የሥርዐት አልበኝነት ዘመን

ትዮጵያም ሆነች ሌሎች የዓለም አገራት በተለያየ ጊዜ ሀገረ-መንግሥታቸውን የሚንዱ አደጋዎች እና የሕግ የበላይነትን የሚጥሱ ሥርዐት-አልበኝትን አስተናግደዋል። የችግሩ ክፋት ግን እንዲህ ዐይነት መንገራገጮች መፈጠራቸው ሳይሆን፤ በፍጥነት ተቆጣጥሮ የአገርን አንድነትና የሕዝብን ሰላም የማስከበር ፍላጎቱም ዐቅሙም ሳይኖር ሲቀር ነው።

አገሪቱ፣ በታሪኳ “ዘመነ-መሳፍንት” እየተባለ የሚጠራውን ማዕከላዊ መንግሥቱ ተዳክሞ፣ የጎበዝ አለቆች (የጦር አበጋዞች) አካባቢያዊ “ንጉሥ” በሆኑበት አስቸጋሪ ወቅቶች ማለፏ ይታወቃል። የተፈጠረውን ክስተት በጊዜ መቆጣጠር ባለመቻሉም፣ እ.ኤ.አ ከ1769- 1855 ድረስ በሕገ-ወጦችና በሥርዐት-አልበኞች መዳፍ ሥር ወድቃ ብዙ ማቅቃለች። ካሳ ኃይሉ (በኋላ ዳግማዊ ቴዎድሮስ) የአካባቢ ገዥዎችን በጦርነት አሸንፈው ኢትዮጵያን አንድ እስኪያደርጉ ድረስ፣ ከ80 ዐመት በላይ የፈረሰች አገር ሆና ቆይታለች።

ይህ ከሆነ ከ120 ዐመት በኋላ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ወርደው፣ ደርግ ሥልጣን በጨበጠ ማግስት ተመሳሳይ ክስተት ተፈጥሮ ነበር። ይሁንና ቤተ-መንግሥቱን የያዘው ወታደራዊ ቡድን ሁሉንም ታጣቂዎች አንበርክኮ አምባገነናዊ ሥርዐት ቢያነብርም ቅሉ፤ ኢትዮጵያን ማስቀጥል ግን አልተሳነውም። እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጥሬ ሃቅ፣ በወቅቱ አገሪቱን በብሔር-ተኮር አጀንዳ ለመበታተን ብረት-ከነከሱ ቡድኖች ውስጥ፣ ዛሬም ለሰላምና አንድነት ጠንቅ ሆነው የተሰለፉት ኦነግ እና ሕወሓት ዋንኞች የነበሩ መሆኑ ነው። እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ለንፁሃን ሞት እና ለሕዝቦች መስተጋብር የግማሽ ክፍል ዘመን ዕዳ ሆነው መቀጠላቸው ደግሞ የአደገኝነታቸው መገለጫ ነው።

በተለይ “ኦነግ-ሸኔ” በሚል ስም የሚጠራው ቡድን፣ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ የዐማራ ብሔር ተወላጆችን በግፍ የመጨፍጨፊያ ሰብብ ከሆነ ሦስተኛ ዐመቱን ደፍኗል። ከቡድኑ ጀርባ፣ ከኦሮሚያ ክልል በተጨማሪ፤ የፌደራል መንግሥቱን ቁልፍ ሥልጣን የተቆጣጠሩ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ልሂቃን እጅ እንዳለበት በስፋት ይነገራል። አንድ ሁለቴም መንግሥት ራሱ ውንጀላውን አመኖ በአደባባይ መግለጫ ሰጥቷል። ለማሳያም ‹ከአንድ ሺሕ በላይ የኦሮሚያ ፖሊሶች ከኦነግ-ሸኔ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ስለተደረሰበት አባርረናል!› የተባለውን ማስታወስ ይቻላል።

በኦሮሚያ ክልል፣ የዐማራ ተወላጆችን የጥቃት ዒላማ ያደረግ የዘር ማፅዳት ወንጀል የሚፈጸመው በታጠቁ ቡድኖች ብቻ አይደለም። በወጣቶችም ጭምር ነው። አቶ ጃዋር መሐመድ በመንግሥት ኃይል እንደተከበበ በፌስቡክ ገጹ መናገሩን ተከትሎ፣ ከ86 በላይ ዜጎች በማንነታቸው በግፍ ተጨፍጭፈዋል። አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳም አዲስ አበባ ላይ የመገደሉ ዜና በተሰማ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ፣ በኦሮሚያ ክልል የዐማራ ተወላጆች ተመርጠው ተጨፍጭፈዋል፤ በቢሊዮን የሚቆጠር ንብረታቸው ወድሟል። አርቲስቱን የገደለው ኦነግ- ሸኔ እንደሆነ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ጭምር መነገሩ፣ ንፁሃን ዜጎችን ከጥቃት አለመታደጉ ደግሞ፤ በዘር ማጽዳት ወንጀሉ ላይ መንግሥታዊው መዋቅር እና የጫካው ኃይል ተናበው የመሥራታቸው ምልክት ነው።

ክልሉ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ የልዩ ኃይል አባላትን ደጋግሞ ማሰልጠኑን ይዘን፤ ኦሮሚያን በየቀኑ የንፁሃን ደም መፍሰሻ ከመሆን አለመታደጉ ጋር ስንደምረው፣ መከራከሪያውን ይበልጥ ያጠናክረዋል።

በጥቅሉ አገሪቱ በኦሮሞ ፖለቲከኛ እና ልሂቃን የበላይነት መዳፍ ከገባችበት ጊዜ ጀምሮ “ኢትዮጵያ አትፈርስም” የሚል አፋዊነት ቢነግሥም፤ የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸው ተርታ ዜጎች በማንነታቸው ብቻ የጥቃት ዒላማ መሆናቸው ንሯል። አደጋው ወደ አገሪቱ መዲናም እየተዛመተ ይመስላል። አዲስ አበባ “ያልታወቁ ሰዎች”፣ የሚታወቁ ሰዎችን ገድለው ወይም ደብድበው የሚሰወሩበት ከተማ እየሆነች ነው። ድርጊቱን አስደንጋጭ የሚያደረገው ደግሞ የመንግሥት ጭንቀት ከሟቾቹ ይልቅ፤ ወንጀሉን በአጋጣሚ የተፈጠረ ወይም ተራ ዕለታዊ ግጭት ማስመስል ላይ መሆኑ ነው። ይህንንም፣ በቀጥታና በዘወርዋራ በሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች እና ዳረጎት በሚሰፈርላቸው “አክቲቪስቶች” ሲያስተባብል ደጋግመን ታዝበናል። በቅርቡ “ባልታወቁ ሰዎች” የተገደለው የቴዎድሮስ አበባው (“ቴዎድሮስ ቡናማው”) ዜና-ህልፈት መነጋገሪያ ሲሆን፤ ከሴት ጓደኛው ጋር “ሰይፉ በኢቢኤስ” ላይ የቀረበው ወጣት ወንጀሉን ለማቃለል መሞከሩን መጠቀስ ይቻላል። በፕሮግራሙ እንደተመለከትነው አዘጋጁ እድሉን ያመቻቸው “ጓደኛው ነኝ” ያለው ወጣት ላስተላለፈው መልዕክት እንጂ፤ የሟቹ እጮኛ ለተናገረችው እንዳልሆነ በግልጽ ታዝበናል።

ሰሞኑን ባልታወቁ ሰዎች፣ ያውም በአምፑላስ ታፍነው የተደበደቡት አክቲቪስት ስዩም ተሾመ እና ሙክታሮቪች ኡስማኖቪች ላይ የደረሰው አደጋም፣ አገሪቱ በሥርዐት- አልበኞች ቁጥጥር ስር ለመዋሉ ዋንኛ ማሳያ ነው። እኒህ ሁለት የማኀበረሰብ አንቂዎች ‘የአገር አንድነትን እና የሕዝብን ሰላም ያስረግጣል’ ብለው ያመኑበትን ሃሳብ ፊት-ለፊት ሲገልጹ ቆይተዋል። ከዚህ አኳያም የደረሰባቸው ጥቃት የግለሰቦቹ ብቻ ተደርጎ ካለመወሰዱ በዘለለ፤ ሁለት ነገሮችን አመላክቷል። የመጀመሪያው፣ ሃሳብን የመግለጽ መብት ከባድ አደጋ ላይ መውደቁን ሲሆን፤ ሁለተኛው፣ አገሪቱ ላይ የነገሠው ሥርዐት- አልበኝነት ጫፍ መውጣቱን ነው። ይህ ዜጎች ፍትሕን፣ ከፍርድ ደጃፎች ይልቅ፤ በሰይፍ ለማግኘት እንዲነሳሱ የሚጋብዝ ክፉ ትምህርት ነው።

‹አገር ፈረሰ› የሚባለውም ሰለማዊ ዜጎች በአደባባይ የጥቃት ሰለባ ሲሆኑ፣ በታጠቁ ቡድኖች ተደጋጋሚ ጭፍጨፋ ሲፈጸምባቸው፣ ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ሲደረግና የመሳሰሉት ወንጀሎች ሲከሰቱ እንጂ፤ ተራራ ሲናድ ወይም ጫካ ሲመነጠር አይደለም። ስለዚህም፣ መንግሥት አደጋውን ለመረዳትም ሆነ ለመፍታት ከማይፈልግበት ሱባኤው ወጥቶና ነባሩን የሀገረ- መንግሥቱን ፒላሮች ተንተርሶ ሕግ ማስከበር ግዴታው እንደሆነ ለማስታወስ እንወዳለን። ሁኔታዎች በዚሁ ከቀጠሉ የተቋመጠለት ሥልጣን ጭምር፣ ከእጅ ሊወጣ የሚችለበት አጋጣሚ ቅርብ እንደሆነ “ፍትሕ መጽሔት” ታስገነዝባለች።

1 Comment

  1. ተመስገን ደሳለኝ በድምፃችን ይሰማ ግዜ ብዙ ትፅህፍ ነበር ለአብነት ያክል መጅሊሱና ሲኖዶሱ እና ሌሎቹም አንተም በግልፅ እንደምታውቀው የአብይ መንግስት በተቋሞች ላይ ግልፅ ጣልቃ ገብነት ያከናወነበትን እንቅስቃሴ ባሳለፍነው ሳምንት በሙስሊም የጠቅላላ ጉባኤ ተወካዩች ላይ በደህንነት ሹሙ በተመስገን ጥሩነህ አማካኝነት ግልፅ ማስፈራሪያወችን ስብሰባውን ለማደናቀፍና የታሰብበትን አላማ ለማሳት ከፍተኛ ጥረት አድርጎ በቦርድ አባላቶቹ ጥንካሬ በብዙ ውጣ ውረድ ስብሰባዎቹ ተከናውነዋል እንደዚህ ያሉ ጣልቃ ገብነቶችን አንተም ከስር መሰረቱ ስለምታውቅ ጉዳዩን እንዴት እንዳየኽውና የአንተን እይታ እንድታጋራንና የመንግስትን ጣልቃ ገብነት በሰላው ብእርህ አይበጅም እንድትልልን በአክብሮት እጠይቅሀለሁ የዘወትር አድናቂህና አክባሪህ ታደሰ ይመር ከአሜሪካን

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*