ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለብስለትና ስክነታቸው ይመሰገናሉ!

ስድስተኛው አገር ዐቀፉ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መጠናቀቁ ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ መሆኑ እንደተጠበቀ፤ ከድምጽ አሰጣጡ ጋር ተያይዘው የተነሱ ችግሮችም በአግባቡ ተጣርተው መፍትሄ ሊያገኙ እንደሚገባ ምርጫ ቦርድ ይዘነጋዋል ተብሎ አይታሰብም።

በዕለተ ሰኞ ሰኔ 14/2013 ዓ.ም የ“ፍትሕ መጽሔት” ዘጋቢዎች ከማለዳ ጀምሮ በአዲስ አበባ የተለያዩ ምርጫ ጣቢያዎች ተዟዙረው ባደረጉት ቅኝት፣ ምንም እንኳ በውጤቱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጡ ባይሆንም፤ የተለያዩ ችግሮች ሲፈጠሩ እንደበረ ታዝበዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዋንኞቹ፡- ዘግይተው የተከፈቱ የምርጫ ጣቢያዎች መኖራቸው፣ ከመራጩ ቁጥር ጋር ያልተመጣጠነ ምርጫ አስፈጻሚ በመመደብ መራጮች ለተራዘመ ሰዓት ዝናብ እና ፀሀይ እንዲፈራረቅባቸው መደረጉ፣ (አንዳንድ ቦታ ደግሞ የማይመርጡ እና የመረጡ ሰዎች ሰልፉን በመቀላቀል ሆን ብለው እንዲራዘም ስለማድረጋቸው ለዝግጅት ክፍሉ ጥቆማዎች መድረሱን ልብ ይሏል)፣ የተወሰኑ ጣቢያዎች በተለይ “አረጋውያንን ለመርዳት” በሚል ሰበብ የምስጢር ክፍል ውስጥ አብረው የሚገቡ ሰዎች እንደነበሩ በመስክ ቅኝታችን ታዝበናል፣ ዘጋቢዎቻችን በሄዱባቸው አብዛኛው ጣቢያዎች የምርጫ ካርድ የጠፋባቸው ሰዎች በምርጫ አስፈጻሚዎች የተለያየ ሰበብ እየተሰጣቸው እንዳይመርጡ ሲደርጉ ተመልክተዋል፣ የብልፅግና ፓርቲ ተወዳዳሪዎች ከምርጫ ጣቢያዎች እንዲርቁ ሕጉ ከሚያስገድደው ኪሎ ሜትር ባነሰ ርቀት ላይ ሆነው አንዳንድ መራጮችን (በምን ጉዳይ እንደሆነ በርግጠኝነት መናገር ባይቻልም) ሲያነጋግሩ ተስተውሏል፣ በታዛቢዎች እና በምርጫ አስፈጻሚዎች መሀል ተደጋጋሚ ጭቅጭቅ እየተነሳ የምርጫ ሂደቱ ሲስተጓጎል ታዝበናል…።

በሌላ በኩል፣ በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ‘በምርጫው ላይ የታዩ የገዥው ፓርቲ ግድፎቶች’ ያሏቸውን ችግሮች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዘርዝረው ከማቅረባቸው በዘለለ፤ ለምርጫ ቦርድ አመልክተዋል። ለምሳሌ ኢዜማ ከመደባቸው የራሱ ታዛቢዎች እና እጩዎች የደረሱትን 461 ቅሬታዎች አደራጅቶ ለቦርዱ ማቅረቡን ይፋ አድርጓል። እናት ፓርቲም በደቡብ ክልል፡- ሆሳና እና አርባ ምንጭ፤ በዐማራ ክልል፡- ምንጃር፣ ሞረት ጅሩ፣ ትክል ድንጋይ፣ ፋርጣ፣ አፈንቅር፣ ፍኖተ ሰላም፣ ወልዲያ እና ዋድላ ደላንታ፤ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ችግሮች እንደገጠሙት፤ እንዲሁም በአዲስ አበባ፡- በአቃቂ እና ንፋስ ስልክ ክፍል ከተሞች ሁለት ታዛቢዎቹ ታስረው እንደተለቀቁ አስታውቋል። ህብር ኢትዮጵያ ደግሞ በደቡብ ክልል አንድ ታዛቢው እንደተገደለበት ተናግሯል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የዚያኑ ቀን ጠዋት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱካን ሚዲቅሳ በገዥው ፓርቲ አባላት አንዳንድ ችግሮች እየተከሰቱ እንደሆነ ጠቀሰው፣ ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ይህም ሆኖ፣ 6ኛው ዙር አገር ዐቀፉ ምርጫ በጥቅሉ ከእነ ችግሮቹ የተሻለ ስለመሆኑ እጩዎችን አቅርበው የተሳተፉ ፓርቲዎች መመስከራቸው፣ ለመጪው ጊዜ የሰናፍጭ ቅንጣት የምታህልም ቢሆን ተስፋ የሚሰጥ ተደርጎ እንዲወሰድ ገፊ-ምክንያት መሆኑ አይቀርም። በተለይ ምርጫ ቦርድን እንደ ዐዲስ በማቋቋም የተካሄደ ምርጫ ከመሆኑ አኳያ፣ ተቋሙ ከስህተቱ እየተማረ፣ ክፍተቶቹን እየደፈነ፣ ድክመቶቹን እያስተካከለ ከሄደ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ አገሪቱ እና ሕዝቧ ለዘመናት የቃተቱበትን ዴሞክራሲያዊ እና ታአማኒ ምርጫ የማካሄድ ዐቅም እውን ለማድረግ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው ማለት ያስደፍራል።

በዚህ አጋጣሚ “ፍትሕ መጽሔት” ወደ ማተሚያ ቤት እስክትገባ ድረስ በምርጫ ቦርድ የተሰጠ ይፋዊ ሪፖርት ባይኖርም፤ በተለያየ መንገድ በምርጫው ውጤት እንዳላገኙ የተነገረባቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ከድምጽ መስጫው ቀን ጀምሮ የተከሰቱ ችግሮች ተካረውና ውጥረት ፈጥረው አገር እንዳያተራምሱ ያሳዩት ጨዋነት እና ሥልጣኔ በእጅጉ የሚያስመሰግናቸው እንደሆነ ሳትጠቅስ አታልፍም። በማንኛውም መስፈርት አገር ከፓርቲም ሆነ ግለሰብ ሥልጣን በላይ እንደሆነ ያሳዩበት ታላቅነት ነውና ደግመን እናመሰግናቸዋለን። ከዚህ ዐይነቱ ስክነት እና ብስለት የተሞላበት አካሄድም ገዥው ፓርቲ ብልፅግና፣ ትምህርት ሊወስድ እንደሚችል ይታመናል።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*