
በዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ታሪክ፣ ዜጎችን እንደወጡ የሚያስቀር እንዲህ ዐይነቱ ክፉ ቀን ገጥሞ ስለማወቁ፣ የድርሳናቱ ምስክርነት የለም። አገሪቱ የቱንም ያህል አያሌ መከራዎችን ብታሳለፍም፣ ህላዊነቷን የሚፈታተኑ አደጋዎችን ብትጋፈጠም፣ በዚህ ደረጃ ተዳክማ የታየችበት ዘመን እምብዛም ነው። የዜጎች ደህንነት እና የአገር አንድነት በአንድ ተቋጥሮ፣ በዛሬው ልክ ወደ ገደል የተገፋበት ክስተት ስለመኖሩም አልተሰማም። በአጠቃላይ ከውስጥም ከውጪም፣ ከገዢዎችም ከተቃዋሚዎችም፣ ከቡድኖችም ከግለሰቦችም፣ ከመንፈሳዊውም ከዓለማዊውም… ለግባተ-መሬቷ እንዲህ በወል የተረባረቡበት ጊዜ አልነበረም።
ርግጥ ነው፣ ኢትዮጵያ ለጦርነት ዐዲስ አይደለችም። በተለያየ ጊዜ መንግሥት መቀየሩን ተገን አድርገው ዳር ድንበርን ለመዳፈር የሞከሩ የውጭ ጠላቶች ተደጋጋሚ ጊዜ ግልጽ ጦርነት ማወጃቸውም ሆነ ሠራዊት ማዝመታቸው መሬት የረገጠ ሃቅ ነውና። የተከፈለው ዋጋ ውድ ቢሆንም፣ እንደ አመጣጣቸው በጀብዱ እየፎከሩ ሳይሆን፤ በአሰቃቂ ሽንፈት አንገታቸውን ደፍተው ወደመጡበት መመለሳቸውም ጥሬ ሃቅ ነው። ለማስረጃ፣ ከጣሊያን እስከ ግብፅ ህያው መስክሮችን መዘርዘር ይቻላል። የድሉ ምስጢር ደግሞ፣ ወታደራዊው ሳይንስ እንደሚያስረግጠው፣ ‹ጠላትን አስቀድሞ ማወቅ፣ የመከላከሉን መንገድ የቀለለ ስለሚያደርገው ነው።
የዛሬይቷ ኢትዮጵያ፣ ከእነዚህ የተለዩ ሁለት አጋጣሚዎች ፊት ቆማለች። የመጀመሪያው እያገዛት ያለው “ወዳጅ”፤ ወይም እያስጠቃት ያለው “ጠላት” የትኛው እንደሆነ ተለይቶ አለመታወቁ ነው። ሁለተኛው፣ የራሱ የመንግሥት መዋቅር፣ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ተሳትፎ ለሌላቸው ተርታ ዜጎችም የደህንነት ስጋት መሆኑ ነው። በተለይ ከ2010 ዓ.ም ለውጥ በኋላ የፌደራል መንግሥቱ ሰላማዊ ዜጎችን ከታጣቂዎችም ሆነ ከደቦ ፍርድ የመከላከል ግዴታውን ለመወጣት፣ በአንዳንድ ቦታ ዐቅመ ቢስ ሲሆን፤ በአንዳንድ ቦታ ደግሞ ፍላጎቱ የለውም። የክልል አስተዳደሮችም የወንጀለኞቹ ዋንኛ ተባባሪ እና ጉዳይ ፈፃሚ ሆነዋል። ይህ ኹነት፣ በዋናነት በኦሮሚያ፣ በትግራይ እና በቤንሻንጉል ከፍቶ ታይቷል። የሰሞነኛው የአማሮ ጥቃት እና በሲዳማ ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ ሙሉ በሙሉ የከሰመው የንፁሃን ጥቃት ሳይዘነጋ ማለት ነው።
ሦስቱ ክልሎች ዛሬም “ሕዝባዊ መቃብር” እንደሆኑ መቀጠላቸው እንደተጠበቀ፤ የቤንሻንጉሉ የሞት መጠን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመቀነስ ምልክቶችን ሲያሳይ፤ ሁለቱ ክልሎች ግን በሞት ቀጠናነታቸው እንደፀኑ ነው። ልዩነቱ፣ የትግራዩ በግልፅ በመንግሥት እና በቀድሞ የክልሉ ገዥ ፓርቲ መሀል በታወጀ ጦርነት የተነሳ ሲሆን፤ የኦሮሚያው ዐማጺያኑን እና መንግሥታዊ መዋቅሩን መደገፉ ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ የቁጥር ልዩነት ካልሆነ በቀር፣ የአብዛኛው ብሔር ተወላጅ በህይወቱ፣ በአካሉ እና በንብረቱ ዋጋ ከፍሏል። እየከፈለም ነው። በተለይ እርሳቸው በሚወክሉት ብሔር በሚተዳደረው ኦሮሚያ የጅምላ ፍጅቱ ንሯል። ከመዲናይቱ አዲስ አበባ ከምትጎራበተው ቡራዩ እስከ ሶማሊያ ተጎራባቿ ባሌ፣ ከወለጋ እስከ ቦረና… በማንነታቸው ተመርጠው የተገደሉ ዜጎች ደም ያልፈሰሰበትን መሬት ማግኘት ይቸግራል።
ሁኔታውን የከፋ ያደረገው ጭፍጨፋውም ሆነ ንብረት ማወደሙ እና ማፈናቀሉ፣ መላው የአገሪቱ ሕዝብ በኢኮኖሚ ድቀት እና በዋጋ ንረት እየተሰቃየ ባለበት ወቅት መሆኑ ነው።
ይህም ሆኖ፣ ምንም እንኳ በእልቂቶቹ ልባችን ቢሰበርም፣ ‹መንግሥት ችግሩን ይቆጣጠረዋል› በሚል ሆደ ሰፊነት ሦስት ዐመት ለሚጠጋ ጊዜ በበዛ ትዕግስት ብንጠብቅም፣ ነገሩ “ከድጡ ወደ ማጡ” እየተዘናበለ ነው። የዜጎች ሰቅጣጭ ሞት ቀዳሚ ዜናዎች ከመሆን አልቦዘኑም። በሠላሳ ስድስት ወራት ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረት ወድሟል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ተፈናቅለዋል፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ለአሰቃቂ ሞት ተዳርገዋል።
ይህ ሁሉ የሆነው ‹በጦር ሠራዊቱ፣ በደህንነቱ እና በፌደራል ፖሊስ ላይ የተሳካ ሪፎርም ተደርጓል› እየተባለ በሚደሰኮርበት አገር ነው። በየክልሉ ከፖሊስ በተጨማሪ፤ ዓላማው የማይታወቅ ልዩ ኃይል በገፍ ሰልጥኖ በታጠቀበት አገር ነው። እናም፣ ደግመን ደጋግመን እንጠይቃለን፣ ይህ ዐይነቱ እልቂት እስከ መቼ ይቀጥላል? የዜጎች ደህንነትን መጠበቅ ስንት ቀን ይፈጃል? አገሪቱ ቅድሚያ መስጠት ያለባትስ ለሚጭበረበር ምርጫ ወይስ ለዜጎች ደህንነት?
በመጨረሻም፣ የፌደራል መንግሥቱም ሆነ የክልል መንግሥታት በራስ-ገዝ አስተዳደራቸው ውስጥ ለሚደርሱ የንፁሃን ጭፍጨፋ በይፋ ኃላፊነት ሊወስዱ ይገባል። እንዲህ ዐይነቱ እርምጃ ለዶ/ር ዐቢይ መንግሥት ዐዲስ እንዳልሆነም ይታወቃል። ከዚህ ቀደም በሶማሌ ክልል ለደረሰው ጥቃት የክልሉ አስተዳዳሪ አብዲ መሐመድ ኡመር ተጠያቂ ተደርጓል። ለቅርቡ፣ የቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን እልቂትም የዞኑ አስተዳደሪን ጨምሮ፣ በተለያየ የኃላፊነት እርከን ላይ ያሉ ግበረ-አበሮች በቁጥጥር ስር ውለዋል። እናም በተለይ፣ በወለጋ እየደረሰ ላለው እልቂት ከላይኛው እስከ ታችኛው አመራር ድረስ እጃቸው ያለበትን እና ኃላፊነታቸውን በመወጣት ዜጎችን ከጥቃት መከላከል ያልቻሉ የአመራር አባላት ሕግ ፊት ሊቀርቡ ይገባል።
ይሄ እስካልሆነ ድረስ፣ ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎሽ ዋንኛው ተጠያቂ የት እንዳሉ የማይታወቁት ታጣቂዎች ሳይሆኑ፤ የት እንዳሉ የምናውቃቸው ግብር ሰብሳቢዎቹ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት መሆናቸው ርግጥ ነው።
Be the first to comment