ያዘቀዘቀችው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምበር | አበበ አካሉ ክብረት

“መሪዎች ከሕዝብ የሚነሳን ወይም ከተመሪዎቻቸው የሚሰነዘርን ተቃውሞና ሃሳብ እንደ አስፈላጊነቱ የሚቀበሉ ካልሆኑ፣ ራሳቸው ሞገደኛ ይሆናሉ ማለት ነው። ይህም መሪነት የሚያስፈልገውን የጋራ ሕልምን ትቶ፣ የራሱን የመሪውን ሕልም ብቻ ይዞ ስለሚጓዝ፣ መሪውን ከመሪነት ወደ ገዥነት ይቀይረዋል።” ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) መደመር መጽሐፍ።

የኢሕአዴግን “ፍጻሜ” ተመርኩዞ፣ በለውጥ ኃይል ስም የተሰየመው መንግሥት ‹እኔ አሻግራችኋለሁ› የሚል ቃል ገብቶ ሥልጣን ከጠቀለለ በኋላ፤ አገሪቱን በኮሮኮንቻማ መንገድ እየናጠና በማይጨበጥ ተስፋ እየሸነገለ መጓዝ ከጀመረ አራተኛ ዐመቱ እየደፈነ ነው። ቡድኑ ስሙን ቀይሮ፣ ነገር ግን በተለመደው ግብሩ በዶ/ር ዐቢይ አህመድ ዘዋሪነት አገሪቱን እንዳሻው ማሽከርከሩ ውሃ የመጠጣት ያህል ቀሎታል። እኛም፣ በየጊዜው የሚጋገሩ፣ ግን የማይጎረሱ የተስፋ እንጀራዎችን እንደ ሙሴ ዘመን መና ወደ ሰማይ አንጋጠን እየጠበቅን፣ መሪና ተመሪው በውል በማይለይበት አገር በግራ-መጋባት ቀጥለናል።

በጥቅሉ፣ ኢትዮጵያችን ዐዲስ አንደተገፈፈ የበሬ ቆዳ በየአቅጣጫው ተወጥራለች። ክቡር የሆነው የሰው ልጆች ህይወት በተልካሻ ምክንያት በየቀኑ ይቀጠፋል። በትሕነግ አምባገነናዊ አገዛዝ ዘመን ዴሞክራሲን ለማንበር ይደረግ የነበረው ሰላማዊውም ሆነ የነፍጡ ትግል፣ ዛሬ ቅንጦት ከመሆኑ በተጨማሪ፤ አገርን ከፍርሰት ለመታደግ ወደ መንፈራገጥ ተሸጋግረናል።

ከዚህ በተቃራኒው፣ ብልፅግና “አልበላሽምን ምን አመጣው?” ብሂልን በሚያስታውስ መልኩ፣ ‹ኢትዮጵያ አትፈርስም› የሚል የሰርክ ዲስኩርን የሙጢኝ ብሏል። ይሁንና፣ ድርጅቱ አገር እንዳይፈርስ በመሥራት እና በመፈክር መሃል ጥልቅ ስፋት ያለው ሸለቆ መኖሩን ዘንግቷል። ሌላው ቀርቶ፣ ዛሬ የእለት ዜና የሆነው የበዛ መከራ፣ የሕዝብ ሰቆቃና ዋይታ ማብቂያው መቼ እንደሆነ ማወቅ አይቻልም። አንዱ ሽንቁር ሲደፈን፣ ሌላ እየተፈጠረም፣ አገሪቱ በመጣፊያና በውታፍ መአት ድሪቶ እየመሰለች ነው።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*