በሥልጣን ከመገልገል ወደ ማገልገል! | ርእስ አንቀጽ

ኢትዮጵያ በየዘመኑ በስሟና በሕዝቧ እየማሉና እየተገዘቱ የመጡ ገዥዎች ቃላቸውን ማጠፋቸው፣ በሹመቱም ከማገልገል ይልቅ የራስን ምቾት ማደላደያ፤ ለሕዝብ ደግሞ መቅጫ መሳሪያ አድርገው ስለመጠቀማቸው ታሪክ ምስክር ነው። የቀደመውን አቆይተን፣ የግማሽ ክፍለ ዘመኑን ብንመለከተው እንኳ በሥልጣናቸው የተገለገሉ እንጂ፣ ያገለገሉት እምብዛም ናቸው።

‘መሬት ላራሹ’ን ቀዳሚ የትግል አጀንዳ ያደረገው የተማሪዎች ንቅናቄ፣ በሂደት ሌሎች ጥያቄዎችን በማስከተል የ1966ቱን አብዮት ሲያስከትል፤ የነገሥታቱ ‘መለኮታዊ’ የሥልጣን ቅብብል አብቅቶ፣ ‘በኢትዮጵያ በሕዝብ የተመረጠ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት ይፈጠራል’ የሚል እምነት ነበር። ይሁንና፣ አብዮቱን የጠለፈው ወታደራዊው ኃይል፣ በኢትዮጵያ የሥልጣን ምንጭ ሕዝብ ሳይሆን አፈሙዝ እንዲሆን አደረገ። ሥልጣን የሕዝብ ማገልገያ መሳሪያ ከመሆን ይልቅ፤ በፀረ-አብዮት ትግል ስም ንጹሃንን መፍጃ ሆነ። አንዳንዶች በአዳራሽ የሶሾሊስት ሰባኪ ሆነው፤ ሥልጣናቸውን የአየር ባ’የር ንግድ ለማጧጧፍ እንደተጠቀሙበት ታሪክም ትውልድም በትዝብት መዝግቦት አልፏል። ከ“ያ ትውልድ” የተሻገሩ የሕዝብ ጥያቄዎች ዛሬም ምላሽ ያለማግኘታቸው አንደኛው ጭብጥ፣ በኢትዮጵያ በሥልጣን ከማገልገል ይልቅ፤ የሚገለገሉት ሹማምንት መብዛታቸው ነው።

ድኀረ-ደርግ የተፈጠረው ሥርዐት ዜጎች በችሎታቸውና በብቃታቸው እንዲያገለግሉ ከማድረግ ይልቅ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ የብሔር-ተኮር የጥቅመኝነት ሥርዐት ተቋማዊ መሠረት እንዲይዝ አድርጓል። በዚህም በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ለሥልጣን ያለው አመለካከት እጅግ የተዛባ ሁኖ ቆይቷል። በአንድ በኩል በሕወሓት የበላይነት የተያዘው መዋቅር፤ በሌላ በኩል ደግሞ ብሔር የሥልጣን ምንጭ የመሆኑ እውነታ አድርባይነትንና የጥቅመኝነት ፖለቲካን አሳድጓል።

‘ሥርዐቱ እንጥሉ’ ድረስ እንደበሰበሰ በድርጅቱ ሊቀ- መንበር ሳይቀር እንዲነገር ያስገደደው፣ አመራሩ ኢትዮጵያን በሚያጎበጥ የዘረፋ ኔትዎርክ መዘፈቁ ነው። በተለይ ከ2002 ዓ.ም ወዲህ ኢሕአዴግ አውራ ፓርቲ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፣ የአስፈጻሚው ጥገኛ የሆነው ምክር ቤት፣ አስፈጻሚውን አካል መከታተልና መቆጣጠር ባለመቻሉ፣ የአገልጋይነት ስሜት ጠፍቶ ሥልጣን የሀብት ምንጭ ሲሆን ታይቷል።

ከኢሕአዴግ ውህደት በኋላ ስሙን ቀይሮ፣ በግብር ራሱን አክፍቶ የመጣው ብልጽግና ፓርቲም ከቀዳሚ ማንነቱ አብዝቶ የወረሰው ነገር ቢኖር፣ አመራሩ ለሥልጣን ያለው አተያይ ከአገልጋይነት ይልቅ፤ የመገልገል ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑ ነው። ምንም እንኳ የጠሉትን መምቻ በቀል-ተኮር የመሆን ተለምዷዊ አሠራሮች ቢኖሩትም፤ በዘመነ-ኢሕአዴግ የውስጠ-ፓርቲ ግምገማዎች ነበሩ። ትልልቁቹ አሳዎች ያለመጠመዳቸው እውነታ እንደተጠበቀ፤እነዚህ ግምገማዎች ቢያንስ ሙሉ መዋቅሩ ወደዘረፋና ስርቆት እንዳይገባ በማስፈራራትና በማጨናነቅ ዋጋ አልነበራቸውም ማለት አይቻልም።

ብልጽግና ከምስረታው በኋላ የቀጠለበት መንገድ፣ በተለይ የአመራር ምደባው፣ በሹመት የቀጠሉና ዐዳዲሶቹ፣ የሥራና የአሠራር፣ የተጠያቂነትና የውሳኔ አሰጣጥ ባህልና ሥርዐቱ ከቀዳሚው የሚከፋ እንጂ፣ የሚበጅ ሁኖ አይታይም። የግጭት አዙሪት ውስጥ የገባች አገር ውስጥ በመኖራችን ጋርዶብን ካልሆነ በቀር፤ አደገኛ የሆነ አመራር ተፈጥሯል።

ለሥልጣን የሚኖር አመለካከት፣ ከአገልጋይነት ይልቅ፤ የተረኝነት ስሜት እንዲላበስ የተደረገበት ሁኔታ አደጋውን አክፍቶት ታይቷል። ገና ከመነሻው ብልጽግና ውስጥ ቡድንተኝነት የተንሰራፋው ፓርቲው በውርስ ከያዛቸው ኢሕአዴጋዊ ባህሪያት በላይ፤ ሥልጣንን ከተረኝነት ጋር ያያዙ ኃይሎች በመኖራቸው ነው።

‹ተረኛ ነን በአገሩ ላይ እንወስንበት› ከሚል የፖለቲካ አተያይ የሚነሳው ይሄ ቡድን፣ ባለሀብቱ፣ ተቃዋሚው፣ ሹመኛው የራሱን ኢ-መደበኛ አደረጃጀት በማበጀት ተፅዕኖ የሚፈጥርበትን የፖለቲካ አውነታ ቀምሮ አገር ሲያምስ፣ ደም ሲያፈስ ከርሟል። በተለይ የሰሜኑ ጦርነት ከመቀስቀሱ ቀደም ብሎ ከ2011-2012 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ የነበረው እውነታ ይሄ ነው። ‘የጋራ አመራር’ እና ‘የጋራ የፖለቲካ ቋንቋ’ የሌለው ኃይል በየግል ፍላጎቱ በነጎደ ቁጥር፣ መንግሥታዊ መዋቅሩን ከተልዕኮ ውጭ ሲያሰማራው፣ አልፎም መዋቅሩን ሲንደው ታይቷል።

በሥልጣን ከማገልገል ይልቅ፣ ለመገልገል ፍላጎት እንዳለው ያሳየን እበላ ባዩ አመራር፣ ከአንድ ዘውግ ወጥቶም እርስ-በርስ የመናቆር ችግሮች በከፋ ሁኔታ ታይቶበታል። ይህም ሁኖ በሥልጣን ከመገልገል አኳያ የመርህ ፀብ የለውም። መመሪያው ‹ተረኛ ነን በአገሩ ላይ እንወስንበት› የሚል ሁኖ ታይቷል። ይሄ የጋራ አመራርም ሆነ የጋራ የፖለቲካ ቋንቋ የሌለው ኃይል፣ በየግል ፍላጎቱ የሚሮጥ በመሆኑ፤ በመሪነት በተሰየመባቸው ክልል፣ ከተማ አልያም የሚኒስቴር ተቋም ጥገኛ አመራሮችን በስሩ ሲሰበስብ ታይቷል።

አመራሩ የራሱን መንጋ ያደራጀ በመሆኑም፣ ‘የጋራ አመራር’ የለውም። በመብላት ዙሪያ እንጂ፣ በመሥራት ላይ ስምምነት ሲያሳይ አልተስተዋለም። በዚህ ሁሉ የአመራር ምስቅልቅል ውስጥ በዐቢይ አህመድ አመራር፣ ግምገማ የሚባል ፖለቲካዊ አሠራር የውሃ ሽታ መሆኑ፣ ባለሥልጣናቱን እንዳሻቸው የሚጋልቡ አድርጓቸዋል። የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄዎች የመዘንጋታቸው ሥረ- ምክንያቶችም ከዚህ ይመነጫሉ የሚል እምነት አለን።

በ“ፍትሕ መጽሔት” ግምገማ፣ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አለመታዘዝ (የዕዝ ጠገግን አለመጠበቅ)፣ ከባድ ሙስና፣ የኔትዎርክ ፖለቲካ፣ ጥገኛ አመራር፣ ሥራን በሚፈለገው ጊዜና ጥራት አለማድረስ፣ ተጠያቂነት አለመኖር… በሰፊው የሚታዩ ችግሮች ናቸው። በእነዚህና መሰል ችግሮች የተነሳ፣ ዛሬም በሥልጣን ከማገልገል ይልቅ፤ መገልገልን አብዝተው የሚያልሙ ሹመኞች ተበራክተዋል። ግማሽ ቀን ፖለቲካ፣ ግማሽ ቀን ቢዝነስ የሚለው ቀርቶ፤ የሙሉ ቀን ቢዝነስ የሚሠሩ ባለሥልጣናት መበራከታቸው ሁኔታዎችን ከድጡ ወደማጡ አድርጓቸዋል።

6ኛው አገር ዐቀፍ ምርጫን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያን በአውራ ፓርቲ የመመራት ታሪክ ያደሰው ብልጽግና. በክልሎች የመንግሥት ምሥረታ ለመተካካት ቦታ የሰጠ አይመስልም። ካድሬነት እየገነገነ በኔትዎርክ ፖለቲካ ባለበት መርገጥ፤ አልያም መገላበጥን አማራጭ አድርጎ እንዳቀረበ ታዝበናል።

ለግማሽ ክፍለ ዘመን የተሻገሩ የሕዝብ ጥያቄዎች ያልተመለሱባት፣ ከምንም በላይ በጦርነት ውስጥ የምትገኝ፣ የምዕራባውያን ጫና እና ከኤርትራ በቀር፤ ዙሪያዋን በእሳት ቀለበት ያለችውን ኢትዮጵያ ከተደቀነባት የህልውና አደጋ መንጥቆ የሚያወጣ አመራር በየደረጃው ማስቀመጥ ካልተቻለ፣ መጭው ጊዜ አሰፈሪ ነው። ሕዝባዊ ዐመጽ ተመልሶ ላለመምጣቱ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ስለዚህም ኢትዮጵያን ለማዳን ሹመኞቿ በሥልጣን ከመገልገል ወደማገልገል ሊቀየሩ ይገባል። ከምንም በላይ፣ ብልጽግና የሕግ የበላይነትንና ተጠያቂነት የማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት አለበት። ይህን ደግሞ በየደረጃው ካሉ ባለሥልጣናቱ ሊጀምር ይገባል!!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*