ምርጫ፣ አገር እና የሕዝብ ደህንነት

መደነቃቀፍ የበዛበት ስድስተኛው አገር ዐቀፍ ምርጫ ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ከምርጫ ቦርድ፣ ከመንግሥት እና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች በተጨማሪ፤ ምርጫው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሙሉ የዜግነት ድርሻ እንዳለባቸው እሙን ነው።

ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዐት የምትሸጋገርባቸውን ተደጋጋሚ ዕድሎች በተለያየ ጊዜ ብታገኝም፤ ሁሉም መምከናቸው የማይካድ እውነታ ነው። ለዚህ ደግሞ፣ ዋንኛ ተጠያቂዎቹ የፖለቲካ መሪዎች፣ የፀጥታ ተቋማት፣ ጥቅመኛ ልሂቃን፣ አድር- ባይ ዜጎች እና ምንግዴ የተጫነው አብዛሃው ሕዝብ የመሆኑ ጉዳይ ለክርክር አይቀርብም።

አሁንም ከፊታችን ያለው ዕድል በእንደ እነዚህ ዐይነቶቹ ስግብግቦች እንዳይመከን፣ በትኩረት መከታተል የሁሉም ዜጋ ግዴታ ነው። እንደ አገርም ሆነ እንደ ሕዝብ በአንድነት መቀጠል የሚቻለው፣ እንደ ቀድሞው በ“ብረት እና በመሰዋትነት” ሳይሆን፤ በዴሞክራሲያዊ ሥርዐታ እና መብቶችን በማክበር ብቻ መሆኑ በምልዓት የሚያስማማ ደረቅ ሃቅ ነው። ይህ ምርጫም፣ ቢያንስ ለቀጣዩ ምርጫ ትልቅ መሰረት የሚጣልበት እንዲሆን ማድረግ የበዛ ጠቀሜታ አለው።

ከዚህ ባለፈ፣ አገሪቱ በርካታ መልስ የሚፈልጉ ጥያቄዎችን የተሸከመች እና በአያሌ ችግሮች የተተበተበች ከመሆኗ አኳያ፣ የዘንድሮው ምርጫ ብቻውን ምሉዕ-በኩሌ መፍትሄ የሚሰጥ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። ይህም ሆኖ፣ በአንድ አገር ልጅነት የመግባባት መንፈስ ለመቀጠል፣ ልዩነቶችን ለማጥበብ እና ለዘለቄታው መፍትሄ ለማበጀት መደላድል የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው።

እዚህ ጋ ሊሰመርበት የሚገባው ትልቅ ጉዳይ፣ ምርጫውን በማጭበርበር አቅጣጫውን ለማስቀየስም ሆነ ውጤቱን በፀጋ ላለመቀበል ማፋፈር፣ ሊታረም ለማይችል ስህተት የሚዳርግበት አጋጣሚ የመፍጠሩን አይቀሬነት ነው።

“ፍትሕ መጽሔት”ም ሁሉም ወገን ይህንን ከግምት ከትቶ፣ ሕጋዊውን እና ሰላማዊውን መንገድ ብቻ ሊከተል እንደሚገባ አጥብቃ ታስገነዝባለች።

በተለይ ምርጫ ቦርድ እና የምርጫ አስፈጻሚዎች፣ እንዲህ ዐይነቱ ችግር የሚፈጠርባቸውን ቀዳዳዎች በሙሉ የመድፈን ግዴታቸውን ከመቼውም በላይ መወጣት የሚጠበቅባቸው በድምጽ መስጠቱ እና በቆጠራው ላይ እንደሆነ ይጠፋቸዋል ተብሎ አይታሰብም። ከተቋሙ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ ግልጽ ስህተቶችም ሆኑ አድሏዊ የሚመስሉ ድርጊቶች የኹነቱን አጠቃላይ ገጽታ እንዳይቀይሩ እና የግጭት መነሾ እንዳይሆኑ፣ የበዛ ጥንቃቄ የማድረጉን አሰፈላጊነት ልብ ይሏል።

ሁሉም የፀጥታ መዋቅር፣ በድምጽ አሰጣጡ ወቅት እና በድኀረ-ምርጫው የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን የመቆጣጠር ኃላፊነታቸውን ሲወጡ፣ ከገዥው ፓርቲም ሆነ ከተቃዋሚ ወገንተኝነት በራቀ መንፈስ መሆን እንዳለበት ጠንቅቀው ያውቃሉ ተብሎ ይታመናል። የእነዚህ አካላት ሚና፣ ከአገሪቱ ህልውና ጋር በጥብቅ ከመቆራኘቱ አኳያ፣ ስምሪታቸውም ሆነ የአደጋ መከላከል ግዳጃቸው ሕግን እና ሕግን ማስከበር ላይ ብቻ ያተኮረ ሊሆን ግድ ይላል። ከዚህ በተቃራኒው፣ ወደ ፓርቲ ውገና የሚያመዝኑ ከሆነ፣ ነገሩ ወደ እርስ በርስ ጦርነት (Civil War) ተቀይሮ ሁሉም ዋጋ የሚከፍልበት፣ አገሪቱም ሲሟረትባት እንደከረመው የምትፈርስበት ሊሆን የሚችልበት ክፍተት ሊፈጠር ይችላል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የድኀረ-ምርጫ ቅሬታዎችም ሆኑ ጥያቄዎች የሚኖራቸው ፓርቲዎች፣ በሰላማዊ መንገድ እና በሕግ አግባብ ብቻ እንዲፈቱላቸው የማድረግ ግዴታቸውን ፈጽሞ መዘንጋት የለባቸውም።

በጥቅሉ፣ ከ48 ሰዓት በኋላ የሚካሄደው ምርጫ ውስን ግብና ዓላማ ያለው መሆኑን በማስታወስ፣ ሌሎች ስር- ሰደድ ጥያቄዎች መልስ ሊያገኙ የሚችሉበት አማራጮች መኖራቸውን ታሳቢ ማድረጉ ይመከራል። ይህ ምርጫ የዓለም ፍጻሜ የሚታወጀበት ባለመሆኑም፤ ከምንም በላይ የዜጎች ደህንነት እና የአገር አንድነት ሊቀድም ይገባል።

የዛሬ ተሸናፊ፣ የነገ አሸናፊ ነው። የዛሬ አሸናፊ ደግሞ የነገ ተሸናፊ መሆኑ አይቀርም። ስለዚህም፣ ምርጫ ቦርድ እና ሌሎች የታዛቢ ቡድኖችን መስክርነት የመቀበልም ሆነ ያለመቀበሉ ጉዳይ ከስሜት ይልቅ፤ በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ መሆን እናዳለበት፣ ለሁሉም ወገኖች ደግመን ደጋግመን ለማስታወስ እንወዳለን።

አገራችንንና ሕዝቧን ፈጣሪ ይባርክ!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*