ታሕታይ ምስቅልና እና ፖለቲከኞች – መስፍን ማሬ

በሺዎች በሚቆጠሩ የኑባሬ ዓመታት ኢትዮጵያ አሁን እንደምንገኝበት ዘመን ፈተና ውስጥ ገብታ አታውቅም። ለበርካታ ጊዜያት በውጭ ወራሪዎች ጥቃት የፈፀሙባት ጠላቶቿ በዚህ ዘመን ጡቶቿን ጠብተው ለጉልምስናና ለአዛውንትነት ዕድሜ የበቁ ልጆቿ የጋረጡባትን ያህል ፈተና አላመጡባትም። የዚህ ዘመን ኢትዮጵያ ‹‹…ላም እሳት ወልዳ እንዳትልሰው እሳት ሆነባት፤ እንዳትተወው ልጅ ሆነባት›› ዓይነት ነገር ሆኖባታል። አንድነቷ ተናግቶና ጠፍቶ በነበረበት ዘመነ መሳፍንት እንኳ በሕዝቦቿ ላይ የአሁኑ ዓይነት የመከፋፈል ስጋት አልተደቀነም።

በዚያ ዘመን የነበሩ መሳፍንቶች ዋነኛ ዓላማ፣ ሥልጣን በኃይል ይዞ ሕዝቡን አስገብሮ የአንድ አካባቢ ገዥ ከመሆን በተለየ የሕዝብን ሠላም የማናጋት እኩይ ዓላማ ይዘው አልሰሩም። የነበረው ልዩነት ይበልጡኑ በጉልበተኞቹ መካከል ተወስኖ የሚቀር ስለነበረ፣ በዚህ ዘመን ክሱት እንደሆኑት ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች ሕዝቡን እርስ በእርስ የማጋጨት አባዜ የተጠናወታቸው አልነበሩም። ኢትዮጵያ እንደ አገር ፀንታ ለመቆየት ፈተና ሆነውባታል የሚባሉት የዚያን ዘመን መሳፍንት በሕዝቦቿ መካከል የጥላቻ ዘር አልዘሩም። በተደጋጋሚ የውጭ ወረራ በገጠማት ጊዜ እንኳ በዚህ ዘመን እንደምናየው የድንበሮቿንም ሆነ የህዝቦቿን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ እኩይ ሥራዎችን አልሰሩም። መሣፍንቶቹ፣ ከፍተኛ የሆነ የሥልጣን ጉጉት ይኑራቸው እንጂ እንደዚህ ዘመን መሪዎች፣ ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች አንዳቸውም ኢትዮጵያን አላሳነሱም። እንዲያውም በሁሉም አቅጣጫ ድንበሮቿ ይከበሩ ዘንድ አጥብቀው የሚፈልጉ እንደነበሩ ታሪካቸው አስረግጦ ይነግረናል። እነዚያ የኢትዮጵያን አንድነት ወደ ጎን ትተው ለሥልጣን ይሻኮቱ የነበሩ መሳፍንቶች በግዛቶቿ እስከመደራደር የሚያደርስ አሳፋሪ ስብዕና የነበራቸው ስለመሆናቸው የሚነገርባቸው አንዳች ነገር የለም። ሌላው ቀርቶ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸው ግራኝ አሕመድ እንኳ የሐይማኖት ማስፋፋትን ዋነኛ ግባቸው አድርገው እልቂትና ውድመት ይፈጽሙ እንጂ እንደ አገር ኢትዮጵያን ያሳነሱበት ጊዜ እንዳልነበር የታሪክ ድርሳናት ያሳያሉ።

ፅሁፉን የምታነቡ፣ እነዚህን መሳፍንቶች በአዕምሯችሁ ያዙና ስለእነዚህ የዘመናችን ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች ፍፁም ያልተገራውን የአጥፊነት ባሕርይ ለመመርመር ሞክሩ። ባሰብኩ ቁጥር መልስ የማላገኝላቸው በርካታ ጥያቄዎች አዕምሮዬን ሰንገው ይይዙታል። አንድ ሰው የቱንም ያህል በደል ደርሶብኛል ብሎ ቢያስብ እምብርቱ የተቀበረባትን አገር እንዴት መጥላት ይቻለዋል? የትኛውንም ያህል የድህነት ቀንበር ተጭኖት ቢያድግና ቢኖር የሚጠራባትን አገሩን እስከማፍረስ የሚደርስ የበቀል ፍላጎት እንዲኖረው የሚያደርገው ምክንያት ምን ሊሆን ይችላል? የጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ፋና ወጊ፣ ለተገፉ ሕዝቦች የብርሃን ተምሳሌት በመሆናቸው ዝናቸው ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ የናኘውን ብርቅዬ ንጉሰ ነገስት አፄ ምኒሊክን ከተራ ወንጀለኛነት በታች አውርዶ በየአደባባዩና ስማቸውን እስከማጥፋት የሚያደርሰው ልክፍት ካልሆነ በስተቀር ምን ሊባል ይችላል? የዓለም መንግስታትና የታሪክ ተመራማሪዎች በአመራር ጥበባቸውና በጀግንነታቸው አድናቆት የቸሯቸውን ነገስታቶቻችንን ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ወደኋላ ሄደው ጥላሸት እስከመቀባት የሚደርስ ጥላቻ በአዕምሯቸው ሊፈጠር የቻለበት ምክንያት ምን ይሆን? የተበደሉበት ሁኔታ አስከፊ ነበር ቢባል እንኳ፣ ደልቶት ወይም ተመችቶት የማያውቀው ምስኪን ወገናቸውን ከቀዬው እስከማፈናቀል የሚደርስ ጥላቻ ባለቤት መሆን ጤነኛነት ነው? የዘመናችን ፖለቲከኞችና አክቲቪስት ነን ባዮች ማንኛውም ዜጋ በእዕምሮው ሊያስብ ከሚችለው ጤናማ ሃሳብ የተለየ እንዲያስቡ ያደረጋቸው ምን ይሆን? ኢትዮጵያ ለበርካታ ዜጎቿ ማዳረስ ያልቻለችውን ዘመናዊ ትምህርት እንዲማሩና የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ያደረገቻቸው እነዚህ የእንጀራ ልጆቿ የድሆች ወገኖቻቸውን ሕይወት ለመለወጥ ሌት ተቀን ተግተው ከመሥራት ይልቅ ጡት ነካሽ የሆኑበት ምክንያት ለእኛ ለተቀረነው ያልታየን እነሱ የተለየ ተፈጥሮ ባለቤት ሆነው ይሆን?

እነዚህ ተምረናል፣ ታሪክ እናውቃለን፣ ተቆርቋሪ ነን፣ ወዘተ… የሚሉ(አንዳንዶቹ ከፍተኛው የአካዳሚክ ማዕረግ ተሸክመዋል) ስያሜዎችን ለራሳቸው ስለ ሰጡ ከመልካም ነገራቸው ይልቅ የአጥፊነት ስብዕናቸው ጎልቶ ስለወጣ ሰዎች ለበርካታ ጊዜያት ሳስብ ኖሬያለሁ፤ ቆይቻለሁ። እስካሁን ድረስ አጥጋቢ ምላሽ አላገኘሁም። ይህ ሁኔታ ግራ ሲጋባኝ ቆይቷል። አሁን በምንገኝበት ዘመን የሰዎቹ ኢትዮጵያን የመጠየፍ አባዜ ከየት የመጣ እንደሆነ ለመረዳት ማለቂያ በሌለው ሃሳብ ውስጥ ሆኜ ስማስን ይህን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ምክንያት የሆነኝን አንድ ሃሳብ አገኘሁ። የታዋቂው የሳይኮአናሊቲካል ንድፈ-ሃሳብ(psychoanalytical theory) አፍላቂ የነበረው ሲግመንድ ፍሮይድ ተከታይ የነበረው ፈረንሳዊው ሳይኮሎጂስት አልፍሬድ አድለር ግኝት የሆነው ስለ ታህታይ ምስቅልና(inferiority complex) የፃፈው መፅሐፍ ለፅሁፌ መንደርደሪያ የሚሆኑ ሃሳቦችን ይዟል። በዚህ ፅሁፍ ውስጥ “inferiority complex”ን የአማርኛ አቻው በሆነው ታዕታይ ምስቅልና በሚለው ሐረግ የምጠቀም ሲሆን፣ ይህን ሐረግ ያገኘሁት በ1977 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ የ1ኛ ዓመት ተማሪ በነበርኩ ጊዜ አንድ ክፍል ውስጥ አብሬው ስማር የነበረው ታዋቂው ፕሮፌሰር ምንዳርአለው ዘውዴ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ነው። ከዚህ የተሻለ መጠሪያ አለ ብዬ ስላላመንኩ ከእርሱ ተውሼ ሐረጉን መጠቀም መርጫለሁ።

ስለ ታህታይ ምስቅልና ለመጀመሪያ ጊዜ እንደፃፈ የሚነገርለት አልፍሬድ አድለር “Individual Psy­chology” የሚል ርዕስ በሰጠው መፅሐፉ ውስጥ ነው። አድለር በዚህ መጽሐፉ ውስጥ የሰዎችን የሥነ ልቦና አወቃቀር አመልክቷል። ሰዎች የዚህኛው ወይም የዚያኛው ወይም የመልካም ወይም የእኩይ ሃሳብና ድርጊት ባለቤት እንዲሆኑ ስለሚያደርጓቸው ገፊ ምክንያቶች በዝርዝር አስፍሯል። በዚህ ፅሁፍ ታህታይ ምስቅልናን በሚመለከት መፅሐፉ ያካተታቸው ቁም ነገሮች ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን እያመሱ ያሉት ፖለቲከኛና አክቲቪስት ነን ባዮች የሚታይባቸው ሥነ ልቦና ውቅር ጋር ተያያዥነት ያላቸው መሆኑን ለማሳየት እሞክራለሁ። የሰዎቹ የሥነ ልቦና ሁኔታ መፅሐፉ ከያዛቸው አንኳር ሃሳቦች ጋር የሚያያዝ ስለመሆኑ ዳሰሳ አደርጋለሁ። ታህታይ ምስቅልናን በሚመለከት መፅሐፉ ውስጥ የተካተቱ ሃሳቦች የፅሁፌ ትኩረት ከሆኑ ሰዎች የሥነ ልቦና ውቅር ጋር ያለውን ግንኙነት ለማሳየት እሞክራለሁ። መደምደሚያው የግሌ ሆኖ መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱ ሃሳቦች በእርግጥ የሰዎቹን ሥነ ልቦናና ባህርይ አመላካች ሊሆን ይችል አይችል እንደሆነ አንባቢዎች በየራሳችሁ መደምደሚያ ላይ መድረስ እንድምትችሉ እምነቴ መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ።

ታህታይ ምስቅልና ምንድን ነው?

በምድራችን የሚኖር ማንኛውም ሰው ምሉዕ ሆኖ አልተፈጠረም። ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች ሰዎች ጋር አነፃፅረው የመመልከት ባሕርይ ያላቸው ሲሆን፣ የሚበልጡት የሚያደርጉት ንፅፅር አንድ የሆነ ነገር እንደሚጎድላቸው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይኼ አዲስ አይደለም። የተለመደ ነው። በሌላ በኩል በአካዳሚክ እውቀቱ እጅግ የተዋጣለት ምሁር ወይም በሥራው የስኬት ማማ ላይ የደረሰ አንድ የምታውቁት ሰው ሊኖር ይችላል። ይሁንና ይህ ሰው ሰላም አልባ ሆኖ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሕይወቱን ሊመራ ይችላል። ላይ ላዩን በራሱ የሚተማመን የሚመስል ሰው ልታውቁ ትችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን በውስጡ ራሱን ዋጋ አልባ አድርጎ ሊቆጥር ይችላል። ከዚህ ቀደም አግኝቷቸው ከማያውቃቸው ሰዎች ጋር ሲገናኝ እሱን የሚጠሉት ወይም የማይወዱት ሊመስለው ይችላል። እንደዚህ ዓይነቶቹ በራሱ እንዳይተማመን የሚያደርጉ ነገሮች መላ ስሜቱን መቆጣጠር ሲጀምሩ ሰውየው የታህታይ ምስቅልና ተጠቂ ስለሚሆን መደበኛ ሕይወቱን በአግባቡ እንዳይመራ ሊያደርገው ይችላል።

ፓም ጆህንሰን የተባሉ ፀሐፊ እ.አ.አ. በ2015 “The Inferiority Complex” በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ ታህታይ ምስቅልና ማለት ራስን ዋጋ ቢስ አድርጎ መቁጠር እንደሆነ ገልጸዋል። በማያያዝም ታሕታይ ምስቅልና ማለት አንድ ሰው የሆነ ነገር መሥራት ስለመቻሉ እርግጠኛ መሆን ሲያቅተው ወይም የጥርጣሬ ስሜት ሲገባ ያለውን ሁኔታ የሚያሳይ ሐረግ እንደሆነ በመጽሐፉ ውስጥ አስፍረዋል። እንደ ፓም ጆህንሰን አገላለጽ አንድ ነገር ለመፈጸም የፈለገ ሰው የሚያድርበትን ስጋትን ተከትሎ አዕምሮው ትርምስምስ ያለ ነገር ውስጥ የሚገባበትን ሁኔታ የሚያሳይ ሊሆን እንደሚችል በመግለፅ ታህታይ ምስቅልና በተለያየ ሁኔታ ሊገለጽ የሚችል መሆኑን ገልጿል። አያይዘውም ታህታይ ምስቅልና አንድን ነገር ከማድረግ በመታቀብ ወይም ይፋዊ የሆነ የአመጸኝነት ባሕርይ በማሳየት ሊገለጽ እንደሚችል አስፍረዋል።

የጽንሰ ሃሳቡ ባለቤት የሆነው አልፍሬድ አድለር ታህታይ ምስቅልና ማለት አንድ ሰው በውስጡ የሚሰማው የማነስ ስሜት ከፍተኛ ሆኖ የዕለት ተዕለት ሕይወቱ ምሉዕ እንዳይሆን የሚያደርገው መታወክ ደረጃ የሚደርስበት ሥነ ልቦናዊ ሁኔታን የሚያመለክት ሐረግ እንደሆነ እ.አ.አ. በ1920 ዎቹ በጻፈው መፅሐፍ ውስጥ ጠቅሷል። እንደ አልፍሬድ አድለር እይታ ታህታይ ምስቅልና ማለት ለመጥፎ ወይም በጎ ላልሆነ ነገር እጅ መስጠት ወይም መሸነፍ መሆኑንና በዚህ የተነሳም በዚህ የበታችነት ስሜት ውስጥ የገባ ግለሰብ ችግሮችን ወይም መጥፎ ነገሮችን ተቋቁሞ ማለፍ ወደማይቻል ስሜት ያመራዋል በማለት ገልፆታል።

“World Encyclopedia” በበኩሉ ታህታይ ምስቅልና ማለት አንድ ሰው ከሌሎች ሰዎች በሁሉም አንሶ የሚገኝ ስለመሆኑ የሚሰማውን ጥልቅ ስሜት የሚያመለክት ሐረግ ነው በማለት ይገልፀዋል።

በደቀ መዝሙርነት ሲከተለው ከነበረው ታዋቂው የሳይኮአናሊቲካል ንድፈ ሃሳብ አራማጅ የነበረውና ታህታይ ምስቅልና የሰዎችን ባሕርይ የሚያነቃቃ ወይም የሚያበረታታ ንቁ ባልሆነው የአዕምሮ ክፍል(uncon­scious) የሚፈፀም ነው በማለት ሲግመንድ ፍሮይድ ሲያራምደው ከነበረው ሃሳብ በመለየት “ego psy­chology” የሚል ርዕስ የሰጠውን አዲስ ሃሳብ ለዓለም አስተዋውቋል። “ego psychology” የሚል ርዕስ በሰጠው ፅሁፍ ላይ እንዳሰፈረው የሚያበረታታው ፍላጎት ንቁ ባልሆነው የአዕምሮ ክፍል ብቻ ሳይሆን ንቁ(conscious) በሆነውም ሊፈፀም የሚችል መሆኑን ገልéEል። አድለር በዚህ ሥራው የሰው ልጅን ሰብዕና አቅጣጫ በማስያዝና ባሕርይን በመወሰን በኩል ንቁ የሆነው የአዕምሮ ክፍል(conscious factors) የማይናቅ ሚና እንዳለው አመላክቷል።

አድርለር አዎንታዊነትን ወይም ውጤታማነትን ከሚያበረታታው ከተለመደው የበታችነት ስሜት በተለየ ታህታይ ምስቅልና ሰዎች ችግሮችን ተጋፍጠው ከማለፍ ይልቅ ወደ ኋላ እንዲሉ የሚያደርግ በከፍተኛ ደረጃ አሉታዊ ስሜት የሚፈጥር እንደሆነ ሃሳቡን ገልéEል። በማያያዝም የዚህ ድብርት መሳይ የአዕምሮ ነርቭ በሽታ(neurosis) ሊከሰት የሚችለው ፍፁም ተግባራዊ ማድረግ የማይቻል ግለሰባዊ መልካም ስብዕና ለማግኘት ከሚደረግ ከንቱ ሙከራ ጋር የተያያዘ መሆኑን አስምሮበታል። ከዚሁ ጋር በማያያዝም አንድ ሰው በራሱ ላይ የሚኖረው እምነት ጥልቅ በሆነው የበታችነት ስሜት የተነሳ ዝቅተኛ ሊሆን አንደሚችል ይናገራል። በሌላ በኩል እንደ አድለር እምነት ታህታይ ምስቅልና ሁሌ አሉታዊ ውጤትን ብቻ የሚያመጣ ሳይሆን፣ አዕምሯቸው በከንቱ በሚፈጥረው ስሜት ማለትም ሌሎች እነሱን ደካማ እንደሆኑ አድርገው የሚያስቡ መሆኑን ከመገመት የተነሳ የችግሩ ሰለባ የሆኑ ሰዎች እንደ ግለሰብ የሚሰማቸውን የበታችነት ስሜት ለማካካስ ወደ አንድ ጫፍ ተገፍተው በመሄድ ራሳቸውን ከማሕበረሰቡ ማግለልን ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ስኬታማነትን ሊቀዳጁ እንደሚችሉ ይናገራል።

“Idividual Psychology” በተባለው መፅሐፉ አድለር ጤነኛ አዕምሮ ማለት አንድ ሰው ከሌሎች ጋር አለኝ ብሎ የሚያስበውን ሰዋዊ ትስስር ወይም ቅርበትና ለሌሎች እድገትና ብልፅግና ማሰብና መሥራት እንደሆነ ገልፆታል። ይህ መልካም የአዕምሮ ሁኔታ በአግባቡ ካልዳበረ ወይም ካልበለጸገ ግለሰቡ የታህታይ ምስቅልና በሽታ ተጠቂ ሊሆን ወይም የዚህ ተቃራኒ የሆነውን የላዕላይ ምስቅልና ችግር ሰለባ ሊሆንና ከሌሎች ጋር የተካረረ ቅራኔ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ገልጿል። አንድ ሰው የላዕላይ ምስቅልና ሕመም ተጠቂ ከሆነ ራሱን ብቻ ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ በማዳበር በውስጣዊ ስሜቱና አዕምሯዊ አስተሳሰቡ ሌሎች የሱ ጤናማ ያልሆነ አስተሳሰብ ተከታዮች ብሎም አምላኪዎች እንዲሆኑ የማድረግ ዝንባሌ እንደሚታይበት ይገልፃል። ልብ በሉ። ካለፉት ሦሥትና አራት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ የሆኑ ነገሮችን መለስ ብላችሁ በእዝነ ኅሊናችሁ ቃኙ። የታህታይ ወይም የላዕላይ ምስቅልና ሕመም ተጠቂ የሆኑ ፖቲከኞች እና አክቲቪስት ነን ባዮች ንቁ ያልሆነው የአዕምሯቸው ክፍል ለዓመታት ሲያጠነጥኑ የቆዩትን ሃሳብ አመች ጊዜ ያገኙ ሲመስላቸው በአስር ሺዎችና ከዚያ በላይ የሚቆጠሩ ወጣቶች ይኸው የምስቅልናው ውጤት የሆነውንትርክት በመንዛት በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ለጥፋት ተግባራቸውአሰማርተው በንፁኃን ወገኖቻችን ላይ ያደረሱትን መከራና ሰቆቃ ማስታወስ በቂ ነው። በአድለር የ“Idividual Psy­chology” ንድፈ ሃሳብ ውስጥ በፃፈው የሥነ ልቦናዊ ማካካሻ አስተሳሰብ መሠረት የምስቅልናው መጠን ጠንካራ በሆነ መጠን የግል ፍላጎቶቹን የማሟላት አቅሙ በዚያው መጠን ከፍተኛ እንደሚሆን ያብራራል። እነዚህ ከኢትዮጵያዊነት የወደቁ የታሕታይ ምስቅልና ሰለባዎች የሚሰማቸው የዝቅተኛነት ስሜት ጥልቅ በሆነ ቁጥር የጥፋት ተልዕኳቸው የዚያኑ ያህል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል አስምሮበታል። ሌሎች ወገኖቻቸው እነሱ ያገኙት የመማር ዕድልና የመሥራት አጋጣሚ ዋነኛ ምክንያት ጠንክሮ መሥራት መሆኑን ከመምከርና ከማስተማር ይልቅ ለመልካም ነገር ቦታ የሌለው አዕምሯቸው የጥፋት መርዝ መርጨት ሠርክ ሥራቸው አድርገው ተያይዘውታል። እየሆነ ያለውም ይኸው ነው። ይህ የታህታይ ምስቅልና ሕመም ሰለባ መሆን ያመጣው ነገር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

አድለር በዚህ “Idividual Psychology” የሚል ስያሜ በሰጠው መጽሐፉ የበታችነት ስሜትን ቀዳማይና(pri­mary) ተከታይ(secondary) በማለት ለሁለት የከፈለው ሲሆን፣ ቀዳማይ የበታችነት ስሜት ገና ከጨቅላ የሕፃንነት ዕድሜ የሚጀምር ሆኖ መነሻ የሚያደርገውም አቅመ ቢስ መሆንን፣ ደካማነትንና በአዋቂዎች ጥገኛ የመሆን ስሜት እንደሆነ ገልፆታል። ተከታይ የበታችነት ስሜት የሚመለከተው አዋቂዎችን ሆኖ መነሻ የሚያደርገው የመጨረሻ ግቦቹ የሆኑትን ግለሰባዊ ደህንነትና ስኬትን ለመቀዳጀት ያስችሉኛል ብሎ የሚያስባቸው በአጋጣሚ የሚሆኑ ነገሮችና ያን ሊያካክሱለት የሚችሉ ነገሮች በገሃዱ ዓለም አለመኖራቸው የሚፈጥርበት ስሜት እንደሆነ አስፍሯል። ዓላማውን ሊያሳኩ ይችላሉ የሚላቸው ነገሮች ተጨባጭ አለመሆናቸው ጉድለት ያለበት እንደሆነ እንዲሰማው በማድረግ እውተኛው የታህታይ ምስቅልና ስሜቱን በፍጥነት እንደሚቀሰቀስበት አስፍሯል። እነዚህ የበታችነት ስሜትን የሚያመጡ ነገሮች ሲደማመሩ የታህታይ ምስቅልና ስሜቱን ሁለንተናዊ እንደሚያደርጉት ይናገራል። የዚህ ዓይነቱ ሰው የበታችነት ስሜት እየተባባሰ የሚመጣው እውን ሊሆን የማይችል ከፍተኛ የማካካሻ ዓላማ ሲያስቀምጥ መሆኑን አድለር በመፅሐፉ ውስጥ ገልéEል። በተጨማሪም፣ እነዚህ ሊሳኩ የማይችሉ ፍላጎቶች ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ውስጥ በመክተት ቀዳማይ የበታችነት ስሜት እስከ መጨረሻው እንዳይለቀው ያደርጋል።

ሳም ጆህንሰን በበኩላቸው ታህታይ ምስቅልና አንድ ሰው ራሱን ከሌሎች ሲያወዳድር ብቁ ያለመሆን ስሜት እንዲሰማው ሊያደርግ የሚችል መሆኑን ከፍ ብሎ በተጠቀሰው መጽሐፋቸው ላይ ያሰፈሩ ሲሆን፣ ምክንያቱን ሲያስቀምጡም በማሕበረሰቡ ውስጥ ያለው ሥፍራ፣ አካላዊ ጉድለትና አዕምሯዊ ድክመት ያለበት ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል። የዚህ ስሜት ተጠቂ የሆነ ሰው በሚያደርጋቸው ነገሮች እርካታ የማይሰማው ሲሆን፣ ይበልጡኑ ራሱን ከሱ ይበልጥ አዋቂ፣ መልከ መልካምና በራሱ የሚተማመን ነው ብሎ በሚያስበው ሰው እግር ተክቶ የማየት ምኞት እንደሚበረታበት ገልፀዋል። እንደ ሳም ጆህንሰን አገላለጽ ታህታይ ምስቅልና እውነተኛ ወይም ሃሳባዊ ሊሆን ይችላል። ታህታይ ምስቅልና ግለሰቡ በራሱ ምናብ የሚፈጥረው እውን ያልሆነ ሊሆን ይችላል። ራሱን ከሌሎች በታች አድርጎ በመቁጠር የሚፈጥረው ሆኖ ስሜቱ በዚህ አስተሳሰብ የተጎዳ ሊሆን ይችላል። አልፍሬድ አድለር እንደገለጸው፣ ሳም ጆህንሰንም ታህታይ ምስቅልና ከሕፃንነት ዕድሜ ጀምሮ ሊከሰት እንደሚችል በመፅሐፋቸው ውስጥ ጠቅሰዋል።

ታህታይ ምስቅልና ከግለሰቦች ባለፈ ሰፊ ማሕበረሰባዊ መልክ ሊኖረው እንደሚችልና መላው የአኗኗር ባሕል ላይ ጭምር ተፅዕኖ ሊያሳርፍ እንደሚችል አድለር “Idividual Psychology” በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ አስፍረዋል። አድለር የዚህ ዓይነቱን ሁኔታ የባሕል መሸምቀቅ(cultural cringe)የሚል መጠሪያ የሰጡት ሲሆን፣ በዋነኛነት አንድ ማሕበረሰብ ባሕሉ ከሌሎች ያነሰ ወይም ዝቅ ያለ እንዲመስለውና በዚህም ሀፍረት እንዲሰማው የሚያደርግ መሆኑን አስፍሯል። የዚህ ዓይነቱ አብዛኛውን የሕብረተሰብ ክፍል የሚነካ የባህል ሽምቅቅና በርካቶችን በጅምላ የዝቅተኛነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ጥላቻቸው ከተራነት አልፎ አገራዊ ይዘት እንዲኖረው ሊያደርግ እንደሚችል በመፅሐፉ ውስጥ አስፍሯል። ይህ ሁኔታም በበኩሉ የእርስ በእርስ ግጭት አልፎ ተርፎም ጦርነት እንዲነሳ ወደ ማድረግ ሊሄድ እንደሚችል አስምሮበታል። የዚህ ዓይነቱ የታህታይ ምስቅልና ስሜት የሚሰማቸው በማሕበረሰቡ ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች በምናባቸው የሚፈጥሩትን የደህንነት ስጋት ለማስወገድ የጦርነት ነጋሪት የመጎሰም ያህል በየሄዱበት ሲጮሁ መስማት የተለመደ ነው። ቁጥሩ የበዛ የማሕበረሰብ ክፍል ጦርነቱን ለሚሰማቸው የደህንነት ስጋት ማስወገጃ መፍትሔ አድርገው የመቀበል አዝማሚያ ይኖራቸዋል። በኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ይህ ነው።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*