
በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ ብቻ ተገድቦ የሚካሄደው ስድተኛው ዙር ምርጫ በቀናት የሚቆጠሩ ጊዜያት ብቻ ቀርቶታል። ከዚህ ጋር ተያይዞም የተለያዩ ችግሮች እንዳይፈጠሩ መንግሥት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን እየገለፀ ነው።
ይህ ምርጫ የሚካሄደው ለሃያ ሰባት ዐመት የአገሪቱን ዋና ዋና የሥልጣን መዋቅር ይዘው የነበሩት የሕወሓት አባላት፣ ራሳቸው ያወጡትን ሕገ-መንግሥት ተቃርነው በትጥቅ የተደገፈ የተቃውሞ እንቅስቃሴ እያደረጉ ባለበት ከመሆኑ በተጨማሪ፤ ለውድድር የቀረቡት ፓርቲዎችም ከብልፅግና ጋር ገና ከመነሻው በበርካታ ጉዳዮች ሲወዛገቡ እንደከረሙ ይታወቃል። ከዚህ አኳያም፣ በቀጣይ ያልታሰቡ ችግሮች ሊፈጠሩ የሚችሉባቸው ክፍተቶች ሊኖር ስለሚችል፣ ሁሉም የፀጥታ መዋቅር ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አይጠፋውም ተብሎ ይታመናል።
ይህ ምርጫ ከዚህ ቀደሞች የሚለይበት ዋንኛው ጉዳይ ጠመንጃ አንስተው ይፋለሙ የነበሩ ድርጅቶች፣ በ“ሰላማዊ መንገድ ለመታገል” በሚል ወደ አገር ቤት ከእነ ታጣቂዎቻቸው እንዲገቡ ከተደረገ በኋላ የሚካሄድ በመሆኑ ነው። ከእነዚህ ብረት-ነካሽ ኃይሎች ውስጥ ብዙ ተዋጊዎች እና ተከታይ ያሉት የ“ኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ)”፤ እንዲሁም የ“ኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ)” ከምርጫው ራሳቸውን ማግለላቸውን ከግምት በመክተት፣ ለፈጠሩ የሚችሉ አደገኛ ሁኔታዎችን በቢሆን ሃሳብ እያሰሉ፣ የአገርንም ሆነ የሕዝብን ሰላምና ደኀንነት መጠበቅ ከምንጊዜውም በበለጠ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው።
ከኦሮሞ ድርጅቶቹ በተጨማሪ፣ በሶማሌ ክልል የሚወዳደረው የ“ኡጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባር (ኦብነግ)” እና የ“ቤንሻንጉል ሕዝቦች ነፃ አውጪ ንቅናቄ (ቤሕነን)” ከኤርታራ እና ከተለያዩ የአገሪቱ በረሃዎች ተዋጊዎቻቸውን ይዘው ወደ አገር ቤት መግባታቸው ይታወቃል። በተለይ በቤንሻንጉል ክልል መተከል እና ካማሼ ዞኖች እየተከሰተ ካለው የንፁሃን ጭፍጨፋ አኳያ፣ በሁለቱ ዞኖች ምርጫ የሚደረግ ባይሆንም፤ በአካባቢው የሚንቀሳቀሰው አማፂ እና የሽፍታ ቡድን ከጎረቤት አገራት በሚደረግለት የትጥቅና ስንቅ እገዛ፣ አጠቃላይ ክልሉን ሊረብሽ የሚችልበት አጋጣሚ እንዳይፈጠር፣ ሁሉም የፀጥታ መዋቅሮች በተናበበ መልክ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
ሌላኛው ትልቅ ስጋት ያለው በአገሪቱ መዲና አዲስ አበባም ነው። መነሻቸውን ኦሮሚያ እና ትግራይ ያደረጉ በኀቡዕ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች ተደብው መኖራቸውን መንግሥት ጭምር የሚያውቀው ከመሆኑ አኳያ፣ ከምንጊዜውም በላይ ተጠንቅቆ መጠበቅ ያስፈልጋል።
በዚህ ላይ በግልጽ እንደምናውቀው አዲስ አበባ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች የበለጠ ከፍተኛ የምርጫ ፉክክር የሚደረግባት ከተማ ነች። ባለፉት ሁለትና ሦስት ዐመትም የከተማዋን ፀጥታ ለማደፍረስ እና የነዋሪዎቿን ደኀንነት አደጋ ላይ ለመጣል የተለያዩ ሙከራዎች ሲደረጉ ቆይተዋል። አሁን የምርጫ ወቅት መሆኑ ደግሞ ለረብሻና ለጥፋት ለተዘጋጁ ኃይሎች ከወትሮ በተለየ አመቺ ነው። ከዚህ አኳያም ድብቅ ፍላጎት ያለቸውና በኀቡዕ ጭምር የተደራጀ ታጣቂ ክንፍ ያሰረጉ ቡድኖች፣ ምርጫውን ተገን አድርገው የእስር በርስ እልቂት ለመፍጠር መንቀሳቀሳቸው ተገማች ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድም ከሁለት ወር በፊት “ዐዲስ ወግ” በተሰኘ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው በሰጡት አስተያየት፣ ከምርጫው ጋር ተያይዞ የሚያሰጋቸው “ድምጼን ተዘረፍኩ” የሚል የሕዝብ ተቃውሞ ሳይሆን፤ የታጠቁ ኀቡዕ ቡድኖች በመራጭ እና ተመራጩ ላይ ሊፈጽሙት የሚችሉት ግድያዎች እንደሆነ በግልጽ መናገራቸው ይታወቃል። ይህም ሆኖ፣ እስከ አሁን ድረስ መንግሥታቸው እነዚህን ኀቡዕ ቡድኖች በቁጥጥር ስር ማዋሉን ወይም አደጋ በማያደርሱበት ደረጃ ከተማዋን ስለመቆጣጠሩ የተሰማ ነገር አለመኖሩ ስጋቱን ያንረዋል።
ሌላው የስጋት መነሾ ተደርጎ የሚታሰበው፣ “የአዲስ አበባ ባለቤት ነኝ” በሚለው የኦሮሚያ ብልፅግና እና የከተማው ነዋሪ መካከል ያለው ስር-ሰደድ መፋጠጥ፣ ነገሮችን ወደ አልታሰበና አላስፈላጊ አቅጣጫ ሊገፋ የሚችልበት ዕድል ሰፊ መሆኑ ነው። በዚህ ላይ የኦሮሚያ ብልፅግናም ሆነ የአመራር አባሉ የሆኑት የአዲስ አበባ ከንቲባ አደናች አበቤ ከከተማው ሕዝብ ፍላጎት ውጭ የሆኑ ርምጃዎችን ሲወስዱና ሲያስወስዱ መቆያተቸው ይታወቃል።
ባለፈው ዐመት መጨረሻ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሚያ ክልል ወረዳዎች የተሰባሰቡ ወጣቶች ከተማውን ለመረበሽ ከሞከራቸውም በዘለለ፤ በበርካታ ህንፃዎች እና መኪናዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸው ይታወሳል።
በጥቅሉ፣ ከላይ የተጠቀሱትን እና ሌሎች ምልክቶችን ከግምት በመክተት ከቀናቶች በኋላ የሚካሄደውን ምርጫ (ውጤቱን ተከትሎም ሊሆን ይችላል) ለሁከትና ብጥብጥ ሊጠቀሙበት የሚችሉ ቡድኖች መኖራቸውን ታሳቢ ያደረገ ጠንካራ የፀጥታ ጥበቃ ስምሪት መስጠት ቀዳሚው መንግሥታዊ ግዳጅ እንደሆነ ለማሳሰብ እንወዳለን።
Be the first to comment