የሕዝብ ድምጽ ይከበር!

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት ሊቀ-መንበር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ፣ አገሪቱ በታሪኳ አይታ በማታወቀው መጠን ሰላማዊ ዜጎቿ በግፍ ተጨፍጭፈውባታል፤ ሃብት ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ከኖሩበት ቀዬ በገፍ ተፈናቅለዋል። ይህ እኩይ ድርጊቱ አሁንም ቀጥሏል።

መንግሥታቸውም ችግሩን ከመቆጣጠር ይልቅ፤ የበለጠ እንዲንር ለአጥፊዎቹ መዋቅራዊ እገዛ እያደረገ ለመሆኑ ግላጭ የወጡ ማሳያዎች አሉ። በተለይ የኦሮሚያ ክልል አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የክልሉ የአመራር አባላት በአደባባይ ማንነት-ተኮር የጠላቻ ንግግር ደጋመው ማድረጋቸው፣ አሁንም እያደረጉ መሆኑ ተጠቃሽ ነው። የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲም አጥፊዎቹን በመግለጫ ከመደገፍ አልፎ፤ በፓርላማው ጭምር የሀሰት ክስ የሚያቀርቡ የምክር ቤት አባላትን በመመደብ፣ በተጎራባች ክልሎች ሰርጎ-ገቦችን በመላክ… የሚያደርገው ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ፣ አገሪቱን ወደ ፍርሰት-ጠርዝ እየገፉ ስለመሆኑ መረዳት ተስኖታል።

ይህ ሁኔታም ከዕለት ወደ ዕለት፣ ከቁጥጥር ውጪ ወደ መሆን አዘንብሏል። በተለይ ባለፈው ሳምንት መነሻውን በዐማራ ክልል የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ያደረገው አጥፊ ኃይል፣ በከፈተው ጦርነት የበርካታ ሰላማዊ ዜጎች ህልፈት እና ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል።

ከዚህኛው ጥቃት በፊት (በመጋቢት ወር አጋማሽ) ይኸው የሽብር ቡድን በዐማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ወረዳዎች ላይ ጦርነት ከፍቶ ሰላማዊ ሕዝብን ሲጨፈጭፍ፣ የኦሮሚያ ብልፅግና ባወጣው መግለጫ ከእውነታው አፈንግጦ፣ የዐማራ ክልል ልዩ ኃይል ንፁሃንን የጨፈጨፈ አስመስሎ በማቅረብ፣ ውገናው ከሽብር ቡድኑ እንደሆነ አስረግጧል። በተጨማሪ፣ በአካባቢው የሌለውን ኦነግ ያለ አስመስሎ፣ “ኦነግ-ሸኔ” በሚል የፈረስ ስም ወንጀለኞቹ በሕግ እንዳይጠየቁ ለማድበስበስ ሞክሯል።

እውነታው ግን መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ መረጃ፣ የዐማራ ክልል ብልፅግና እና የፀጥታ መዋቅሩ ባደረጉት ማጣራት፣ ጥቃቱን የሰነዘረው ታጣቂ ኃይል ከኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን መነሳቱን እና የዞኑ አመራሮችም እጃቸው እንዳለበት የሰበሰቡት መሳረጃዎች ማጋለጣቸው ነው። ይሁንና፣ ከጥቃቱ በኋላ የተወሰደ ሕጋዊም ሆነ ፖለቲካዊ እርምጃ አለመኖሩ፣ የክልሉ እና የፌደራሉ መንግሥት የሚመሩትን ሕዝብ ከየትኛውም ጥቃት እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የመጠበቅ ኃላፊነታቸው መወጣት እንደተሳናቸው ወይም እንዳልፈለጉ አስረግጧል። ኹነቱን ይበልጥ አሳዛኝ ያደረገው ደግሞ፣ ይኸው ኃይል እና የዞኑ መዋቅር ሰላማዊ ሕዝብና ከተሞች ላይ ዳግም መጠነ-ሰፊ ጥቃት እንዲሰነዝሩ ማድረጉ ነው።

ከሚያዚያ 6 ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በአጣዬ ዙሪያ በማጀቴ፣ በካራ ቆሬ፣ በኔጌሶ፣ በኩሪቱሪ፣ በቆሬ ሜዳ እና በሌሎችም አካባቢዎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ በከባድ ማሳሪያ በተደገፈ ጥቃት ተሰንዝሮ አያሌ ዜጎች መስዋት ሆነዋል፤ እጅግ የበዛ የንብረት ውድመት ደርሷል። በተለይ አጣዬ እና ካራ ቆሬ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚያስደፍር ደረጃ ወድመዋል፤ ተዘርፈዋል። ይሄ ሁሉ ሲሆን፣ የሽብር ቡድኑ መነሻ በሆኑት የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ስር ያሉት እና ከሰሜን ሸዋ ዞን ጋር በሚዋሰኑት የኬሚሴ ከተማ አስተዳደር፣ የዳዋ ጨፋ ወረዳ፣ የአርጡማ ፋርሲ ወረዳ እና የጅሌ ጥሙጋ ወረዳዎች አንድ ጥይት ሳይጮኽ መዋሉ ታይቷል። በዞኑ ያሉ አስተዳዳሪዎችም ጦርነቱን በተለያየ መንገድ መምራታቸውን የሾለኩ መረጃዎች ያስረግጣሉ። የዞኑ አስተዳዳሪ አቶ አህመድ ሀሰን ለአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ዘመናዊ የጦር መሳሪያ በታጠቀ ኃይል የደረሰውን ከፍተኛ ጉዳት፣ በተቆጦ አርሶ ዐደሮች የተፈፀመ አስመስሎ በማቅረብ ሕዝብን ለማታለል ሞክሯል። ግለሰቡ ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ የሰላማዊ ዜጎች እልቂት እጁ እንዳለበት ማስረጃ ተገኝቶ ቢከሰስም፤ ባልታወቀ ምክንያት ክሱ ውድቅ ከመደረጉም በዘለለ፤ ወደ ሥልጣኑ ተመልሷል።

በሌላ በኩል የሚያዚያውን መጠ-ሰፊ ጭፍጨፋ ተከትሎ፣ በበርካታ የዐማራ ክልል ከተሞች ግዘፍ- የሚነሱ ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል። ሰልፈኛው ካስተጋባቸው መፈክሮች ውስጥ “ዐማራን መጨፍጨፍ ይቁም”፣ “የዜጎች ጭፍጨፋ ይቁም”፣ “ገዳዮቻችን ለፍርድ ይቅረቡ”፣ “ሸዋ የገባው ኮማንድ ፖስት ገለልተኛ አይደለም” የሚሉና የመሳሰሉት ዋንኞቹ ናቸው።

ይሁንና፣ ሕዝቡ ተፈጥሯዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብቶቹ እንዲከበሩ በነቂስ ወጥቶ ቢጠይቅም፤ የፌደራሉ መንግሥት እንደ ወትሮው ባልተገራ ዝምታ (በንቀት) ከማለፉ በዘለለ፤ አንዳንድ የኦሮሚያ ብልፅግና አመራሮች በማኀበራዊ ሚዲያ ጉዳዩን የሴራ ፖለቲካ ለማስመሰል ሲሞክሩ ታዝበናል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድም ዐደባባይ የወጣው ሕዝብ “በህይወት መኖር ሳይቻል፣ ምርጫ ብሎ ቅንጦት የለም!!!” በሚል ላቀረበው ጥያቄ፣ በፌስቡክ ገጻቸው በጥቂት ሰዓት ልዩነት ሁለቴ ባስተላለፉት መልዕክት ‹የምርጫ ካርድ ውሰዱ› ሲሉ በመሳለቅ፣ ምንግዴነታቸውን በይፋ አሳይተውታል።

የዐማራ ብልፅግናም በተመሳሳይ መንገድ ከጥያቄው ይልቅ፣ የብልፅግና ፕሬዚዳንት ስም በተቃውሞ መነሳቱ እንዳሳሰበው ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል።

“ፍትሕ መጽሔት” የፌደራሉም ሆነ የክልሉ መንግሥት ሕዝብ በአደባባይ “አትግደሉን” ብሎ ላቀረበው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ የመሰጠት ውዴታ ሳይሆን፤ ግዴታ እንዳለባቸው ታስገነዝባለች። ከዚህ ባለፈ፣ ከሰልፉ ዋንኛ ጥያቄዎች እና ምስሎች አፈንግጦ፣ በአንዲት ባነር ላይ የተጻፈ ምልዕክትን ዋናው አጀንዳ ማድረግም ሆነ ጉዳዩን በተቃዋሚ ፓርቲ የተቀነባበረ ሴራ ለማስመሰል መሞከር ጽዩፍና ተቀባይነት የሌለው የቁማር ፖለቲካ ነው።

1 Comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*