆናቸውን የአይን እማኞች ለፍትህ መጽሔት ገለጹ። ረቡዕ የካቲት 25 2012 ዓ.ም የጀመረው ግድያ ፣ እና ዝርፊያ ሀሙስ እለትም እንደቀጠለ የአይን እማኞች ተናግረዋል።

ከሚሌ እስከ አዋሽ በሚወስደው መንገድ ላይ አሁንም በታጠቁ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መዋሉን ከአካባቢው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። የጦር መሳሪያ የታጠቁ ናቸው የተባሉት የሶማሌ ኢሳ አባላት ሲሆኑ መንገደኞችን በማውረድ የግድያ እና የዝርፊያ ወንጀሎችን እየፈጸሙ እንደሆነ  ነዋሪዎች ገልጸዋል። በዚህም የህብረተሰቡን ደህንነት አደጋ ላይ መውደቁን አስታውቀዋል።

በአካባቢው የመከላከያ ሰራዊት ቢኖርም ህብረተሰቡን ከጥቃት ማዳን እንዳልቻለ የሚገልጹት የአይን እማኞች በተለይ ረቡዕ የካቲት 25 2012 ዓ.ም በገዋኔ ከኡንደፋዖ ቀበሌ አከባቢ ጥቃት አድራሾቹ በተሳፋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ በርካታ ተሰፋሪዎች ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል። ከእዚህ ቀደም በጉዳዩ በተደረገ ውይይት የችግሩን አደገኝነት በመረዳት በስፍራው የመከላከያ ሰራዊት እንዲገባ በማድረግ የአካባቢው ጸጥታ መቆጣጠር እንዲችል ሃፊነት ተሰጥቶት ነበር። ነገር ግን ሰራዊቱ በቂ የሆነ የህግ ማስከበር እየሰራ አይደለም በማለት እማኞች ይናገራሉ።

በአካባቢው የሚታየው ስርዓተ አልበኝነት ህብረተሰቡ ሰላሙን እያጣ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪዎች የክልሉ ልዩ ሃይል ወደ ስፍራው በመላክ ህግ የማስከበር ስራ እንዲሰራም ጥያቄያቸውን አቅርበዋል። የመከለከያ ሠራዊት የኢትዮ-ጅቡቲን መስመር ከእነዚህ ሀይሎች መታደግ አለመቻሉንም በማንሳት ወቀሳቸውን አቅርበዋል።

የሰላም ሚንስቴር በክልሎች የሚፈጠሩትን ግችቶች ለመፍታት ከሃይማኖት አባቶች እና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር የተለያዩ ውይይቶችን በማድረግ ጥረት እያደረገ ቢገኝም እስካሁን ውጤት አለማምጣቱን የአፋር ክልል ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል።

የ1.5 ሚሊዮን የእድሜ ባለጸጋ ቅሪት ተገኘ

በአፋር ክልል ጎና ፕሮጀክት 1.5 ሚሊየን ዓመት ያስቆጠረ ቅሪተ አካል ተገኘቷል። እድሜ ጠገቡ የራስ ቅል ቅሪተ አካል፣ መጠኑ በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ከሚገኙትና ሆሞ ኢሬክተስ በመባል ከሚታወቁት የቅድመ ሰው ዝርያ አካላት አነስተኛ የሆነ የራስ ቅል ነው ተብሏል። ከራስ ቅሉ በተጨማሪም የተለያዩ የድንጋይ መሳሪያዎችም መገኘታቸው ተገልጿል።

ግኝቱን ይፋ ያደረጉት ስፔን በሚገኘው የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናት ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዶክተር ስለሺ ሰማው እና በአሜሪካ በሳውዘርን ኮኔክቲከት ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ማይክል ሮጀርስ (ዶክተር) በሚመራው የጎና መካነ ጥናት ፕሮጀክት ነው።

የተገኙት የራስ ቅል ቅሪተ አካላት ኦልዶዋን እና አሹሊያን ተብለው ከሚጠሩት የድንጋይ ዘመን መሳሪያዎች የሚካተቱ መሆናቸው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ በመረጃው ጠቅሷል። የራስ ቅሉ የአንጎል መጠን (590 ሲሲ) ሲሆን፣ ይህ ግኝት ከአሁን ቀደም በሆሞ ኢሬክተስ የድንጋይ መሳሪያ አጠቃቀም የነበረውን የእውቀት አድማስ በማስፋት ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋልም ተብሏል።

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን እንዳስታወቀው በጎና ፕሮጀክት የተገኙት የራስ ቅሎች ሁለት ሲሆኑ ሆሞ ኢሬክተስ በመባል በሚታወቀው የቅድመ ሰው ዝርያ የሚካተቱ መሆናቸውንም አስታውቋል። የመጀመሪያው በአቶ ኢብራሂም ሀቢብ የተገኘው ሙሉ የራስ ቅል 1 ነጥብ 5 ሚሊየን አመታት ዕድሜ ያለው ነው። በሁለተኛው ግኝት በፕሮፌሰር ኒኮላስ ቶዝ በከፊል የራስ ቅል የተገኘ ሲሆን፥ እድሜው 1 ነጥብ 2 ሚሊየን ዓመት ነው ተብሏል።

ይህ ግኝት ሆሞ ኢሬክተስ ሁለቱንም የድንጋይ መሳሪያ አይነቶች በአንድ ተመሳሳይ ጊዜ ሰርቶ ይጠቀም እንደነበር አመላካች መሆኑን እንደሚያሳይ ተገልጿል። ከአሁን ቀደም በሀገራችን የተገኙት የሆሞ ኢሬክተስ ቅሪተ አካላት የሚታወቁት ከመካከለኛው አዋሽ (ዲካ)፣ መልካ ቁንጡሬና ከኮንሶ ብቻ ሲሆን፥ በጎናው ፕሮጀክት የተገኘው ሆሞ ኢሬክተስ ግኝት አዲስ እና ተጨማሪ አስፈላጊ መረጃን አበርክቷል መባሉንም ሰምተናል።

የጎና የፓሌዎ አንትሮሎጂ ጥናት ፕሮጀክት ባለፉት 30 ዓመታት የምርምር ስራው በዓለም እጅግ ጥንታዊና 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠሩ የድንጋይ መሳሪያዎችን እንዲሁም 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ዓመታት ያስቆጠረውን አርዲፒቲከስ ራሚደስ የተባለውን ጥንታዊ የሰው ቅሪተ አካል በማግኘት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ጆርናሎች ላይ ማሳተሙ ይታወቃል።

ምድረ ቀደምት በመባል ስሟ የሚነሳው ኢትዮጵያ ስያሜውን ያገኘችው አፋር ክልል ውስጥ ሉሲ እና ሰላም የተባሉ እድሜ ጠገብ የሰው ልጅ ቅሪቶች የተገኙበት ስፍራ መሆኑ ነው። ክልሉ ከዚህ ባሻገር በርካታ የቱሪሰት መስህብ ስፍራዎች የሚገኙበት ጭምር ነው።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*