የረከሰው ጋብቻ

በኢትዮጵያ ሃይማኖት እና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸው በአዋጅ ከተደነገገ ግማሽ ክፍለ ዘመን ቢቆጠርም፤ በሕገ-አራዊት የሚመራው ፖለቲካ የረከሰ እጁን ከሃይማኖት ላይ ለአፍታም አንስቶት አያውቅም። በተለይ የድኅረ-83ቱ መንግሥት ከበረሃ ጀምሮ ሁለቱ ትልልቅ ሃይማኖቶችን መቆጣጠር፣ ለፍፁማዊ ሥልጣን ወሳኝ መሆኑን በማስላት፣ ፕሮግራም ቀርጾ መተግበሩ መሬት የረገጠ ሃቅ ነው።

የሕወሓት ስልት ዋንኛ ትኩረቱን ያደረገው ኦርቶዶክስ ክርስትናን ‹‹ጠላት›› ብሎ ከፈረጃቸው መደቦች ጋር ቀላቅሎ መታገል ሲሆን፤ እስልምናን ደግሞ በተበዳይ ትርክት አደናግሮ መጠቀሚያ ማድረግ ነው። ይሁንና፣ “ነፃ አውጪ”ው ድርጅት ብዙም ሳይቆይ፣ ከትግራይ ሕዝብ ‹ከ95 መቶ በላይ የሚሆን መእምናን አላት› ብሎ ያመነውን ቤተ-ክርስቲያን ከማውደም፤ በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ወደ መግራት ተሸጋግሯል። ለዚህም ማሳያው፣ የሕወሓት ወታደራዊ አዛዥ የነበሩት ዶ/ር አረጋዊ በርሄ ‹‹የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ፖለቲካዊ ታሪክ›› በሚል ርዕስ ባስነበቡት መጽሐፍ የገለፁት ነው፡-

‹‹ቀሳውስቱን ለመግራት ሲባል በ1971 ዓ.ም የተካሄደው ተከታታይ ኮንፈረንስ ነው። የዚህ መግፍኤም፣ የትግራይን ቤተ-ክርስቲያን፣ ከሰፊው የኢትዮጵያ ቤተ-ክርስቲያን ነጥሎ ከሕወሓት ስትራቴጂካዊ ግብ አኳያ፣ የትግራይ ብሔርተኝነት ማሳደጊያ ለማድረግ ነበረ። የተጨቆነው የትግራይ ብሔርተኝነትን ማነቃቃት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስቲያንን መገዳደሪያ መንገድ ነበር። ለቀሳውስቱ ሲሰጥ የነበረው ሴሚናር መጀመሪያ ይካሄድ የነበረው በአንደበተ ርትዑ የሕወሓት ተዋጊና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ-መለኮት ምሩቅ በነበረው ገብረኪዳን ደስታ አማካኝነት ነበር። የሴሚናሮቹ ጭብጦች የቤተ-ክርስቲያኗ ቋንቋ ትግርኛ በማድረግ የትግራይን ማንነት እና ብሔርተኝነት ማስፋፋት ነበር። ይህ ሂደትም የሰበካ ጉባኤያት ቀሳውስትን እና ተርታውን አማኝ ከብሔራዊው ተዋረዳዊ የዕዝ ሰንሰለት መነጠልን ያካተተ ነበረ። የቤተ-ክርስቲያኗን ሥልጣን ለማዳከም ሲባልም በስብሓት ነጋ የሚመራ የደኅንነት ቡድን የግንባሩን አባላት መነኩሴ አስመስሎ እንደ ደብረዳሞ ባሉ የአካባቢው ገዳማት አስርጎ በማስገባት፣ የቤተ-ክርስቲያኗን እንቅስቃሴ በሕወሓት ፍላጎት ስር እንዲሆን እስከማድረግ ተኪዷል። በ1971 እና 1981 ግን ነፃ በወጡት አካባቢዎች ያሉትን ቤተ-ክርስቲያናት በሕወሓት ፕሮግራም ለመግራት ሲባል፣ አካባቢያዊ ኮንፈረንሶች ለቀሳውስቱ ይሰጡ ነበር። በሕወሓት መሪዎች ስር የሚንቀሳቀስ የተነጠለ ጽሕፈት ቤትም በነፃዎቹ አካባቢዎች ተቋቋመ።››

ይህንን ሃሳብ፣ ሕወሓት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ፣ የክርስትናን ያህል ባይሆንም፤ እስልምናም ላይ ለመተግበር ተግቶ ሠርቷል። በተለይ የፌደራሉን መጅሊስ ለመቆጣጠር የሄደበት ርቀት የሕዝበ- ሙስሊሙን የዐደባባይ ተቃውሞ ቀስቅሷል።

የ2010ሩን ሕዝባዊ ንቅናቄ ተመርኩዞ ለሥልጣን የበቃው የኦሮሞ ፖለቲካም፣ የሕወሓትን መንገድ እየተከተለ ለመሆኑ አያሌ ማሳያዎች አሉ። በተለይ፣ የትግራዩ ድርጅት ወጥሮ የሠራበትን ብሔርተኝነትን እና ሃይማኖትን ቀላቅሎ የመጠቀም ስልቱን እንደ ወረደ ተቀብሎ እየፈጸመ ነው። በጠቅላይ ሚኒስትሩ አጋፋሪነት የተመሰረተው የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች በአዋጅ አንድ ካውንስል እንዲመሰርቱ መደረጉን ጨምሮ፤ በእስልምና እና በኦርቶዶክስ ላይ እጁን በስፋት መንከሩ መሬት የረገጠ ሃቅ ነው። በተለይ ሕወሓት በረሃ ላይ፣ የኦርቶዶክስ ቤተ-ክርስትያንን ለትግራይ ብሔርተኝነት ማቀጣጠያ እንደተጠቀመበት ሁሉ፤ ኦዴፓም ‹‹የኦሮሚያ ቤተ-ክርስትያን አደረጃለሁ›› የሚለውን አፈንጋጭ ቡድን ከጀርባ ሆኖ ስለመምራቱ በቂ ምልክቶች ታይተዋል። እንቅስቃሴው ከፊት መስመር በቄስ በላይ መኮንን የሚመራ ቢመስልም፤ አቡነ ሳውሮስ፣ አቡነ ሩፋኤል፣ አቡነ ያሬድ እና የመሳሰሉት የቅዱ ሲኖዶሱ አባላት፣ ያውም በቤተ-ክርስትያኗ መዋቅር፣ የኦሮሚያ ቤተ-ክርስትያንን ለማደራጀት ሳይታክቱ እየሠሩ እንደሆነ የሾለኩ ማስረጃዎች ያሳያሉ።

የኦሮሚያ ብልፅግና፣ ከላይ የተጠቀሰውን የሕወሓት ተሞክሮ በሙሉ ኃይል እየተተገበረ ለመሆኑ ሌላኛው ማሳያ ፓትርያርኩ አቡነ ማቲያስ በይፋ በመንግሥት አፈና ስር መሆናቸውን የተናገሩበት የቪዲዮ መልዕክት ነው። ከዚህ የበለጠ የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ማሳያ ሊኖር አያችልም።

አቡነ ማትያስ፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ከሆነችው ወይዘሮ ጊታ ፔቲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ምንም ዐይነት ሥራ እየሠሩ እንዳልሆነ እና የቤት ውስጥ እስረኛ መደረጋቸውን የገለፁበት ዐውድም፣ ከሃይማኖቱ ተከታዮች በዘለለ፤ ኢትዮጵያውያን ጨምሮ፣ የአገር ውስጥ እና የውጪ መብት ተሟጋች ድርጅቶችን ተቆርቋሪነት ይፈልጋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ በኦርቶዶክስ ክርስትና ልሂቃኖች የሚመራው “ማኅበረ ቅዱሳን” ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱን መጥቀሱ የችግሩን ስር-ሰደድነት ያስረግጣል።

“ፍትሕ መጽሔት” ቤተ-ክርስትያንን ለመበታተን በመንግሥት በኩል የሚደረገውን ጫናንም ሆነ ‹ሕዝበ- ሙስሊሙ የፌደራል መጅሊስን በነፃነት እንዳላቋቁም መንግሥት ጣልቃ ገብቶ አስቸገረኝ› ሲል ያሰማው የተቃውሞ ድምጽ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብላ ታምናለች። ፖለቲካው የረከሰ እጁን ከሃይማኖት ተቋማት ላይ እንዲያነሳ አጥብቃ ትጠይቃለች። የአገሪቱ ወሳኝ ባለሥልጣናትም የግላቸውን ሃይማኖት ወደ መንግሥታዊው መዋቅር በመለንቀጥ፣ የረከሰ ጋብቻ ለመፈጸም የሚደርጉትን ጥረት አምርራ ታወግዛለች።

አገር የጋራ ነው፣ ሃይማኖት የግል ነው!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*