በትግራይ “ታሪክ ራሱን ይደግማል?!”

ትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ተራዛሚ ባህሪ በመያዙ፣ የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአገሪቱ ኢኮኖሚ ዋንኛ ተጎጂዎች ሆነዋል። ሕወሓት፣ ጦርነቱን የጀምረው በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ አቅዶ ቢሆንም፤ ውጤቱ የተገላቢጦሽ ሆኖ ከአሸናፊነት ቀቢፀ-ተስፋ ወደ ተሳዳጅነት እና ሽምቅ ተዋጊነት ተቀይሯል። የፌደራል መንግሥቱም ‘አፈንጋጩን ኃይል በፍጥነት አንበርክኬ አጀንዳውን እዘጋለሁ› ቢልም፤ ሂደቱ ከታሰበው በተቃራኒው እየሆነ ወደ መበለሻሸት እና ብሔራዊ ህልውናን ወደ መፈታተን አዘንብሏል። ይህ ደግሞ ያልተገመቱና ለመቋቋም ዝግጅት ያልተደረገባቸው ዐዳዲስ ችግሮችን ከማዋለዱ በዘለለ፤ የጉዳዩ ተሳታፊ “አክተሮች”ን አብዝቷል።

የችግሮቹ ዐይነቶችም በሚከተለው መንገድ በግርድፉ ሊጠቀሱ ይችላሉ፡- በፌደራል መንግሥቱ እና በሕወሓት ጦርነት ንፁሃን የትግራይ እና የዐማራ ሕዝብ የህይወት፣ የሰበዓዊ መበት ጥሰት እና የንብረት ውድመት ሰለባ ሆነዋል፤ ከሰሜን ዕዝ የተነጠቁ ቀላል የማይባሉ የጦር መሳሪያዎች ለጥፋት ተግባር እንዳይውሉ ከአገልግሎት ውጪ ተደርገዋል፤ ዘመቻውን ለማጠናቀቅ ከፍተኛ የሆነ መዋለ-ንዋይ እየወጣ ነው፤ ባልተለመደ መልኩ ሉዓላዊነትን እስከ መዳፈር የተለጠጠ ዓለም ዐቀፍ ጫና ተፈጥሯል።

ዋንኛው ጥያቄም፡- እነዚህ ችግሮች እንዴት እና መቼ ይፈታሉ? የሚለው በመሆኑ፣ ሁለት ነጥቦችን አስታውሰን እንለፍ።

የጦርነቱን አጀንዳ መዝጋት

የሰሜን ኢትዮጵያን ችግር ለመፍታት ብቸኛው መንገድ የጦርነቱን አጀንዳ መዝጋት በመሆኑ፤ ሁለት አማራጮችን እንጠቅሳለን።

የመጀመሪያው (የሚቻል ከሆነ) የሕወሓት የፖለቲካ እና ወታደራዊ አመራር አባላትን ከተደበቁበት አድኖ በማውጣት ለፍርድ ማቅረብ ነው። ይህ የማይሳካ ከሆነ ግን፣ ቡድኑ የአገሪቷ ችግር ሆኖ እንዳይቀጥል ማድረግ ግዴታ ነው። ለዚህ ደግሞ፣ መከላከያ እስከ አሁን የተደረጉትን ዘመቻዎች ጥንካሬና ድክመቶችን በጥልቀት ገምግሞ፣ ዐዲስ ስትራቴጂ መንደፍ ይኖርበታል።

በግምገማው ሊታለፍ የማይገባው ግዘፍ-የሚነሳ ነጥብ፣ የሕወሓት ኃይል ከመቀሌ እስኪባረር ድረስ የነበረው ዐይነት መደበኛ አደረጃጀት ዛሬ የሌለው መሆኑ ነው። ቡድኑ፣ ወደ በረሃ ከሸሸ በኋላ፣ የሠራዊቱን ቁማና አፍርሶ እንደገና ለሽምቅ ውጊያ በሚያመች መንገድ አደራጅቷል። ባለፈው አርብ ኮረም አካባቢ በነበረው የዐማራ ክልል ልዩ ኃይል (አንድ ሻለቃ እና ሁለት ሻምበሎች) ላይ ድንገተኛ ጥቃት በሰነዘረበት ወቅት አሰላለፉ እና የተጠቀማቸው የጦር መሳሪያዎችም በሽምቅ ውጊያ ስልት የሚበየኑ መሆናቸው፣ የቅያሪውን እውነታነት አስረግጠው አልፈዋል። ውጊያው ከቀኑ ስምንት ሰዓት እስከ ምሽት አራት ሰዓት የተካሄደ ሲሆን፤ በመጨረሻም ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የሕወሓት ኃይል ወደመጣበት ለመመለስ ተገድዷል። ይሁንና፣ እንዲህ ዐይነቱ ጥቃት የመከላከያ ሠራዊት እና የዐማራ ልዩ ኃይል በሳሱባቸው አካባቢዎች ወደፊትም ተስፋፍቶ መቀጠሉ አይቀሬ ነው። ዓላማው በአገሪቱ ሠላምና መረጋጋት እንዳይኖር ማድረግ፣ ስንቅና ትጥቅ መዝረፍ፣ የመንግሥት ተቋማትን ማውደም፣ ለዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎች ዜና የሚሆኑ ኦፕሬሽኖችን ማካሄድና የመሳሰሉት ናቸው።

ስለዚህም የመከላከያ ሠራዊት ይህን የተበታተነ እና በየገዳለ-ገደሉ የመሸገ ኃይል በተሳካ ሁኔታ ደምስሶ፣ የትግራይ ሕዝብን ከመከራ መታደግ የሚችለው፣ በፀረ- ሽምቅ ብርጌዶች ላይ በተመሰረተ ጥቃት እንጂ፤ ጠላት የቱ ጋ እንደመሸገ የማይታወቅባቸውን ተራራዎች በአየር ኃይል እና በታንክ በመደብደብ አይደለም። የወታደራዊ ሳይንስ አስተምህሮ እንደሚለውም፣ ‘ጉዳቱ የማይታወቅ ጥቃት ውጤታማ አይደርግም።’ የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ለሽንፈቱ አንዱ ምክንያት የጠላትን ቁመና ከግምት ያልከተተ አደረጃጀት እና የጦርነት ስልት መከተሉ እንደሆነ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋ ተያይዞ የሚነሳው ሌላው ጉዳይ፣ በአሁኑ ወቅት ከተለያዩ የትግራይ ከተሞች እየኮበለሉ ሕወሓትን የሚቀላቀሉ ወጣቶች ቁጥር መጨመሩንም ሆነ ጉዞው ቀላል የሆነበትን ስረ-ምክንያት አጣርቶ እርምጃ መውሰዱ ለነገ የማይተው የቤት ሥራ መሆኑ ነው። በተለይም ወጣቶች አላስፈላጊ መስዋትነት እንዳይከፍሉ ከተጠቂነት ስሜት የሚወጡበትን መንገድ ማበጀት ይገባል።

ሁለተኛው፣ የፌደራል መንግሥቱ ‘ሕግ የማስከበር ዘመቻውን በጦር ሠራዊት ለማጠናቀቅ ያዳግተኛል’ ብሎ ካመነ፤ ቀሪው መፍትሄ የፖለቲካ ውሳኔ መሆኑን መቀበል ነው። በርግጥም፣ ሁኔታዎች ወደ ጠረጴዛ የሚገፉ ከሆነ፣ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ታሳቢ ባደረገ መልኩ በድርድር ለመፍታት ተዘጋጅቶ መጠበቁ ይመከራል።

ሰበዓዊ ቀውሱን መግታት

በዚህ ጦርነት ከኢትዮጵያ ጎን የተሰለፈው የኤርትራ መንግሥት አጋር ከመሆኑ በፊት፣ ወገን እንደነበረ እና ኤርትራውያንም ለሀገረ-መንግሥቱ ግንባታ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ማድረጋቸው እውነት ነው። ይህን ይዘን ታዲያ፣ ‘ኤርትራ ራሷን የቻለች አገር ሆና ለመገንጠል እንዴት በቃች?’ ብለን ስንጠይቅ፣ ከምንላተማቸው ጥሬ ሃቆች አንዱ ‘የቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ አስተዳደር እና የደርግ ሥርዐት ከክፍል ሀገሩ የሚነሱ ጥያቄዎችን ያስተናገዱበት መንገድ ሆደ- ሰፊነት እና አቃፊነት ይጎድለው ነበር’ የሚል ይሆናል።

ዛሬም፣ በትግራይ ባለው የሰበዓዊ ቀውስ ምሬት ማኀበረሰቡ ኢትዮጵያዊነቱን ወደ ማጠየቅ ተገፍቶ፣ ታሪክ ራሱን እንዳይደገም አብዝቶ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በተለይ በአካባቢው የተፈጠሩት ችግሮች ከውስጥ ጉዳይነት ወደ ዓለም ዐቀፍ አጀንዳነት ከመቀየራቸው አኳያ፣ አደጋው ሊከፋ ይችላል። ስለዚህም፣ ለኢትዮጵያ ፍርሰት ያሰፈሰፉት አሜሪካንን የመሳሰሉ ዘራፊ አገራትም ሆኑ የ19ው እና የ20ኛው ክፍል ዘመን ስግብግብ ቀኝ-ገዢ አውሮፓውያን ክፍተቱን ተጠቅመው አገር አልባ ከማድረጋቸው በፊት፤ ሕወሓትን ማጥፋት (ማምከን) እና ተጋሩን ከጥቃት መከላከል ላይ ያተኮረ አፋጣኝ መፍትሄ ብቸኛው አመራጭ እንደሆነ “ፍትሕ መጽሔት” ታሳስባለች።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*