ተጠያቂነት በተግባር!

“ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን” እና በ“ሰሜን ሸዋ ዞን” አጎራባች ወረዳዎች ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የተጠኑ ትንኮሳዎችንና ጥቃቶችን መነሻ ያደረጉ አምስት ግጭቶች ተፈጥረዋል። ከተደጋጋሚ ሪፖርቶች መረዳት እንደሚቻለው የአጥቂዎቹ መነሻ ከልዩ ዞኑ ከመሆኑ በዘለለ፤ በመዋቅር የሚደገፍ እና ሃይማኖትን ከብሔር ማንነት ጋር የለነቀጠ ነው።

በተለይ፣ በያዝነው ዐመት መጋቢትና ሚያዚያ ወር በተከታታይ የተከሰቱት ሁለቱ ጥቃቶች፣ በአካባቢው በሚገኙ ዜጎች የህይወትና ንብረት ውድመትን ከማስከተላቸውም በላይ፤ የዐማራ ክልልን የጸጥታ ኃይል፣ በከፍተኛ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ በማስገባት፣ ቀላል የማይባል ዋጋ አስከፍለዋል። የሚያዚያውን ግጭት ለማሳያ ብንወስደው እንኳ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ህይወታቸው ሲያልፍ፤ 205 ሺሕ ዜጎችን ደግሞ የአገር ውስጥ ተፈናቃይ አድርጓል። በሰሜን ሸዋ ዞን ስር የሚገኙ አራት ከተሞችም ከባድ ውድመት ደርሶባቸዋል። ይህ ሁሉ ጥፋት ሲደርስ አንድም አመራር በሕግ ቁጥጥር ስር አልዋለም። ለጉዳዩ መፍትሔ የተባለውም፣ አካባቢውን ከክልሉ አስተዳደር የሚነጥል ኮማንድ ፖስት ማቋቋም ነው።

ይኼው ኮማንድ ፖስት፣ በሳምንቱ አጋማሽ “ባለድርሻ” ከተባሉ አካላት ጋር በሸዋ-ሮቢት ከተማ ስብሰባ አድርጎ ነበር። የስብሰባው መሪ የኮማንድ ፖስቱ ኃላፊ ሌ/ ጀኔራል ደስታ አብቼ ሲሆኑ፤ ጀኔራሉ በስብሰባው ላይ ‹‹ቀጣናው እንዳይረጋጋ ህብረተሰቡን የማሸበር ሥራ የሚሠሩ አመራሮች አሉ […] ዋነኛ ጥፋተኛ ራሱ አመራሩ ነው፤›› ሲሉ፣ ችግሩ ከመዋቅሩ ጋር የተገናኘ ስለመሆኑ አስረግጠው ተናግረዋል። ‹‹ጠብ-አጫሪነት፣ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ፣ የሥነ-ልቦና ጦርነት ማድረግ አልቆመም›› ያሉት ጀኔራል ደስታ፤ ሁኔታውን ያወሳሰበው፣ አመራሩ ራሱ ጉዳዩ ውስጥ ስላለበት፣ ራሱን ከተጠያቂነት ለመደበቅ የሚፈጥረው ችግር እንደሆነ አስረድተዋል።

እዚህ ጋ የሚነሱት መሰረታዊው ጥያቄዎች፡- ‹የትኛው አመራር?› እና ‹የግንኙነቱ ሰንሰለትስ የት ድረስ ነው?› የሚሉት ናቸው።

በሰሜን ሸዋ ዞን፡- አጣዬ፣ ሸዋ-ሮቢት፣ ማጀቴ፣ ካራ- ቆሬ፣ አለላን… በመሳሰሉ ከተሞች የጅምላ ግድያና ቁሳዊ ሃብቶችን በማውደም፣ ከተማዎቹን የማጥፋ ተግባራት ሲፈጸሙ፣ በሎጀስቲክስና በፕሮፓጋንዳ ድጋፍ ያደረጉ በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እንዳሉበት፣ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምስክሮች ይናገራሉ።

ለበርካቶች ሞትና መፈናቀል ምክንያት በሆነው የመጋቢት 2011 ዓ.ም ጥቃትና ግጭት፣ በጊዜው የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን አመራር ከነበሩት በርካቶች በሕግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ቢደረግም፤ የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊ በነበሩት ብርሃኑ ፀጋዬ ትዕዛዝ መለቀቃቸው ይታወሳል።

“ፍትሕ መጽሔት” መሠረታዊ የችግሩን ቋጠሮ እዚህ ላይ መፈለግ ተገቢ ነው ብላ ታምናለች። ለበርካታ ንፁሃን እልቂትና ንብረት ውድመት የተጠረጠሩት አመራሮች፣ ተረኝነት በተጫነው የፖለቲካ ውሳኔ መለቀቃቸው፣ ዛሬ ድረስ ለቀጠለው ሰብዓዊ እልቂት ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። አደጋውን ያበዛው ደግሞ፣ ተጠርጣሪዎቹ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ወደ አመራርነት ቦታቸው መመለሳቸው ነው። ሌ/ጀኔራል ደስታ አብቼም፣ ‹‹ዋነኛ ጥፋተኛ ራሱ አመራሩ ነው›› ሲሉ የተናገሩት ሃቅ፣ ከልዩ ዞኑ አልፎ ወደ ፌዴራሉ የሚሳብ ሊሆን እንደሚችል ምልክቶች ታይተዋል።

ችግሩን በመሠረታዊነት በሁለት መልኩ መመልከቱ ተገቢ ነው።

የፖለቲካ አመራሩ ሁኔታ

በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ከላይኛው እስከ ታችኛው የቀበሌ አመራር ድረስ ያለው አደረጃጃት፣ በዐማራ ክልል አስተዳደር ሥር በተዋረድ የሚመራ መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና፣ ከ2010ሩ “ለውጥ” ወዲህ ከአመራሩ የሚበዛው የኦነግን አስተሳሰብ የሚያቀነቅንና ለተግባራዊነቱ የ“ሚታገል” እንደሆነ ድርጊቶቹ በበቂ አጋልጠውታል።

ቀውስን ለሚያቀጣጥሉት የልዩ ዞኑ አመራሮች፣ ፖለቲካዊ ድጋፍ የሚያደርጉ ስለመኖራቸውም የመጋቢት 2013 ዓ.ም ግጭት ሰሞን፣ የኦሮሚያ ብልጽግና ቅ/ጽ/ቤት ያወጣው መግለጫ ይዘት እና የኦ.ቢ.ኤን ቴሌቭዥን ተደጋጋሚ ፕሮፓጋንዳዎች በአስረጅነት ይጠቀሳሉ።

በሌላ በኩል፣ የልዩ ዞኑ አመራሮች ሃይማኖታዊ ተቋማትን ፖለቲካዊ ቅርፅ ለማስያዝ የተጓዙበት ርቀት፣ ሁኔታዎችን ይበልጥ በማወሳሰብ አደጋውን አክፍቶታል። የሃይማኖት ተቋማት የሠራዊት መሰባሰብያና የጦር ማዛዣ ጣብያ እንዲሆኑ ስለመደረጉ የሾለኩ መረጃዎች ያስረግጣሉ። የጥፋት ተልኮዎችን ከሚያስፈጽሙባቸው አደረጃጀቶች ውስጥም የወጣቶች አደረጃጀት አንዱ ሲሆን፤ ይህን ስያሜ በሽፋንነት በመጠቀም ዓላማቸውን በቀላሉ እያስፈጸሙ ነው። የተጠቀሱት አደረጃጀቶች ጠንካራ ሆነው የየራሳቸውን ሚና በመጫወት፣ የተስፋፊነት ትልም ላለው ለጽንፈኛው የኦሮሞ ብሔርተኛ የፖለቲካ መስመር እንዲያመቹ፣ በልዩ ዞኑ አስተዳደር የተለያዩ ድጋፎችና ስልጠናዎች ይሰጣቸዋል።

የታጠቀው ኃይል ሁኔታ

የ“ፍትሕ መጽሔት” ምንጮች እንደሚጠቁሙት፣ በቀጠናው ሁለት ዐይነት አደረጃጀት ያለው ወታደራዊ ክንፍ ተፈጥሯል። አንደኛው፣ በልዩ ዞኑ እና በአጎራባች ክልል የሚያወስኑ ነፃ-መሬቶችን በመጠቀም፣ የተለያዩ ወታደራዊ ልምምዶችንና ምልመላ በማድረግ፣ ተልዕኮ በሚሰጥበት ወቅት ደግሞ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ጥፋቶችን የሚፈጽም ነው። ሁለተኛው፣ በመንግሥት በተለያዩ የጸጥታ አደረጃጀቶች ውስጥ በመታቀፍና መዋቅሩን በሽፋንነት በመጠቀም ለእኩይ ዓላማው የተሰለፈና የመንግሥትን ትጥቅ የታጠቀ ነው። ይህ ቡድን፣ ነፃ-መሬቶችን በመቆጣጠር የተለያዩ ጥፋቶችን እየፈጸመ ከሚገኘው ወታደራዊ ክንፍ ጋር መረጃ በመለዋወጥ፣ በሎጂስቲክ በመደጋገፍና የተናበበ ተልዕኮ በመያዝ በቅንጅት የሚሠራ ነው።

በአጠቃላይ በኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን መዋቅር ላይ ቁልፍ ቦታ የያዙ የፖለቲካ አመራሮች፣ ከኢ- መደበኛ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው፣ የሕዝብን ሠላምና ደህንነት የመጠበቅ ተልዕኮ የወሰዱ የጸጥታ ኃይሎችን የሚያጠቁበት መንገድ፣ አገር የማፍረስ ዓላማ እንዳለው የእስካሁኑ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ያስረዳል።

በዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግር ላይ በአከባቢው ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር እያደገ መምጣቱ ሲስተዋል፤ ቀጣናው የሃይማኖት እና ብሔር-ተኮር ውጥረት የነገሠበት በመሆኑ፣ ችግሩን በፍጥነት ከምንጩ ማድረቅ ከማይታረም ስህተት ይታደጋል። የአጭር ጊዜ የችግሩ መሻገሪያ መንገድም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በወንጀል ሊጠየቁ የሚገባቸው የልዩ ዞኑ ዋና አመራሮች እና በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ሲተባበሯቸው የነበሩ ከፍተኛ አመራሮችን ለሕግ ማቅረብ እንደሆነ፣ “ፍትሕ መጽሔት” በአጽኗት ታሳስባለች።

የእርሻ ወራት ከመቃረቡ ጋር በተያያዘም፣ አርሶ ዐደሮች በነፃነት ወደ ግብርና ሥራቸው እንዲያተኩሩ፣ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ለማድረግና እምባቸውን በፍትሕ ለማበስ፡- ቅድሚያ ተጠያቂነት በተግባር! የዕለቱ መልዕክታችን ነው።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*