ለድርድር የሁለትዮሽ ጫና | ርእስ አንቀጽ

ፌደራል መንግሥቱ እና በሕወሓት መሃል የተቀሰቀሰው ጦርነት ወደ ከፍተኛ ደረጃ መሸጋገሩ ይታወቃል። የዐውደ ውጊያው ተሳታፊዎችም ግጭቱ ሲጀመር ከነበሩት የመከላከያ ሠራዊት እና የዐማራ ልዩ ኃይል በተጨማሪ፤ የሁሉም ክልል ልዩ ኃይሎች ሆነዋል። በዚህ ላይ፣ ሰሞነኛው የፌደራል መንግሥቱ ጥሪ እና የዐማራ ክልላዊ መንግሥት የክተት አዋጅ፣ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሕዝብ ወደ ዘመቻ እና ማሰልጠኛ ጣቢያዎች እንዲተም እያደረገ መሆኑን ታዝበናል። መቼም፣ ይህ ዐይነቱ ጦርነት በሁለቱም ወገኖች ላይ የሰዋዊ ጉዳቱንም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራውን በከፍተኛ ደረጃ ሊያንረው እንደሚችል ሳይታለም የተፈታ ነው።

ይህም ሆኖ፣ በዚህ ዐውድ የምናነሳው አጀንዳ፣ ከድርድር ጋር በተያያዘ የሚቀርበው ጥሪም ሆነ ጫና ወደ አንድ ወገን ብቻ ማዘንበሉ፣ መፍትሄ ሊያመጣ እንደማይችል አጽንኦት መስጠት ነው።

ሁላችንም እንደምንገነዘበው፣ የእርስ-በርስ ጦርነት ከሚያነብራቸው ጉዳቶች መሃል፣ ሁለቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ ጠባሳና ቁርሾ ጥለው የሚያልፉ ናቸው። ቀዳሚው፣ በጦርነቱ ከመተላለቅ በቀር፤ የተናጠል አሸናፊ ወይም የተናጠል ተሸናፊ ካለመኖሩ ጋር ይያያዛል። ሁለተኛው፣ የመጨረሻው ውጤት “የሞተው ባልሽ፣ የገደለው ወንድምሽ…” የመሆኑ አይቀሬነት ነው።

ከዚህ አኳያም፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ችግሩ በድርድር እንዲፈታ ከውስጥም ከውጪም ምክረ-ሃሳቦች እየተሰሙ መሆኑ ተስፋ ሰጪ ነው። ይሁንና፣ “ተደራደር” የሚለው ግፊት፣ በፌደራሉ መንግሥት ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑ፣ ጥሪውን ጎደሎ ሊያደርገው አንደሚችል የተዘነጋ ይመስላል። በተለይ የትግራይ ተወላጆች ይህንን የመፍትሄ ሃሳብ ደፍረው ሲያነሱት አለመስተዋሉ የክፍተቱ ዋንኛ ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል። ስለዚህም ግጭቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ከፌደራሉ በተጨማሪ፤ ሕወሓት ላይም ጫና የማሳደሩ ግዴታ አስፈላጊ ነው። ከአንድ ወር በፊት እና ከትላንት በስቲያ ሊተገበሩ የማይችሉ (ወይም ሆን ብሎ ከድርድር ለማፈንገጥ) ይፋ ያደርጋቸውን ቅድመ-ሁኔታዎች ወደ ጎን ብሎ፤ ራሱን ለእውነተኛ የሰላማዊ መፍትሄ እንዲያዘጋጅ ማስገደድ ይገባል።

ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ዛሬ ሐምሌ 24/2013 ዓ.ም ዘጠነኛ ወሩን ቢደፍንም፤ እስከ አሁን በነበረው የዐወደ ውጊያ ውሎ ለዘለቄታው አሸንፎ ሊወጣ የሚችል ወገን አለመኖሩን መታዘባችን፣ ‘ብቸኛው አማራጭ ድርድር ነው’ የሚለውን ሃሳብ ይበልጥ እንድናተኩርበት ያስገድደናል። በተረፈ፣ ‘ሕወሓት እዚህ ደረሰ’፣ ‘እገሌ ከተማን ተቆጣጠረ’፣ ‘ይሄን ያህል ሺሕ ወታደሮች ማረከ’፣ ‘ክፍለ ጦሮችን ደመሰሰ’ እና የመሳሰሉት ዜናዎች (የቱ እውነት፣ የቱ ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ማጣራቱ እንደተጠበቀ)፤ መከላከያ ሠራዊቱ መቀሌን ተቆጣጥሮ ከለቀቀበት ድል የተለየ ፋይዳ እንደሌለው መረዳቱ ጠቃሚ ነው። በዚህ ላይ፣ ጦርነቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ ሕዝብ ለሕዝብ መሸጋገሩ የተራዛሚነቱ አይቀሬነት አስረጋጭ መሆኑን ልብ ይሏል።

“ፍትሕ መጽሔት”፣ እነዚህን ኹነቶች ከግምት በማስገባት የትግራይ ልሂቃን፣ አክቲቪስቶች እና ማኀበረሰቡ ሕወሓት ወደ ድርድር እንዲመጣ ግፊት የማድረግ ኃላፊነታቸውን ይወጡ ዘንድ ትመክራለች። መቼም፣ በዓለም የጦርነቶች ታሪክ ወታደር እንጂ፤ ሕዝብ ተሸንፎ እንደማያውቅ ለመረዳት ጥቂት ድርሳናትን ብቻ ማገላበጡ በቂ ነው። በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ጦርነት ደግሞ የመከላከያ ሠራዊት፣ የዐማራ እና የትግራይ ልዩ ኃይሎች ብቻ መሆኑ ቀርቶ፤ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም ብሔረሰቦች የሚሳተፉበት ሆኗል።

ከዚህ በተጨማሪ ዛሬ፣ እንደ ደርግ ዘመን፣ ከሕወሓት ጋር የሚተባበር “ኢሕዴን/ብአዴን” አለመኖሩ በግላጭ ታይቷል። ይህ መሬት የረገጠ እውነታም፣ መከላከያ ሠራዊቱ ትግራይ መቆየት እንዳልቻለው ሁሉ፤ ሕወሓትም ከመቀሌ እስከ አዲስ አበባ በሰላም መድረስ የሚችልበት እድል አለመኖሩን ያመላክታል።

በጥቅሉ፣ ለሁሉም የሚጠቅመው በሰጥቶ መቀበል መንፈስ የተቃኘ ድርድር በመሆኑ፤ የትግራይ ተወላጆች፣ ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ሕወሓትን የሚያስገድዱበት ጥልቅ ዝምታቸውን መስበር ይጠበቅባቸዋል። ይህ ግን፣ ‹የፌደራል መንግሥት እና የዐማራ ክልል ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ እንዲመጡ ግፊት ማድረግ አይስፈልግም› ማለት አይደለም። በጦርነት ዘላቂ ድል እንደማይገኝ የሚረዱ ተጋሩዎች፣ ከአርምሟቸው ወጥተው የድርድር አጀንዳ እንዲያቀነቅኑ ለማስታወስ ነው።

የፌደራል መንግሥቱን በተመለከተ፣ አሜሪካ እና የአውሮፓ ኀብረትን ጨምሮ፤ የተለያዩ ኢትዮጵያውያኖች ወደ ድርድር እንዲመጣ ሲወተውቱ መቆየታቸው ይታወቃል። ከወር በፊት የተናጠል ተኩስ የማቆም እርምጃ ወስዶ ትግራይን መልቀቁም፣ እንደ በጎ ጅምር ሊቆጠር የሚገባው በመሆኑ ነው።

በዚህ ርዕሰ አንቀጽ፣ ሕወሓትም ተመሳሳይ ፍላጎት እንዲያሳይ የሚጠይቁ የተጋሩ ድምጾች ይሰሙ ዘንድ ለማስታወስ እና ለማበረታታት እንወዳለን።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*