ኢትዮጵያን የማፍረስ ዘመቻ!

ወሓት፣ በማዕከላዊ መንግሥቱ ከነበረው የበላይነት በሕዝባዊ ተቃውሞ ከተገፈተረ በኋላ፣ የአገሪቱ ህልውና ወደ ፍርሰት ጫፍ የመገፋት ምልክቶች ይበልጥ ጎልተው መታየት ጀምረዋል። ኹነቱን የከፋ ያደረገው ደግሞ፣ የአደጋው መነሾ በጠላትነት ከሚፈረጁ ኃይሎች ወይም አገራት ብቻ አለመሆኑ ነው። የመንግሥትን ሥልጣን የተቆጣጠረው ገዢው ፓርቲም በዚህ መንገድ መመላለስ ማብዛቱ ተለምዷዊ እየሆነ ነው። በተለይ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ የሆኑት የኦሮሚያ ብልፅግና እና የዐማራ ብልፅግና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየፈጠሩት ያለው የአደባባይ አተካራ ዋንኛ ማሳያ ነው። ሁለቱ ቡድኖች የትኛውም ዐይነት ጥያቄ እና የሥልጣን መተጋገል ቢኖራቸው እንኳ፣ ልዩነታቸውን ማስተናገድ የሚችሉበት “ብልፅግና” የተሰኘ መድረክ (platform) አላቸው። አየሄዱበት ያለው መንገድ ግን ነፍጥ አንስተው የሚዋጉ ቡድኖች ዐይነት ወደመሆን እዘምሟል። ይህም፣ አጀንዳው ከእነሱ አልፎ በተንሸዋረረ እና ስሁት ትርክት አላስፈላጊ ፍጥጫ ውስጥ እንዲገቡ ወደተገፉት ሁለቱ ማኀበረሰቦች እንዲሸጋገር እያደረገው ነው።

ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ ዞን ስር በሚገኘው የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተደደር ውስጥ የተፈጠረውን ችግር ተንተርሶ፣ ከፓርቲዎቹ መግለጫ እስከ ፓርላማው የተራዘመው ፈር-የሳተ መወነጃጀል ተጠቃሽ ነው። በተለይ ደግሞ፣ ከፌደራል መንግሥቱም ሆነ ግጭቱ ያለበትን አካባቢ ከሚያስተዳድረው የዐማራ ክልል በፊት፣ የራሱን ድርጅት ቅርንጫፍ ፓርቲ የሚወንጀል መግለጫ ያወጣው የኦሮሚያ ብልፅግና ችግሩን በማባበሱ ረገድ የቀዳሚነቱን ሚና ይይዛል። ለዚህም ሁለት ማሳያዎች አሉ። የመጀመሪያው፣ የተፈጠረው ግጭት በአርሶ ዐደር ወይም በሰላማዊ ሰዎች እና በዐማራ ክልል ልዩ ኃይል መሀል እንዳልሆነ የሁለቱም ክልል አስተዳዳሪዎች በቂ መረጃ ያላቸው መሆኑ ነው። ችግሩ ‘የመረጃ እጥረት ነው’ ቢባል እንኳ፣ ከደህንነት መዋቅሮች የተገኙ መረጃዎች እንደተጠበቁ፤ የኃይል አሰላለፉ እና በግጭቱ የተከሰቱ ወታደራዊ ኹነቶች በራሳቸው እውነታውን ያስረግጣሉ። መቼም በየትኛውም መስፈርት የአንዲት መንደር አርሶ ዐደር የቱንም ዐይነት መሳሪያ ቢታጠቅ ከመከላከያ፣ ከፌደራል ፖሊስ እና ከዐማራ ክልል ልዩ ኃይል የተወጣጣ የፀጥታ አስከባሪን ተቋቁሞ (የበላይነትን ወስዶ) መዋጋት የሚችልበት ዕድሉ ከክር የቀጠነ መሆኑ መሬት የረገጠ ሃቅ ነው። በዚህ ላይ የተቆጣ አርሶ ዐደር ጥቃት ከሰነዘረ እንኳ፣ የሚያጠቃው ለቁጣው ምክንያት የሆነውን እንጂ፤ ባንኮችን በመዘርፍ፣ መኖሪያ ቤቶችን እያቀጠለ ፎቶ በመነሳት፣ በኦነግ-ሸኔ አጀንዳ እየፎከረ… ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። በአጣዬ እና በሸዋ ሮቢት የታየው ግን ይህ ነው።

ተዋጊዎቹ የያዙት መሳሪያም በአርሶ ዐደር እጅ ቀርቶ፤ ለክልል ልዩ ኃይሎች እንኳ የተፈቀደ እንዳልሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም።

ሁለተኛው የኦሮሚያ ብልፅግና መሰረታዊ ስህተት፣ በመግለጫው ላይ እንዳሠፈረው ‘የችግሩ ፈጣሪ የዐማራ ክልል ልዩ ኃይል ነው’ ብሎ ቢያምን እንኳ፤ ሁለቱ ክልሎች የብልፅግና ቅርንጫፍ ፓርቲ በመሆናቸው፣ ጉዳዩን በድርጅታዊ መዋቅር እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ፤ ሕዝብ ለሕዝብ የሚያጋጭ፣ ገዥው ፓርቲን ለሁለት እንደተሰነጠቀና መንግሥት እንደፈረሰ የሚያስመስል አካሄድን መምረጡ ነው።

በነገራችን ላይ፣ ይህ ግጭት ከሁለት ዐመት በኋላ ያገረሸው፣ የዞኑን ፀጥታ ይጠብቅ ከነበረው ልዩ ኃይል ውስጥ የሚበዛው፣ ከትግራይ ወደሚያዋስኑና ጦርነት ወዳለበት የክልሉ አካባቢዎች ከሄደ 48 ሰዓት በኋላ ነው። ይህም ከግጭቱ ጀርባ፣ በመንግሥታዊው መዋቅር ውስጥ የሠረጉ የአፍራሽ ቡድኑ መረጃ አቀባዮች መኖራቸውን ይጠቁማል።

ሌላው ጉዳይ፣ ሁለቱ የፓርላማ አባላት፣ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ያዘጋጁትን ጥያቄዎች አስቀድመው ለቋሚው ኮሚቴ አቀርበው ከታየ በኋላ፣ በአፈ-ጉባኤው በኩል ጠቅላዩ መልስ ይዘው እንዲመጡ ከተሰጣቸው ጥያቄዎች የተለየ መሆኑ ነው። አካሄዱን አስገራሚ ያደረገው ደግሞ የፓርላማ አባላቱ፣ ከምክር ቤቱ የአሠራር መመሪያ ሲያፈነግጡ፣ አፈ-ጉባኤው ለይስሙላ እንኳ አካሄዳቸው ሕገ-ወጥ እንደሆነ ጠቅሰው እንዲህ ዐይነቱ ነገር ዳግም እንዳይከሰት ለመገሰጽና ለማስጠንቀቅ አለመፈለጋቸው ነው።

ጠቅላይ ሚንስትሩም፣ ሰሞነኛው ግጭት በኦነግ ሸኔ እና በመንግሥት መካከል መሆኑን እያወቁ፤ ‘በሰላማዊ ሕዝብ ላይ ብሔርን እና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት ነው’ ተብሎ የቀረበበትን ዐውድ፣ በማስተባበል ለማረም አለመፈለጋቸው ብዙዎችን አስደንግጧል።

የሆነ ሆኖ፣ ሁሉም በመንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ የታቀፉ (ጠቅላይ ሚንስትሩ፣ የፓርላማ አባላቱ፣ የኦሮሚያ ብልፅግና እና የዐማራ ብልፅግና…) አገራዊ እና ሕዝባዊ ኃላፊነታቸውን ወደጎን ብለው፣ ለርካሽ ፖለቲካ እና ለተናጠል የዘውግ ጥቅም ብሔራዊ ደህንነትን እና የሕዝብን አንድነት አደጋ ላይ በሚጥል ተግባር ከመሳተፍ የመቆጠብ ግዴታ እንዳለባቸው እንዳይዘነጉ ይመከራል። በተለይ፣ በአሁኑ ወቅት አገሪቱ ግዘፍ- የሚነሳ የፀጥታ ችግር ያለባት ከመሆኑ አኳያ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ የማድረጉ አስፈላጊነት ለክርክር የሚቀርብ አይደለም።

በጥቅሉ፣ የሁለቱ ብሔር “ተወካዮች” ራሳቸው የመሰረቱት የሚነጋገሩበት፣ የሚከራከሩበት፣ ተደራድረው የሚስማሙበት “ብልፅግና” የተሰኘ ፓርቲ እያላቸው፤ ችግሮቻቸውን በውስጠ-ፓርቲም ሆነ በመንግሥታዊው መዋቀር ሳይጨርሱ ወደ አደባባይ መውጣታቸው ኢትዮጵያን የሚያፈርስ አደገኛ ዘመቻ እንደሆነ ማስገንዘቡን አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል። በዚህ መንገድ መጓዝ ከፈለጉ ‘ብልፅግና ወጥ-ፓርቲ ነው’ ብለው በምርጫ ቦርድ ያስመዘገቡበትን የምስክር ወረቀት መልሰው፤ ከተመቻው ጋር ተቀናጅተው ወይም በተናጠል መነታረክም ሆነ መተጋገል ይችላሉ። ከዚህ ውጪ፣ በሕግ አንድ ፓርቲ መስርተው ሲያበቁ፤ ከፓርቲ ዲስፕሊን አፈንግጠው፣ የሕዝብ እና የአገር አንድነትን አደጋ ላይ በሚጥል ድርጊት መሳተፍ፣ አገሪቱን ለማይታረም ስህተት የሚዳርግ መሆኑን “ፍትሕ መጽሔት” በጥብቅ ታሳስባለች።

 

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*