የምርጫው ጦስ…

2010ሩ የኢሕአዴግ ስንጥቃት ራሱን እንደ ዐዲስ ያዋለደው ብልፅግና ፓርቲ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ የጉዳት መጠኑ ቢለያይም፤ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል የሰላማዊ ዜጎች ግድያ እና ማፈናቀሎች የዘውትር ተግባር ሆኖ መቀጠሉ ይታወቃል። ይህ አደገኛ ሁኔታ ቀስ በቀስ ወደ መሀል አዲስ አበባ እየተስፋፉ መጥቷል። የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን በግፍ መገደል ተከትሎ፣ ከአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ የኦሮሚያ ከተሞች የተሰባሰቡ ወጣቶች፣ በከተማው በተለያየ አካባቢ ረብሻ የመፍጠርና ንብረት የማውደም እንቅስቃሴ ማድረጋቸው ይታወሳል። ችግሩ በፍጥነት በቁጥጥር ስር ባይውል እና የከተማውም ነዋሪ ወደ አጻፋ ርምጃ ቢገባ ኖሮ፣ ሊፈጠር የሚችለው ቀውስ የካፋ ይሆን እንደነበረ ለመገመት አይቸግርም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ብልፅግና ምርጫውን አስታክኮ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይ የሚያደርገው ተጽእኖ፤ እና አዲስ አበበን ለአንድ ብሔር ርስተ-ጉልት ለማድረግ የሚያራምደው የሴራ ፖለቲካ ለውጥረቱ ጫፍ መርገጥ እንደ ምክንያት ይጠቀሳል። ነገሩን ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆን ሊያደርገው የሚችለው ደግሞ፣ ይህ ዐይነቱ የፖለቲካ ስህተት በራሱ በብልፅግና አባል ፓርቲዎች እና በኦሮሚያ ብልፅግና መሀል ከፍተኛ መፋጠጥና ጥርጣሬን የማንበር ምልክቶች እያሳየ መሆኑ ነው። የድምጽ መስጫው ቀን እየተቃረበ ሲመጣ፣ በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚያስደፍር መልኩ፣ ገዥው ፓርቲ ወደ ማፋፈሩ ሲያዘነብል፤ በአንዳድ አከባቢዎች ደግሞ የኃይል እርምጃዎችን እስከመውሰድ ሲደርስ ታዝበናል።

በዚህ ዐውድ፣ በዋንኛነት ለማስታወስ የተፈለገው ከሳምንት በኋላ የሚካሄደው አገር ዐቀፉን ምርጫ ተከትሎ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ላይ ስጋት እያሳደሩ መሆኑን ነው።

ከዚህ አኳያም፣ ይህንን እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የተመረኮዙ ጥያቄዎችን ለተለያዩ የከተማው ነዋሪዎች ተዟዙራ ያቀረበችው “ፍትሕ መጽሔት”፣ ከአብዛኛው ነዋሪ ያገኘችው ምላሽ ስጋቱ ስር-ሰደድ መሆኑን ይጠቁማል። በርግጥ፣ ይህ ስጋት ከባዶ ሜዳ የመጣ እንዳልሆነም ተገንዝባለች። ቃለ-መጠይቅ ከተደረገላቸው ግለሰቦች መሃል ቤተሰቦቻቸውን ከአዲስ አበባ ውጭ ያሸሹ እና ‹ቀጣዩ ጊዜ አያስተማምንም› በሚል ከወትሮ የተለየ የምግብ ሸቀጦችን ገዝተው ያስቀመጡ እንዳሉም ለማወቅ ተችሏል።

አብዛኛው አስተያየት ሰጪዎች ‹ሊፈጠር ይችላል› ብለው ከሰጉት ብጥብጥ የበለጠ ፍርሃት ያሳደረባቸው፣ ባለፉት ሦስት ዐመት መንግሥት ግጭቶችን እና የፀረ- ሰላም ኃይሎችን እንቅስቃሴ በቅጡ መቆጣጠር የተሳነው እና ዐቅመ-ቢስ ከመሆኑ ጋር እንደሚያያዝ ተናግረዋል። በአንዳንድ ክልሎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ከተፈጸሙ ጥቃቶች ጀርባ፣ በመንግሥት የተለያየ መዋቅር ላይ ያሉ ሹማምንቶች መሳተፋቸውም፣ ሁኔታውን በጥንቃቄና በፍርሃት እንዲከታተሉ እንዳስገደዳቸው ገልጸዋል። ከምርጫው ጋር ተያይዞ ሊሰራጩ የሚችሉ የሃሰት ወሬዎችም የእርስ በርስ ግጭቶች እንዲፈጠር የወዲያውኑ ምክንያት የሚሆኑበት ክፍተት ሰፊ መሆኑ ፍርሃት እንዳሳደረባቸው አልሸሸጉም።

ከሁለትና ሦስት ዐመት በላይ፣ የፖለቲካ ፍላጎታቸውን በኃይል ለማሳካት ሲያደቡ የነበሩ ቡድኖች፣ በተለይ ደግሞ በመንግሥታዊው መዋቀር ላይ “አምስተኛ ረድፎች”ን የሰገሰጉት የከፋ አደጋ ሊያደርሱ የሚችሉበት እድል አለ። አገሪቱን ለ27 ዐመት በብረት መዳፉ ቀጥቅጦ የገዛው ሕወሓት፣ በማዕከላዊ መንግሥቱ ላይ ከነበረው የበላይነት ከተወገደ በኋላ፣ ለተለያዩ የጥፋት ቡድኖች ስምሪት እየሰጠ ከፍተኛ አደጋ ሲያደርስ ቆይቷል። በመጨረሻም፣ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ ድንገተኛ ጥቃት ሲከፍት፣ በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ በተለያየ ኃላፊነት ላይ ያሉ ተባባሪዎቹ መንግሥታዊውን መዋቅር ተጠቅመው የፈጸሙት ብሔራዊ ክህደት፣ ለደረሰው ጉዳት ትልቅ ድርሻ እንዳለው የእነ ጄነራል ፍቃዱ ገ/መድህን (ወዲ ነጮ) የክስ መዘገብ ያስረግጣል።

እናም፣ በተለይ አዲስ አበባ የፖለቲካው የስበት ማዕከል ከመሆኗ እና በ“ባለቤትነት” ጥያቄ ከማነታረኳ አንጻር፣ የፀጥታው መዋቅር እጅግ ጥብቅ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ይመከራል። መንግሥት ራሱ ባመነው እንኳ፣ “ኦነግ ሸኔ” ከሚባለው የጥፋት ቡድን ጋር እንደሚተባበሩ የተደረሰባቸው አንዳድ የኦሮሚያ ብልጽግና አመራርና አባላት መኖራቸው ይታወቃል። ከዚህ አንጻርም፣ አደጋውን ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ከተከሰተ በኋላ በቁጥርር ስር ለማዋል አስቸጋሪ እንደሚሆን ታሳቢ ያደረገ ጥበቃና ጥንቃቄ ይስፈልጋል።

በጥቅሉ፣ አዲስ አበባንም ሆነ ሌላውን የአገሪቱ ክፍል በምርጫው ጦስ ከሚመጣ እልቂት የመከላከሉ ኃላፊነት ከመንግሥት በተጨማሪ፤ የሁሉም ዜጋ እንደሆነ ለማስታወስ እንወዳለን።

ለውጥ በምርጫ ካርድ ብቻ! የዕለቱ ምልዕክታችን ነው።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*