ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!

ውል ከሚታወቀው ታሪክ ጀምሮ ኢትዮጵያ ካለፈችባቸው የጦርነት ኹነቶች በተለየ፣ ዛሬ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ መግባቷ ርግጥ ነው። በታሪክ የሚጠቀሱትና ለሥልጣን በተደረጉት የእርስ- በርስ ጦርነቶች ቀርቶ፤ በውጭ ወራሪ በተደፈረባቸው ጊዜያቶች እንኳ ያልታየ እጅግ የከፋ ጦርነት በመካሄድ ላይ ነው።

ሕወሓት ከድርጅታዊ ፍጥረቱም ሆነ ከአገዛዝ ባህሪው ኃላፊነት የጎደለውና ለጠባብ ቡድናዊ ጥቅመኝነቱ ሲል “ቆምኩለት” የሚለውን የማኀበረሰብ ክፍል ጭዳ ከማድረግ የማይመለስ እንደሆነ ይታወቃል። ዛሬ ደግሞ፣ ከቀደመ ድርጅታዊ ግብሩ በከፋ ሁኔታ፣ ‹ከጠርሙሱ የወጣ ጂኒ› ሆኗል። ‹ኢትዮጵያን እኔ ካልገዛኋት፣ መፍረስ አለባት› ብሎ ሲኦል ድረስ እንደሚጓዝ በዐደባባይ ፎክሯል። ይህን ሰይጣናዊ መሃላውን ለመተግበርም የሞት-ሽረት ትግል እያደረገ ነው።

አንደኛ ዐመቱን ያስቆጠረው ጦርነት፣ በሕወሓትና የኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የሚደረግ ሳይሆን፤ ተዋናዩና የሚና ተሰላፊው ከሚገመተው በላይ፣ የጦርነቱ ገጽታውም መልከ ብዙ ሆኗል። የጦርነቱ ዋንኛ ዓላማም ኢትዮጵያን እንደ አገር በማስቀጠልና በማፍረስ መካከል ስለመሆኑ ሂደቱ እያሳየን ነው።

ሕወሓት በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳው አብዛሃውን የትግራይ ተወላጆች ከጎኑ በማሰለፍ እንደ ሕዝብ ጦርነት ውስጥ ከመግባቱ ባሻገር፤ ኦነግ-ሸኔ፣ የጉምዝ ታጣቂ፣ የቅማንት ኮሚቴ እና የአገው ነፃ አውጭ ግንባርን… የመሳሰሉ ፀረ-ሕዝብና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎችም ወግነውለት የሚካሄድ ጦርነት ነው። አዲስ አበባን ጨምሮ፤ በአገሪቱ ዋና ዋና ከተሞች በሽብር ወሬም ሆነ በሥነ-ልቦና እና የኢኮኖሚ ጦርነት የሚሳተፉ ደጋፊዎቹና የዓላማው ተጋሪዎች የት-የለሌ ናቸው።

የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት የማፍረስ ዓላማ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ያደረጉ ግብጽን የመሰሉትም ሆኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስተዳደር ጋር ቅራኔ ውስጥ የገቡ ጥቂት፣ ግን ደግሞ ሰፊ ተጽዕኖ ያላቸው የምዕራብ አገራት፣ ለሽብር ቡድኑ ወግነው እጃቸውን አስገብተዋል። ተሳትፏቸውም፡- አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ቁሳዊና መረጃ ተኮር… እንደሆነ ለመታዘብ ተችሏል።

በሊቢያ፣ ሶሪያ፣ የመን፣… እንደታየው ሁሉ፣ የውጭ ኃይል ቅጥረኛ ነፍሰ-ገዳዮች ከሕወሓት ጎን መሰለፋቸውንም ወታደራዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከትሪፖሊ እስከ ሰንዓ ለከፈላቸው የሚነዱ ሱዳናዊ ቅጥረኛ ጉዳዮች በኢትዮጵያ ምድር የመገኘታቸው ምስጢር፣ ከካይሮ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የሚቀዳ ስለመሆኑ ግልጽ ነው። በርግጥ የተሳትፏቸው ባህሪና አድማስ በዚህ አይወሰንም። ምክንያቱም የውጊያ ግንባሮች ድረስ የሚዘልቁ ምዕራባዊ የህክምና ዶክተሮች መገኘታቸውን ጨምሮ፤ የሕወሓት የጦርነት ስልት፣ የሳተላይት መረጃዎችን (Satellite Guided) መሠረት ያደረገ ለመሆኑ ከበቂ በላይ ማሳያዎች አሉ። ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ፣ የሚዲያ፣ የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ጫናዎች በእያንዳንዱ ዐውደ-ውጊያ ተጽዕኗቸውን እያሳረፉ ነው።

በኢትዮጵያ በኩል በአንድ ጎን ጦርነቱ ከሕግ ማስከበር ወደ ህልውና ዘመቻ ተንሸራቶ ቅርቃር ውስጥ የገባበት ግዘፍ-የሚነሱ ስህተቶች የተፈጠሩበት እና እሱን ተከትሎ ቁጥሩ እየናረ የመጣ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የታየበት ‹ብሔራዊ ስብራት› አጋጥሟል። በሌላ በኩል፣ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ የጦርነቱ ሜዳ በዐማራና አፋር ክልሎች ላይ በመሆኑ፣ የፌዴራሉ መንግሥት ጦርነቱን የሙሉ ጊዜ ግዳጅ ከማድረግ ይልቅ፤ ወረራውን በመመከቱ ረገድ ለክልሎቹ ሎጀስቲክስ አቅራቢ መስሎ መታየቱ ለሕወሓት ዕድል ፈጥሯል። ይህን ተከትሎ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የደረሰውና አሁንም የቀጠለው ውደመት በፖለቲካና ወታደራዊ አመራሩ መካከል በጦርነቱ ዙሪያ የሀሳብና የተግባር አንድነትን ከማሳጣቱም በላይ፤ የእርስ-በርስ አለመተማመንን ሲፈጥር ተስተውሏል። ይህ ክፍተት ትልቅ ትርጉም የሚሰጣቸው ዐውደ-ውጊያዎች እንዲበላሹ ምክንያት ሆኗል። ለሰርጎ-ገብ ጥቃትም በር ከፍቷል። የእዚህ ድምር ውጤትም የሽብር ቡድኑን ወረራ አስፍቶታል።

የሆነው ሆኖ፣ በ“ፍትሕ መጽሔት” እምነት ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንዲቋጭ፣ በፌዴራሉ መንግሥት በኩል የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግሥት ለመታደግ የሚያስችል ሙሉ ቁርጠኝነትና የጦር ዝግጅት ከማድረግ በዘለለ፤ በጦርነቱ የውጤት ትርፍ ላይ ቡድናዊ ጥቅምን ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ክብርና ህልውና ሊረጋገጥ በሚያስችል ደረጃ ለሠንደቋ መታመን ግድ ይላል።

ከጦርነት ተግባቦት ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ደካማ የሕዝብ ግንኙነት ሥራም በሕዝብና መንግሥት መሃል አዎንታዊ መተማመን እንዳይኖር አድርጓል። ይህን ችግር በእውቀትና በፖለቲካ ግልጸኝነት በማስተካከል፣ ሕዝብን ለአንድ ዓላማ ማሰለፍ ይገባል። ሕወሓት የሚገለጸበት መንገድም ሆነ ህሊናዊና አካላዊ ድርጊቶቹ የሚብራሩበት ዐውድ ወጥነት እንዲኖረው ማድረጉም መዘንጋት የለበትም። ‹ዱቄት ሆኗል› በተባለ በወራት ልዩነት ‹ከሠራዊቱ ዐቅም በላይ ነው› በሚል አግባብ የተገለጸበት ሁኔታ፣ በሕዝብና መንግሥት መሃል መተማመን እንዳይኖር አደጋ መሰንቀሩን ልብ ይሏልና።

ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አተገባበር ጋር በተያያዘም የሕወሓት ደጋፊዎችና የዓላማው ተጋሪዎች፣ በኢትዮጵያ ወሳኝ ከተሞች ያላቸውን አፍራሽ ሚና መመንጠርና ማምከን የሚቻለውም፣ ዜጎችን በአስተሳሰብ የሀገረ- መንግሥቱ ዘብ ማድረግ ሲቻል ነው። ምክንያቱም አሁን ያለውን አገራዊ ቀውስና የውጭ ጣልቃ-ገብነቶች ብሔራዊ መረጃ እና ሕግ አስከባሪ ተቋማት ብቻቸውን የሚቋቋሙት አይደለም። ስለዚህም መንግሥት ዜጎች፣ ሰርጎ-ገቦችንና ከኢትዮጵያ ህልውና በተፃራሪ የሚቆሙ አካላትን በንቃት እንዲከታተሉም ሆነ ለሕግ አሳልፈው እንዲሰጡ ያልተቋረጠ የሕዝብ ግንኙነት ሥራና አደረጃጀት መፍጠር ይጠበቅበታል። እዚህ ላይ ፍትሕ ትልቁ አዕማድ እንደሆነ ይሰመርበት።

የጦርነቱ ተዋናዮችና መልከዐ-ሁኔታ ብዙ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያና ዜጎቿ በአንድነት ከመቆም ውጭ የተናጠል መዳረሻ ዕጣ-ፈንታ እንደሌላቸው እሙን ነው። አገሪቱ በታሪኳ ዘመነ-መሳፍንትን የመሰሉ ብርቱ ብሔራዊ ፈተናዎችን መሻገር የቻለችው በአንድነት ኃይል ነው። አሁን ያለችበት ፈተና የቱንም ያህል ብርቱ ቢሆን እንኳ፣ የማይናወጥ አንድነት መፍጠር ከተቻለ ኢትዮጵያ በመከራው መካከል እንደ ዐዲስ ትወለዳለች።

በጦርነቱ ላይ አካላዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ፣ ቁሳዊና መረጃ ተኮር… ተሳትፎ ያላቸው የውጭ ኃይሎች መቼም ለኢትዮጵያ እንደማይተኙ የኋላ ታሪካቸው ያስረግጣል። በዳግማዊ የጣሊያን ወረራ ሊጎ ኦፍ ኔሽን ላይ ለፋሽስት በመወገን፣ ዚያድባሪ 700 ኪ.ሜ ዘልቆ በወረረ ጊዜ ደግሞ አገሪቱ ራሷን እንዳትከላከል የጦር መሳሪያ ግዥ ማዕቀብ በመጣል ክህደታቸው እናውቃቸዋለንና። የዛሬውም ዐዲስ ነገር አይደለም።

በታላቁ ዲፕሎማት አንደበትም ኢትዮጵያ ‹‹… መቼውንም ለሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም። ዛሬም ሆነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅ፣ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ ያለባት፣ እሷ ብቻ ነች።››

አዎን፣ በዚህ መንፈስ ኢትዮጵያ ታሸንፋለች!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*