
የሰሜኑ ጦርነት ከባቢውን እያሰፋና ከተገመተው በላይ እየተወሳሰበ በመሄዱ፣ የፌዴራሉ መንግሥት፣ ዘጠኙ ክልሎች እና ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ክተት አውጀዋል። የልዩ ኃይላቸውን አባላትም ወደ ተለያዩ የጦር ግንባሮች አዝምተዋል።
በዚህ ዐውድ የምናነሳው አጀንዳም የዐማራ እና አፋር ክልሎች ካስተላለፉት የክተት አዋጅ ጋር የሚያያዝ ነው።
ዛሬ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ የሄደውን ጦርነት በድርድር እና በውይይት መፍታት የሚቻልበትን መንገድ ማፈላለጉ ቸል የሚባል አይደለም። ይህም ሆኖ የሕወሓት ተዋጊዎች አገሪቱን ለማፍረስ ከፍተኛ ውድመት እያደረሱ ከመሆናቸው በዘለለ፤ ሰላማዊ ዜጎችን፣ በተለይ ሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጽሙትን ጭፍጨፋ ማስቆም የሕግም የሞራልም ግዴታ ነው። የሽብር ቡድኑ “ማኀበራዊ መሰረቴ” ከሚለው ክልል ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቆና ወደ አጎራባች ክልሎች ገፍቶ በመግባት የከፈተውን ጦርነት ለመመከት ክተት መታዋጁም ተገቢ ነው። በየትኛውም አገር፣ እንዲህ ዐይነቱ አገርን ከጥቃት የመከላከል ርምጃ ጦርነት ናፋቂ ተደርጎ ሲያስወነጅል ታይቶ አይታወቅምና።
እዚህ ጋ የሚነሳው ችግር፣ የክተት አዋጁን ከተቀበሉት ውስጥ የሚበዙት የውትድርና ሥልጠና የሌላቸው በመሆኑ፣ የሚሰጣቸው ስልጠና ወደ ውጊያ ቀጠና ሲገቡ ከሚገጥማቸው ኹኔታዎች ጋር ምን ያህል ይመጣጠናል? ጦርነት በባህሪው ከሚጠይቀው ጥብቅ ሥነ-ሥርዐት (ዲሲፕሊን) አኳያስ፣ የእዝ ሠንሰለቱን ጠብቀው ግዳጃቸውን ለመወጣት ያስችላቸዋል ወይ? የሚሉት ጥያቄዎች በቂ መልስ አለማግኘታቸው ነው።
በርግጥ ይህ ክፍተት መከላከያን የሚቀላቀሉ ዘማቾችን አይመለከትም። ምክንያቱም መከላከያ በቂ ማሰልጠኛዎች ያሉት ግዙፍ ወታደራዊ ተቋም በመሆኑ፣ በክተት አዋጁ የሚቀበላቸውን ምልምሎች በአግባቡ አሰልጥኖ ለማውጣት ያቅተዋል ተብሎ አይታሰብም። ይህ ጉዳይ ችግር የሚሆነው ለዐማራ እና አፋር ክልሎች ነው። ሁለቱም ክልሎች በእንዲህ ዐይነቱ አዋጅ የሚቀላቀላቸውን የሰው ማዕበል ቀርቶ፤ በሰላሙም ጊዜ ልዩ ኃይላቸውን የሚያሰለጥኑበት የራሳቸው የሆነ አንድ እንኳ ማሰልጠኛ እንደሌላቸው ይታወቃል። አሁን ያወጁትን የህልውና ዘመቻ ተከትሎ ደግሞ፣ ቁጥሩ እጅግ የተጋነነ (ምናልባትም በሚሊዮን የሚቆጠር) ሕዝብ ጥሪያቸውን እየተቀበለ ነው። እናም ለዚህ ሁሉ ወፈ-ሰማይ ዘማች ቀርቶ፤ ቁጥሩ እጅግ ትንሽ ለሆነው የልዩ ኃይል አባላቶቻቸው እንኳ የወታደራዊ ሳይንስ አስተምህሮን ያሟላ ስልጠና መስጠት የሚችሉበት ተቋም የላቸውም። የችግሩን አሳሳቢነት የሚያጎላውም ይህ ነው።
ይህም ሆኖ ግን፣ የክተቱን ጥሪ ተቀብለው የመጡ አርበኞችን፣ ቢያንስ በዐውደ ውጊያው ሊጠቀሙበት በሚችሉት ትክክለኛ የነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ የሚሰለጥኑበትን መንገድ ማመቻቸት፣ ያን ያህል ከባድ ሊሆን አይችልም። ስለዚህም አንዳንድ አካባቢዎች እየታየ ያለው “አጠና”ን እንደ ጠመንጃ በመሸከም የሚደረግ ልምምድ የትም የሚያደርስ ባለመሆኑ፣ የተሻለ ስልጠና የሚሰጥበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ሌላኛው ችግር ወይም በሂደት አደጋ ሊሆን የሚችለው የእዝ ሠንሰለቱን የሚመለከት ነው። በአንዳንድ ግንባሮች ከመከለከያ ሠራዊቱ፣ ከልዩ ኃይሎች እና ሚሊሻ ውጭ ያሉ አደረጃጀቶች፣ በአንድ የእዝ ጠገግ አለመካተታቸው እተስተዋለ ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ እንኳን በጦርነት፣ በሰላሙም ጊዜ ሥርዐት አልበኝነትን የሚያነብር አደጋ ነው። እናም ጉዳዩ የህልውና ዘመቻ እስከ ሆነ ድረስ፣ ሁሉም ተዋጊ ወይ በመከላከያ አልያም በልዩ ኃይል ስር ብቻ ሆኖ ግዳጁን እንዲወጣ ማድረግ ግድ ይላል።
በዚህ በኩል ያለውን ችግር ለመቅረፍ ራሱ ወዶ ዘማቹም ኃላፊነት አለበት። ማንም ሰው በዘፈቀደ ‘እዚህ ግንባር ዘምቻለሁ’፣ ‘እዚያ ግንባር ተቀላቅያለሁ’… ከማለት መቆጠብ ይኖርበታል። ስምሪት መስጠት፣ የመከላከያ እና የክልል ልዩ ኃይል አዛዦች ሥልጣን ሲሆን፤ መቀበልና መተግበር ደግሞ የሁሉም ዘማች ግዳጅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ዘመቻውን የሚቀላቀሉ የገዥው ፓርቲም ሆነ የተቃዋሚ አመራር አባላቶች ውጤታማ አስተዋጽኦ ሊኖራቸው የሚችለው የእዝ ጠገጉን ተከትለው ሲሰማሩ ብቻ እንደሆነ ማስታወስ ይጠበቅባቸዋል።
“ፍትሕ መጽሔት”፣ ጦርነቱ በማንኛውም መንገድ መቋጫ እስኪያገኝ ድረስ፣ ዘመቻውን እና ዘማቹን በተመለከተ ሁለት ዐቢይ ጉዳዮች ላይ አጽንኦት እንዲሰጥ ታሳስባለች። የመጀመሪያው፣ የዐማራ እና አፋር ክልላዊ መንግሥቶች በክተት አዋጁ የሚመጡ ዜጎችን፣ ከላይ እንደተጠቀሰው ቢያንስ በዐውደ ውጊያ ለሚጠብቃቸው ተግዳሮት የሚመጥን ስልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታቸውን መወጣት ያለባቸው መሆኑ ነው። ሁለተኛው፣ የትኛውም ዘማች አገሩን ለመታደግ ወስኖ እስከ ተቀላቀለ ድረስ፣ የተመደበበትን የመከላከያን ወይም የልዩ ኃይሉን የእዝ ሰንሰለት አክብሮ፣ በሚሰጠው ግዳጅ ላይ ብቻ ማተኮር እንዳለበት የሚያስታውስ ነው። መቼም ለማጥቃትም ሆነ ለማፈግፈግ የአመራሩን ትእዛዝ መጠበቅ ግዴታ መሆኑን ለመረዳት፣ ወታደራዊ ሳይንስ ማወቅ አይጠይቅም።
በጥቅሉ፣ በጦር ሜዳ ሕግ የማይፈቀደውን ‘አስክሬን ይዤ ወደ መንደሬ እመለሳለሁ’ ማለትም ሆነ በእጅ ስልክ እየደወሉ የጦርነቱን ውሎ መዘክዘክ፣ ዘመቻውን ከሚያደናቅፉ ተግባራት ዋንኞቹ እንደሆኑ አለመዘንጋቱ ይመከራል።
ድል የሕዝብ ነው!
Be the first to comment