
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ አዲስ አበባ በተለያዩ ክስተቶች ስትናጥ ቆይታለች። ከተማዋን ላለፉት ሃያ ሰባት ዐመታት ሲመራ የቆየው ሕወሓት/ኢሕዴግ ፖሊሲ አውጥቶ በሕግና በሥርዐት ከማስተዳደር ይልቅ፤ በመቆጣጠር ላይ አተኩሮ ያሻውን ሲያደርግ እንደነበረ ይታወቃል። ከ2010ሩ ለውጥ ወዲህም ከተማዋን የመሩት ከቀደመው የተሻሉ አልነበሩም። በዚህ ሳቢያም፣ በብዙ ችግሮች ውስጥ እንድታልፍ ተገድዳለች። ከቀድሞ ሥርዐት የተላላፉትንም ሆነ ከለውጡ በኋላ የተከሰቱት ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን ዛሬም ድረስ እንደ ተሸከመች ነው። በእነዚህ ውስብስብ ችግሮች ተወጥረው በጣር የሚኖሩ ነዋሪዎቿም ‹የከተማዋንም የእኛንም ችግሮች ይፈቱልናል። ከስጋት እውጥተው በሰላም ያስተዳድሩናል፤› ያሏቸውን ተወካዮች በድምጻቸው መርጠዋል፤(“እስቲ አልጋው ይርጋ” ብላ እንደመረጠችው እናቴና መሰሎቿ።)
ባሳለፍነው ሳምንት የአዲስ አበባ መስተዳድር ዐዲስ ካቢኔ ሰይሞ፣ የቀድሞዋን ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤን ከንቲባ አድርጎ ለአምስት ዐመት ሾሟቸዋል::
አዲስ አበባ ያለባትን ዘርፈ ብዙ ውስብስብ ችግሮች የሚፈታላት አውቀት፣ ክህሎትና ልምድ ያለው፣ ከተሜነት ከገበሬ ማኀበር አመራርነት ጋር የማይምታታበት ጠንካራ አመራርን በብርቱ ትሻለ ች።
በዚህ ዐውድ ዐዲሱ ካቢኔ ሊያውቃቸው ይገባል ያልኳቸውንና ባላፉት ሦስት ዐመት በከተማዋ አመራሮች ላይ የነበሩትን ችግሮችም ለማንሳት እሻለሁ።
የሦስት ዐመቱ ጉዞ!
አዲስ አበባ ተነግረው የማያልቁ ብዙ ችግሮች ያሉባት ከተማ ናት። የመኖሪያ ቤት እጦት፣ የትራንስፖርት፣ የሥራ-አጥነት… ብዙ ብዙ። እነዚህ ከቀደመው ሥርዐት በውርስ የተላለፉት ላይ፣ ባለፉት ሦስት ዐመት የተጨመሩ ችግሮች ናቸው። ከተማዋ የምትመራበት ፖሊሲ አለመኖሩ ደግሞ፣ የአዲስ አበባ የወሰን እና ሌሎች ጉዳዮች ተደማምረው፣ ዛሬ ድረስ ባለቤት አልባ አድርገዋት ቆይቷል።
ከ2010 ዓ.ም ወዲህ ያለውን ሁነት በጥቂቱ እንመልከት። ከተማዋ በሦስት ዐመት ውስጥ ሁለት ከንቲባዎችን አፈራርቃለች። ሁለቱ ከንቲባዎች ማስተዳደር ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ የተሠሩትን ተግባራት ስንመለከት፣ አሁንም ከተማዋ የተሻለ አመራሮች እንዳልነበራት የሚያሳዩ በርካታ ሁነቶችን መጥቀስ እንችላለን። አዲስ አበባ ከዘመነ ሕወሓት/ኢሕአዴግ እስከ ብልጽግና ድረስ ሁነኛ አመራር እንዳላገኘች ለሁሉም በግልጽ የሚታይ ነው። ለዚህ ደግሞ ከመስተዳድሩ ቁንጮዎች ጀምሮ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ በሹመትና በዝውውር በአመራርነት ላይ ተቀምጠው የነበሩትሰዎች የፓርቲ ታማኝነት የነበራቸውና የራሳቸውን ኔትዎርክ ዘርግተው በሕገ-ውጥ ተግባራት፣ በተለይ መሬት ዘርፋ፣ መታወቂያ እደላ እና በሕገ-ወጥ የመንግሥት ቤት ወረራ ላይ ተሰማርተው መቆየታቸው ይጠቀሳል።
Be the first to comment