
ትክክለኛ ስሙ አሪስቶክልስ ይባላል። ከአስተሳሰብ አድማሱ ይልቅ የትከሻውን ስፋት ያስተዋሉ ወዳጆቹ ግን ፕሌቶ ሲሉ ይጠሩታል። ታሪክም እርሱን የሚያስታውሰው በዚሁ ስም ሲሆን ‹ሰፊው› እንደማለት ነው። ዓለም ስማቸውን ሳይጠራ ከማይውላቸው ጥቂት የግሪክ ፈላስፎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ሰው ‹ዘ ሪፐብሊክ› በተሰኘው ስራው በይበልጥ ይታወቃል። ‹ዘ-ሪፐብሊክ› በዋንኛነት የአፍላጦን (ፕሌቶ) ዲበ-አካላዊ፣ ስነ-እውቀታዊና ፖለቲካዊ እሳቤዎች የተንጸባረቁበት ተዋስኦዋዊ ድርሳን ነው። ‹የዋሻው ምስጢር› ደግሞ እንደ አስረጂ የተጠቀመበት መሳሪያ ነው።
የዋሻው ምስጢር ከልደታቸው ጀምሮ ጀርባቸውን ለዋሻው መግቢያ ሰጥተው፣ ከዋሻው ውጭ ያሉ ነገሮች ጥላ የሚመላለስበት ግድግዳ ላይ ብቻ ስለሚያማትሩ እስረኞች ያወጋል። ‹እነዚህ እስረኞች አንድም ቀን ወደኋላ ዞረው ተመልክተው ስለማያውቁ ለእነርሱ እውነት ግድግዳው ላይ ያሉ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንጂ ጥላውን የፈጠሩ ከዋሻው ውጭ ያሉ ነገሮች አይደሉም!› ይላል ፕሌቶ። እንበልና፣ በመጨረሻ ከእስረኞቹ መካከል ጥቂቶቹ ማምለጥ በመቻላቸው ዋሻው ውስጥ ያስተውሉት የነበረው ምስል የውጭው ዓለም የተንሻፈፈ ቅጂ እንጂ ራሱን የቻለ እውነት እንዳልሆነ ደረሱበት። ታዲያ ትልቁ ፈተና ያለው እዚህ ጋር ነው። ዋሻው ውስጥ የቀሩት እስረኞች፣ የሚመለከቱት ጥላ የውጭው ዓለም ቅጂ እንደሆነ እንዴት ያስረዱ ይሆን?
ይህ የአፍላጦን (ፕሌቶ) ዋሻ ከኦሮሚያ ቤተ-ክህነት አደረጃጀት ጋር እጅጉን ይቀራረባል። የአደራጅ ኮሚቴው አባላት የሚያንቀሳቅሷቸው ‹ስልጣነ ክህነት!›፣ ‹በቋንቋችን እንገልገል!› እና ‹መንጋው ተበተነ!› የሚሉ ምስሎች ለእውነት የቀረቡ የገሃዱ ዓለም የተሳሳቱ ‹ጥላዎች› ስለሆኑ በአገልጋዮችም ሆነ በምእመናኑ ዘንድ የእምነትና የእውነት ድንጋሬን ፈጥሯል። ምንም እንኳን የዋሻውን ጥላ ዓለማቸው ያደረጉ ወገኖች ሊወቅሱን፣ ሊገስጹን፣ ቀጥቅጠው ሊገድሉን እንደሚችሉ ብናውቅም እዚህ ላይ ፊታችንን ወደ እውነታው መልሰን ሀሰተኛውን ምስል ልናጠራው ይገባል። እናም ከኦሮሚያ ቤተ-ክህነት አደረጃጀት ዋሻ ወጥተን ከጥላው ባሻገር ስላለው እውነት እናወራለን።
ዋሻ እና ጥላ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት ህልውናዋን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ፈተናዎች ተጋርጠውባት ነበር። ሁሉም ግን በዘመናቸውና መፈታት ባለባቸው መንገድ እየተፈቱ አልፈዋል። ወቅታዊው የቤተክርስቲያኒቱ ፈተና ግን ከእዚህ በፊት ከነበሩት ሁሉ ይለያል።
የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት ጥያቄ የሀገሪቱ የፖለቲካ ቀውስ ከሆነው ብሄርተኝነት ጋር የተጋመደና ምዕመናኑን በሀይማኖት ፖለቲካ ውስጥ የከተተ ውስብስብ የህልውና አጣብቂኝ ነው። በአንድ በኩል አስቀድሞ ቤተክርስቲያኒቱ ለብሄረሰቡ አባላት አሉታዊ እይታ እንዳላት የሚያስገነዝቡ አስተምህሮዎች በስፋት ስለተቀነቀኑ እውቅናውን መከልከል ነገሩን የበለጠ ያወሳስበዋል። በሌላ በኩል ደግሞ እውቅናውን መስጠት አንድነቷን ይገዳደረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት አደራጅ ኮሚቴና ከጀርባው ያሉ ሀይሎች ጉዳዩ ገንኖ ከወጣበት ከጥገናው መጀመሪያ ወራት አሁን እስካለንበት የምርጫ ዋዜማ ድረስ እይታ ሊስቡ በሚችሉ ሶስት መስመሮች ይህንኑ ተልዕኮ ለማሳካት ተንቀሳቅሰዋል። የመጀመሪያውና እጅግ አደገኛ የሆነው መስመር እንቅስቃሴው ከአንድ ታሪካዊ ዳራ ጋር የተቆራኘበት ነው (ከሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ወደ ደቡቡ ከወረደው የሀገረ መንግስት ግንባታ እና የክርስትና ተስፋፍቶት ታሪክ ጋር)። ይህም አማንያኑንም ሆነ ኢ-አማንያኑን በአንድነት ያሰለፈና ቤተክርስቲያኒቱን የሰሜኑ ክፍል የባህል ወኪል ብቻ አድርጎ ይከሳል። ሁለተኛው ደግሞ፣ ሀይማኖቱን ምንም ህጸጽ የሌለበትና የአባቶች ሀዋርያት ሀይማኖት አድርጎ መውሰድ ነው። ይህ ደግሞ ችግሩ ያለው ሀይማኖቱ ሀገርኛ (ሎካላይዝድ) ከተደረገበት ይዘት ጋር ብቻ እንደሆነ ለማስረገጥ ይሞክራል። ሶስተኛውና የመጨረሻው ቤተክርስቲያኒቱን እንደተቋም የቀኝ አገዛዝ መሳሪያና የተንኮል ተባባሪ አድርጎ ማስቀመጥ ሲሆን ጉዳዩን ትኩረት ሳቢ እንዲሆን ያደርገዋል።
እነዚህ ሶስት አውታሮች የኦሮሚያ ቤተ-ክህነት ዋሻ ውስጥ ለተጠለሉና ግድግዳው ላይ ለሚያማትሩ እስረኞች(አገልጋዮችና አማንያን) ቤተ-ክርስቲያኒቱ የአማራና ትግሬ ወኪል እንደሆነች፣ ውክልና ለሌላቸው ምዕመናን በቋንቋቸው አገልግሎት ባለማግኘታቸው እየተበተኑ እንደሆነ፣ የእንቅስቃሴው መሪዎች ከተቆርቋሪነት ውጭ አዲስ ሀይማኖት የመመስረትም ሆነ ሲኖዶሱን የመሰንጠቅና አንድነቷን የመበተን ዓላማ እንደሌላቸው፣ ቤተ-ክርስቲያኒቱ የወራሪዎች የተንኮል መሳሪያ እንደሆነች የሚያስገነዝቡ ምስሎችን ያሳዩዋቸዋል። ሰንሰለቱን በጥሰው ከዚህ ዋሻ መውጣትና መጋፈጥ ለማይፈልጉ ሁሉ ይህ የመጨረሻው እውነት ነው።
በአፍ መፍቻ ቋንቋ መንፈሳዊ አገልግሎት መሰጠቱን (እየተሰጠ መሆኑን)፣ የተጻፉ ቅዱሳት መጻህፍት መታተማቸው እና መንፈሳዊ ዝማሬዎች መኖራቸውን እዚህ ላይ ገታ አድርገን አንድ መሰረታዊ ጥያቄ እንሰንዝር፡-
‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አገልግሎት ሙሉ በሙሉ በአፋን ኦሮሞ ቢደረግና የሊቃነ ጳጳሳቶቿም ሆነ የካህናቷ ቁጥር በአመዛኙ የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላት ቢሆኑ የኦሮምያ ቤተ-ክህነት ጥያቄ መቋጫ ያገኝ ነበርን?››
ከዋሻው ውጭ
ቀደም ብለን የሰነዘርነውን ጥያቄ ተከትለን ከዋሻው ውጭ ያለውን እውነት እንመልከት። የኦሮሚያ ቤተ-ክህነትን የማቋቋም እንቅስቃሴ የመጨረሻው ግብ አገልግሎቱን በአፋን ኦሮሞ ማድረግና ወንጌልን ማስፋፋት አይደለም። ራሱን የቻለ አንድ ቀኖና ላይ የተመሰረተ ቤተ-ክርስቲያን ማቋቋም እንጂ። እናም ‹የኢትዮጵያ› በምትባል ቤተ- ክርስቲያን ውስጥ አገልግሎቱ በአፍ-መፍቻ ቋንቋ ቢሰጥ ‹የኦሮሞ› ቤተ-ክርስቲያን እውን እስካልሆነ ድረስ ተቀባይነት አይኖረውም። ይህም ነጮቹ ‹አውቶሴፋሊ› የሚሉት ዓይነት ግንጠላ መሆኑ ነው።
አውቶሴፋሊ፣ ኮምዩኒዝም ከተዳከመበት 1980ዎቹ (እ.አ.አ) በኋላ በምስራቁ ዓለም በስፋት የተስተዋለ በአስተዳደራዊ ሽፋን ፖለቲካዊ ዓላማን አንግቦ የሚቀነቀን የእውቅና ጥያቄ ነው። እንዲህ ያለው ጥያቄ በተለይ በአንድ ፌደራላዊ ስርዓት ውስጥ ማዕከላዊ መንግስቱ ሀገሪቱን አንድ የማድረግ አቅሙ በተዳከመበት፣ ርዕዮተዓለማዊ ሽግግር እያደረገ ባለበት እና ትኩረቱን ሙሉ በሙሉ ክፍተቶችን በመሙላት ላይ በሚያደርግበት ወቅት ይወለዳል። በ1980ዎቹ (እ.አ.አ) ከኮሚዩኒዝም መውደቅና ከቤልግሬድ መዳከም ጋር ተያይዞ የሰርቢያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ ከ1992 ዓ.ም (እ.አ.አ) እስከዚህ ዘመን ድረስ ደግሞ ከኮሚዩኒስት ርዕዮተዓለም ጋር በተያያዘ የቡልጋሪያ ቤተክርስቲያን መሰል ፈተና ውስጥ ወድቀዋል።
የዩክሬን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ደግሞ ቀድመን ከጠቀስናቸው አብያተክርስቲያናት ይለያል። የዕውቅና ጥያቄው የዘር ሀረጋቸውን ከሀፕስበርግ ስርወ-መንግስት በሚመዙት የዩክሬን ቋንቋ ተናጋሪ ዩክሬናውያን እና የሩስያ ቋንቋ ተናጋሪ በሆኑት ዩክሬናዊያን መካከል በተፈጠረ የብሄርተኝነት ፖለቲካ የተወለደ ነው። ከዚህ በፊት በዩክሬን የሚገኙ የኦርቶዶክስ አብያተክርስትያናት ተጠሪነታቸው ሞስኮ ለሚገኘው የሩስያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ነበር። ይህ ደግሞ እንደ ምዕራባዊ ዩክሬናዊያኑ አገላለጽ የታሪክና የፖለቲካ ተጽዕኖ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል። ስለዚህ የዩክሬን ፖለቲካ በዩክሬናውያንና በሩሲያውያን መካከል የልዩነት ፖለቲካን ለማኖር አመቺ በሆነበት ወቅት የሞስኮውን ማዕከል ወደ ኪየቭ ከማዞር የተሻለ አማራጭ ሊኖር እንደማይችል በሃይማኖቱ ልሂቃንና በብሄርተኝነቱ አቀንቃኞች ታመነበት። የኪዬቭ ሲኖዶስን የማቋቋም ጥያቄም ይህንኑ ተከትሎ ወደ ፊት ቀረበ። ዛሬ ዩክሬን ሶስት የኦርቶዶክስ አብያተክርስቲያናት እርስ በርስ የተፋጠጡባት ሀገር ሆናለች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ፈተና ከዚህ የተለየ አይደለም። የኦሮሚያ ቤተክህነት የማቋቋም ጥያቄ ብሄርተኝነት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጎልቶ በወጣበትና ክልል እንሁን የሚሉ ድምጾች ዓየሩን በተቆጣጠሩበት ወቅት የተገለጠ ጊዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጂ ነው። ይህ አጥፊ ተልዕኮን የሰነቀው እንቅስቃሴ ልክ እንደ ዩክሬንያውያኑ ‹ነፃ ሀገር፤ ነፃ ቤተክርስቲያን› በሚል የገንጣዮች ስሌት በተቀመረ መርህ ይመራል። ከጀርባ ያሉ ሀይሎችም ከዚህ በፊት ይህንን ስሜት (የመገንጠልን) በማንጸባረቅ ይታወቃሉ። ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ምዕመናንና ካህናት በላይ የጉዳዩ ዋና ባለቤት ሆኖ ብቅ ያለው የቀድሞው አክቲቪስት የአሁኑ ፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ በአንድ ወቅት ‹Free Oromia! Ethiopia Out of Oromia!› የሚል መፈክር ያሰማ እንደነበር እዚህ ጋር መዘንጋት የለበትም።
ከዋሻው ውጭ በእነ ቀሲስ በላይ የሚመራው ጎራ ከእነጃዋር ጋር ተዋስኦአዊ ግንኙነት በማድረግ ነጻ ሀገር ለመመስረት የሚያስችሉ መደላድሎችን ለመፍጠር ደፋ ቀና እያሉ ይገኛሉ። የኦሮሚያ ቤተክህነትን በማቋቋም የመረጋጋት አንዱ መንስኤ የሆነውን የብሄርና የሀይማኖት መስቀለኛ ልዩነት (crosscutting diversity) እያጠሩ፣ በብሄር ለተከፋፈለው ህዝብ የተረፈውን የቤተክርስቲያኒቱን አንድነት ለመናድ መስቀልና ነፍጥ እየታጠቁ ነው። ዋሻው ውስጥ የከተሙት ደግሞ ከጀርባ ያለውን እውነት ሳይሆን የሚመለከቱትን ጥላ እስከተከተሉና ከ‹ነጻ ሀገር!› ውጥኑ ጎን እስከቆሙ ድረስ የትኛውም ሀጢያታቸው ይሰረይላቸዋል።
Bertulen Fetarie Kenanete Ga Yehun