
ከተሸከርካሪዎች ስርቆት ጋር በተያያዘ ባደረገው የአንድ ወር ክትትል 27 ተጠርጣሪዎችን መያዙን የሐዋሳ ከተማ ፖሊስ ለፍትህ መሔሄት ገልጽዋል። የከተማዋ ፖሊስ መምሪያ ሀላፊ ምክትል ኮማንደር ኢዮብ አቤቶ ለፍትህ እንደገለጹት፣ ስምንት ሰዎች ከተሸከርካሪ ስርቆት ጋር በተያያዘ እንዲሁም 19 ሰዎች ደግሞ በሞተር ስርቆት ተጠርጥረው መያዛቸውን ነግረውናል።
ውጪ ከተከናወነ በኋላ ወደ ከተማዋ በማስገባት በሀሰተኛ ማስረጃ እንደሚሸጡ፣ እንዲሁም በከተማዋ የተሰረቁት ደግሞ ከሀዋሳ ከተማ ውጪ በመወሰድ በተመሳሳይ ለሽያጭ ማቅረብ የሚደረግ የወንጀል ስራ እንደሆነ በተደረገው ክትትል መታወቁን አስረድተዋል።
በተጨማሪም ‹‹ገንዘብ አታሚ ነኝ›› በማለት የተለያዩ መጠን ያላቸውን የብር ኖቶች ሲያትም የተገኘ የውጪ ሀገር ዜጋ ከነሙሉ ቁሳቁሱ በቁጥጥር ስር መዋሉም በመግለጫው ተጠቁሟል። ሐሰተኛ የብር ኖቶች ህትመት ሲያካሂድ የነበረው ግለሰብ የየት ሀገር ዜግነት እንዳለው ግን በመግለጫው አልተካተተም።
በምርመራው ወቅት የውጪ ሀገራት ገንዘቦችም የሚያትሙ እንዳሉ ግለስቡ መጠቆሙን ያስታወቁት ኮማንደር ኢዮብ፣ የተባለውን ድርጊት ለጊዜው በከተማ ውስጥ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል። ሆኖም ጠንካራ ክትትል እያደረጉ እንደሆነ እና ይሄን ጉዳይ የከተማው ህዝብ እንዲያውቀው እና ጥንቃቄ እንዲያደርግ ሀላፊው አሳስበዋል።
ሀላፊው ረቡዕ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም በሰጡት መግለጫ፣ የሀዋሳ ከተማ ህዝብን ሰላም ለማረጋገጥ ፖሊስ በወንጀለኞች ላይ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ህግ የማስከበር ስራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። ከተማዋን አስተማማኝ ለማድረግ የስምሪት ስርዓት በመቀየር እና የወንጀል ክትትል በማድረግ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሆነ ኮማንደር እዮብ ገልጸዋል።
‹‹በከተማችን ውስጥ በርካታ የስርቆት ወንጀሎች በባጃጅ፣ በሞተር ሳይክል እና አልፎ አልፎ በተሸከርካሪ ይፈፀማሉ። እነዚህን ለማስቀረት እንደጸጥታ ሃይል በራሳችን አቅደን ከባለድርሻ አካላት ጋርም በመቀናጀት እና ከህዝቡ ጋር በመምከር የስምሪት ስርዓት ቀይረን እየሰራን ነው። ፖሊሱ ከዚህ በፊት ሲሰማራ በነበረው ልክ ሳይሆን አሁን ለመቆጣጠር በሚያስችለን አኳኋን ይሻላል ያልነውን ዘዴ መርጠን እና አቅደን ነው ወደ ስራ የገባነው። በዚህ መነሻ በርካታ ሞተር ሳይክሎችን መቆጣጠር ችለናል። በተጨማሪም፣ በሞተር ታግዘው ወንጀል ሲፈጽሙ የነበሩ ግለሰቦችን መቆጣጠር ተችሏል።›› ብለዋል።
በቁጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በምርመራው ጊዜ በሰጡት ቃል ከመኪና ጀምሮ ባጃጅ እና ሞተሮችን ከቆሙበት በመውሰድ ለወንጀል አገልግሎት እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል። ለዚህም የሚረዳቸው በርካታ ቁልፎች እንዳሏቸውም ታውቋል ሲሉ ሃላፊው ጨምረው አስታውቀዋል።
በሃዋሳ ከተማ በተደጋጋሚ ከሚፈፀሙ የንጥቂያና ዝርፊያ ወንጀሎች በተጨማሪ የተሸከርካሪ ስርቆት፣ የህገ ወጥ ንግድ እና የማጭበርበር ወንጀሎች በስፋት እንደሚስተዋሉ ኮማንደር ኢዮብ ተናግረዋል።
ባለፈው ሳምንት ፖሊስ ባደረገው ክትትል በተለያዩ ወንጀሎች የተጠረጠሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ገልጸው፣ ፖሊስ ይሄን ውጤታማ ያደረገው በቅንጅት እና በተደራጀ መንገድ በመስራቱ እንደሆነም በመግለጫቸው ተገልጿል። አያይዘውም በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች በጥፋታቸው ልክ ይቀጣሉ ብለዋል።
በመግለጫው እንደተጠቀሰው ተሸከርካሪዎቹ ከተሰረቁ በኋላ ህጋዊ ለማስመሰል ሰነድ ተዘጋጅቶላቸው ለአገልግሎት እንዲውሉ እንደሚደረግም ኮማንደር ኢዮብ አቤቶ ተናግረዋል።
ሰሞኑን በተካሄደው ክትትል በተደራጀ መንገድ የተሰረቁ ስምንት ባለሁለት እግር ብስክሌቶች እና አራት መኪኖች በቁጥጥር ስር በማዋል በ27 ተጠርጣሪዎች ላይ ምርመራ እያካሄደ እንደሚገኝ ሃላፊው አስታውቀዋል። አብዛኞቹ የስርቆት ወንጀሎች በረቀቀ መንገድ የተፈፀሙ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አንዳንድ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ለፍትህ መጽሔት በሰጡት አስተያየት በተለይ በከተማዋ 01 ቀበሌ የሚባለው ስፍራ ስርቆት እየተከናወነባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች ግንባር ቀደሙ እንደሆነ ያነሳሉ። በተጨማሪም ሪፈራል ሆስፒታል፣ ሐይቅ ዳር፣ አላሙራ እና ቀበሌ 05 ዋነኞቹ ቦታዎች እንደሆኑ ምንጮች ተናግረዋል። ጨምረውም በተለይ አልፓች፣ ዲስከቨሪ እና ኤል (L) የተሰኙ የሞተር ሞዴሎች ለስርቆት የተጋለጡ ናቸው ብለዋል።
በተለይ ኤል (L) የሚባለው ሞዴል አሽከርካሪው አቁሞ በሄደ በደቂቃዎች ውስጥ እንደሚወሰድ ነዋሪዎች አስታውቀዋል። እንደ ነዋሪዎቹ አገላለጽ እነዚህ ተሸከርካሪዎች ለአጠቃቀም ቀላል በመሆናቸው በተመሳሰይ ቁልፍ በማስነሳት እንደሚወሰዱ ተናግረዋል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ (በኮንትሮባንድ) ወደ ሀዋሳ የገቡ አልባሳት ፣ የምግብ ዘይት እና ስኳር መያዙን በመግለጫው ተብራርቷል። እንዲሁም፣ ህገ ወጥ የአደንዛዥ እጽ ዝውውር እና የሺሻ ማስጨሻ ቦታዎች መዘጋታቸውን ጨምረው ገልጸዋል።
እየተደረገ ባለው ክትትል የሀዋሳ ከተማ በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ ትገኛለች ያሉት ኮማንደር ኢዮብ፣ የተደረገውን እንቅስቃሴ በማስቀጠል ከተማዋን የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ በመስራት ላይ መሆኑን ነግረውናል። ህብረተሰቡም እያደረገ ያለውን ትብርር በማድነቅ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።
Be the first to comment