የማኀበራዊ ተቋማት ውድመት እና የትውልድ ክፍተቱ | ርእስ አንቀጽ

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ቅርጽና ይዘቱን እየቀየረ ከቀጠለ አስራ አንደኛ ወሩን ይዟል። ለሕወሓት የአገር ክህደት አጸፋዊ ምላሽ የተጀመረው ‹ሕግ የማስከበር ዘመቻ›ም፣ ከስምንት ወር በኋላ ‹ኢትዮጵያን የማዳን የህልውና ዘመቻ› ወደሚል ተሸጋግሯል። የሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት መጠኑም በዚያው ልክ ጨምሯል።

በተግባር አሸባሪነቱን ያስመሰከረው ሕወሓት፣ ጦርነቱን ከመደበኛዋ ትግራይ ውጭ በማድረግ በዐማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ንፁሃንን መጨፍጨፍ ከጀመረ ሦስተኛ ወሩን አስቆጥሯል። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ሙሉ ትኩረቱ፣ “ታሪካዊ” ጠላት በሚል በፈረጀው የዐማራ ክልል ዞኖች ሆኗል።

የጦርነቱ አድማስ እየሰፋ መምጣት፣ ተራዛሚነቱ፣ የሕወሓት የጦር ወረራ አፈጻጸምና በተግባር ከሚታዩ አስከፊ ውደመቶች አኳያ፣ አጠቃላይ የአገሪቱን የኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ማኀበራዊ መሰረቶች እያናጋ ነው። ሕወሓት ጦርነቱን ከትግራይ ውጭ እንዲሆን ካደረገበት ጊዜ ጀምሮ በሁለቱ የትግራይ አዋሳኝ ክልሎች በተለይም ጦርነቱ በተካሄደባቸውና እየተካሄደባቸው ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ላይ የሚደርሰው መከራ ግዘፍ ነስቷል።

የሽብር ቡድኑ ከጦርነቱ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸውን ዜጎች እና የማኀበራዊ ልማት ተቋማትን ማጥቃት ዒላማ ማድረጉ፣ በሐሰት ትርክት ስለቆመው የበቀል ብሔርተኝነቱ ማስመስከሪያ አድርጓቸዋል። ‹ሂሳብ አወራርዳለሁ› የሚለው ፀረ-ሕዝብ አባባሉ በተግባር ሲገለጥ ንጹሃን አርሶ ዐድሮች፣ የከተማ ንዑስ አምራቾች፣ ተራ የመንግሥት ሠራተኞች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሴቶች፣ ህጻናትና አዛውንቶችን ከማጥቃት አልፎ፤ የጤና እና የትምህርት ተቋማትን ማውደም እንደሆነ በእነዚህ ሦስት ወራት በስፋት ታይቷል። የአርሶ ዐደሩ እና የአርብቶ ዐደሩ የቁም እንስሳትም የሂሳብ መወራረጃው ስሌት አካል መሆናቸው ስለጦርነቱ አስከፊነት የሚናገረው እውነት አለ።

ባሳለፍነው ሳምንት የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ባወጣው መረጃ በሕወሓት የጦር ወረራ 455 ትምህርት ቤቶች ወድመዋል። የዐማራ ክልል በበኩሉ እስካሁን ከወረራ ነፃ በወጡ አካባቢዎች 268 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ፤ 2,635 ትምህርት ቤቶች እና 16 ሙያና ቴክኒክ ኮሌጆች ተዘርፈዋል። በዐማራ ክልል ብቻ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ትምህርት ቤቶች ጉዳት ደርሶባቸዋል። የጤና ተቋማትን ዘረፋና ውድመት ስንመለከት ደግሞ በዐማራ ክልል ብቻ 14 ሆስፒታሎች፣ 153 ጤና ጣቢያዎች እና 642 ጤና ኬላዎች ተዘርፈዋል። በአፋር 1 ሆስፒታል፣ 10 ጤና ጣቢያ፣ 38 ጤና ኬላዎች በተመሳሳይ ተዘርፈዋል።

ከህወሓት የጦር ወረራ ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል 1.8 ሚሊዮን ዜጎች ተፈናቅለዋል። ከእነዚህ ውስጥ 256 ሺሕ ያህሉ ህጻናት ከአምስት ዐመት በታች ናቸው። ከ76 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ እናቶች ናቸው። በአፋር 112,000 ዜጎች ከመኖሪያ ቀያቸው ሲፈናቀሉ፤ አብዛኛዎቹ ህጻናት እና የሚያጠቡ እናቶች ናቸው።

አግባብነት ባላቸው ዓለም ዐቀፍ ሕጎች በጦርነት ወቅት የማኀበራዊ ልማት (ትምህርት፣ ጤና…) ተቋማት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው የተደነገገ ቢሆንም፤ ሕወሓት በወረራ በያዛቸውና ይዟቸው በነበሩ አካባቢዎች በሚገኙ ተቋማት ላይ ከፍተኛ የሆነ ዝርፊያና ውድመት አድርሷል።

የህክምና ተቋማት ህንጻ መፍረስ፣ የላብራቶሪ እና ሌሎች የህክምና መሳሪያዎች፤ እንዲሁም የግል የህክምና እና የጤና ተቋማት መረጃዎች መዘረፍና ሙሉ በሙሉ መውደማቸው መጠነ-ሰፊ የሆነ የጤና ቀውስ ያመጣል። በተለይም የተላላፊ ወረርሽኝ አደጋ ተጋላጭነት፣ የነፍሰ- ጡር እናቶች እና ህፃናት የጤና ክትትል መቋረጥ፣ ቋሚ ክትትል የሚደረግላቸው ህሙማን የጤና ክትትል መቋረጥ… የሚፈጥሩት የጤና ቀውስ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ህይወት፣ በመኖር እና ባለመኖር አደጋ ውስጥ ከቶታል።

በተመሳሳይ የትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰው ውድመትና ዘረፋ ከትምህር ገበታ ውጭ የሚያደርጋቸው ተማሪዎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ አሻግሮታል። ለዘረፋና ውደመት የተጋለጡ ወልድያን የመሰሉ ዩኒቨርሲቲዎችን ከጉዳት የማገገሚያ ጊዜ ስናስብ እንደ አገር የተማረ የሰው ኃይል እና ብቁ ባለሙያ ማፍራት ላይ አደጋ መደቀኑን “ፍትሕ መጽሔት” ታምናለች።

በዐዲሱ የትምህርት ዘመን ትምህርት የማይጀምሩ ተማሪዎች በጦርነቱ ከተፈናቀሉ ዕድሜቸው ለቅድመና መደበኛ ትምህርት የደረሱ ህጻናትና ታዳጊዎችን ከአጠቃላይ ተፈናቃዮች ግምት ውስጥ ስናስገባ፣ በጦርነቱ ከሚያልቀው የሰው ኃይል ጋር ተደምሮ በቀጣይ አስፈሪ የትውልድ ክፍተት ስለማጋጠሙ ተገማች ነው። በተለይም ጦርነቱ ያደረሳቸው የኢኮኖሚ ድቀቶችና ያስከተላቸው ማኀበረሰባዊ እና ሥነ-ልቦናዊ ቀውሶች በቀላሉ የማይሽሩ መሆናቸው በቃጣይ የሚፈጠረውን የትውልድ ክፍተት አስፈሪ ያደርገዋል።

ሰሜን ኢትዮጵያን መልሶ ማቋቋም በዐመጸኛው ሕወሓት መቃብር ላይ የመሆኑ እውነታ ርግጥ የሆነ ቢሆንም፤ የጦርነቱ በአጭር ጊዜ አለመቋጨት በትውልዱ መጻዒ ተስፋ ላይ የሚፈጥረው ጽልመት፣ የኢትዮጵያ አገራዊ ህልውና ክስመት አካል ስለመሆኑ የዐቢይ አህመድ መንግሥት ልብ ሊለው የሚገባ መራር እውነት ነው።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*