ኢትዮጵያ…

ትዮጵያ ህልውናዋን በፈተኑ ከበባድ አደጋዎች ማለፏ እሙን ነው። ከፋፍው ሊያዳክሟት የሞከሩ ኃይሎች እንደሚሉት፣ አያሌ ዘመናትን ያስቆጠረው አንድነቷ ከሜዳ የታፈሰ አይደለም። የበዛ የደም ዋጋ የተከፈለበት ነው።

ከታላቁ የዐድዋ ድል በፊትም ሆነ በኋላ፣ ዳር ድንበሯን የተዳፈሩትን ሁሉ በክቡድ መሰዋትነት መክታለች። የኢትዮጵያ አንድነት፤ ከሦስት ሺህ ዘመናት በላይ ከትውልድ ትውልድ፣ ሲወርድ ሲወራረድ በደምና አጥንት ዋጋ የመጣ ነው። በኢትዮጵያ ጥቁር ሠማይ ሥር የተጠለሉ ማኅበረሰቦች ሁሉ እንደ አንድ ሕዝብ ይህን የማይተካ ሕይወታቸውን ከፍለውበት ነው። መስዋዕት ሆነውበት ነው።

የዚህ ሁሉ ወገንን መስዋዕትነት በተምሳሌት የሚገልጸው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሠንደቅ ዓላማ ነው። ድል ሆነን በጋራ ያለቀስንበት፤ ድል አድርገን በጋራ የፈነደቅንበት። በሀገረ-መንግሥት ግንባታ ሂደት፣ ሀገርን ሀገር አድርገው ከሚያበጁ ዋቢ ኹነቶች ውስጥ በጋራ መጎዳት እና በጋራ መደሰት ትልቅ ሥፍራ ይይዛሉ።

ኢትዮጵያዊያን በአለንበት መልከዐ-ምድር በብዙ የጠላት ወረራዎች ተጎድተን፣ ወገኖቻችን ተገድለው በጋራ አዝነናል፤ በጋራ አልቅሰናል። በአንፃሩም፣ የተፈጸመብንን ወረራ ሁሉ ትውልዱ ዋጋ እየከፈለ፣ ራሳችንን ተከላክለን ነፃነታችን እና ሉዓላዊነታችንን አስከብረን በጋራ ድል አድርገን፣ በጋራ ተደስተናል፤ በጋራ ኮርተናል፤ የጋራ ደማቅ ታሪክ ሰርተናል።

በሌላም በኩል፣ በተለያዩ ጊዜያት በክፉ ቸነፈር ተመተን ወገኖቻችን በገፍ ሞተዋል፤ አካላቸው ጎድሏል፤ እንዲህ ዓይነቱን ክፉ ጊዜም በጋራ ተረዳድተንና ኅብር ፈጥረን ተወጥተን፣ ብዙ የፍሰሃ ጊዜያትን በጋራ አሳልፈናል። ይሄ ሁሉ የጋራ ታሪካችን ነው፤ የውድቀት ሥኬታችን ነው።

ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የሥኬትም ሆነ የውድቀት ዕጣ- ፈንታችን በጋራ የተሰራና የተሠናሠለ ነው። አንድ ስንሆን ስኬታማ፤ ስንበታተን ደግሞ ደካማ እንሆናለን። ይህን ኹነት ለመረዳት የ30 ዓመቱን የምሥራቅ አፍሪቃ ጂኦ- ፖለቲካ ማስተዋል ብቻ በቂ ነው። የኢትዮ-ኤርትራን መለያየት እና በሕብር መቆም የሚገልጽልን መልዕክት አለ። እርሱም ታሪካችን እንደ አንድ ነጠላ ጥለት በኅብር የተጠለፈ መሆኑን ነው።

ኢትዮጵያ እንደ በአጭር ጊዜ ተፈጭታና ተቦክታ የተጋገረች የሚመስላቸው ከውስጣችን ጎሰኛ ኃይሎች እና ስምሪት የሚሰጧቸው ቀለብ ሰፋሪ ኢትዮጵያ-ጠል ታሪካዊ ጠላቶች እንደሚነዙት ትርክት ቢሆንማ ኖሮ፤ ገና ድሮ ከ40 ዓመታት በፊት በፈረሰች ነበር።

ሆኖም፣ ኢትዮጵያ ሊያፈርሷት በሞከሩ ቁጥር፣ የበለጠ እየበረታች፤ ሊበታትኗት ባሰቡ ቁጥር፣ እየተሰባሰበች፤ በሀገረ ግዛቷ የብስ፣ በወንዙና በኃይቁ ላይ፣ በየተራራው፣ በአየሩ ላይ የተነዛ የትውልድ ሠንሠለት መስዋዕትነት- ከአድማስ አድማስ ናኝቷልና እንደ ድንገት ደራሽ ጎርፍ የመጣ ኃይል ሁሉ ሊያፈርሳት አልቻለም፤ አይችልምም።

ዓይኖቻችን ከመመልከት ቢቦዙም፣ ጆሯችን ዳባ ልበስ ቢሉም፣ ሥሜታችን በድን ቢሆንም፣ አንደበታችን ልጉም ቢሆኑም ቅሉ፣ የእነርሱ (የቀደምት ቤተሰቦቻችን) መስዋዕትነት ዛሬም ህልው ነው። ሀገራችን የጋራ ጎጇችን ናት፤ በጋራ ለጋራ የምናበጃት።

ይህን ምስጢረ ኢትዮጵያ ነው ጠላቶቻችን አውቀው ሊያጠፉት ያልቻሉት፤ የኢትዮጵያዊነት ሥውር ንጥረ- ነገር (ኬሚስጥሪ)ን እንኳን እነርሱ፣ እኛ ዜጎቿ በቅጡ አልገባንም። ኢትዮጵያን አጠፋለሁ የሚል ኃይል ሁሉ ቀድሞ የሚጠፋበት የጋረደበት አንዳች ተአምራዊ ኃይል መኖሩ ግልጽ ነው።

ላለፉት ክፍለ ዘመናት፣ ኢትዮጵያ ከውጪውም ከውስጥም በተነሱባትና በሚነሱባት ጠላቶች እልፍ አዕላፍ ጦርነቶችን አድርጋ፣ ራሷን ተከላክላለች። ለዚህም የኢትዮጵያ እናቶች ማህጸን ይለምልም። ወላድ በድባብ ትሂድ!

ጣሊያን ከአንዴም ሁለት ጊዜ በግፍ ወሮን፣ በኢትዮጵያዊያን ተዋርዶ ተመልሷል። ደርቡሽ መጥቶ፣ ተመትቶ ሄዷል። ግብጽ በተደጋጋሚ ወረራ ሞክራ ከእነ ቅጥረኛ አውሮጳዊ ጄኔራሎቿ ተቀጥቅጣ ተመልሳለች። ሌላም ሌላም እንዲሁ።

በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር፣ ትውልድ ሁሉ ለሀገሩ መስዋዕትነት መክፈሉን ያውቅበታል። በዚህ ረጂም የትውልድ ቅብብሎሽና ቅጥልጥሎሽ፣ ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተጠቅተናል፤ በጋራ ተዋርደናል፤ በጋራ ሀገራችንን ተከላክለን ድል አድርገናል፤ በጋራ ብሔራዊ ኩራታችንን፣ ነፃነታችንንና ሉዓላዊነታችንን አጣጥመናል።

እንደ ሕዝብ በጋራ ተርበናል፤ ተጎድተናል፤ ችግሩን በጋራ ተወጥተነዋል፤ በጋራ ድል አድርገን አንድነታችንና ድላችንን አክብረናል፤ እያከበርንም እንገኛለን። የጋራ በደልና ሀዘን እንዳሳለፍን ሁሉ፤ የጋራ ደስታና ሀሴት አድርገናል።

አደዋ ላይ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ክተት ሠራዊት ያሉት፣ ለጋራ ህልውናቸው ነው። ድሉም የጋራቸው ነው። ፋሽስት ጣሊያን ከ40 ዓመታት ዝግጅት በኋላ ለበቀል ወረራ ሲመጣ አምስቱ የዐርበኝነት ጊዜያት እቶን እሳት የሆነበት፣ ሁሉም ዘማች ወደየ አካባቢው በመመለስ የራሱን የትጥቅ ትግል በመጀመሩ፤ የጦርነቱ ማዕከል ወደ ብዙ ዓውድ ስለተለወጠበት ነው።

የኢትዮጵያ ሕዝብ የትኛውንም ጦርነት የተዋጋው ዘር ቆጥሮ አይደለም። ኢትዮጵያዊ ሆኖ ነው።

እንኳን ለ125ኛው የአድዋ ድል በዓል አደረሳችሁ!!!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*