
ሰሞኑን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በድንገት ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ፣ በክልሉ ሕዝብ መሀል የተለያዩ ግራ መገባቶች እና መደነጋገሮች በስፋት እየተስተዋለ እንደሆነ ይታወቃል። እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ገፊ- ምክንያት ተደርጎ የቀረበው ደግሞ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ ወቅቱ ክረምት ከመሆኑ አኳያ ‹አርሶ ዐደሩ ወደ እርሻው ተረጋግቶ እንዲሰመራ› በሚል የጠየቀውን የተናጥል የቶክስ አቁም ስምምነት በመቀበሉ እንደሆነ ሰኔ 21/2013 ዓ.ም ይፋ አድርጓል።
በርግጥ ከዚህ የመንግሥት መግለጫ ግማሽ ሰዓት ቀደም ብሎ፣ የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ፣ በዚሁ ዕለት ምሽት አንድ ሰዓት ሠራዊቱ በተቀዳጀው ወታደራዊ ድል መቀሌ እንዲገባ ትዕዛዝ መስጠቱን፣ በ“አፈ-ጉባኤ”ነት ሲያገለግሉት የነበሩ የውጭ ጋዜጠኞች ጭምር ሲያስተጋቡ እንደነበረ ታዝበናል።
እኒህ ሁለት የተለያዩ እና የተቃረኑ መረጃዎች፣ ከውሳኔው ድንገቴነት ጋር ተዳምረው ግራ መጋባት መፍጠራቸው የሚደንቅ ባይሆንም፤ ከዚያን በኋላ ባሉ ቀናትም ቢሆን፣ ሁሉንም በምልዓት ሊያስማማ የሚችል እውነት መሰማት አለመቻሉ በርካታ ጥያቄዎችን የሚያጭር ነው።
የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልል አስተዳደር ከሁለት ዐመት በላይ በንትርክ ቆይተው፣ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ሕወሓት ሰሜን እዝ እና የዐማራ ክልል አስተዳደር ላይ በተመሳሳይ ሰዓት የከፈተውን ያልታሰበ ጥቃት ተከትሎ፣ አካባቢው ሙሉ በሙሉ የጦርነት ቀጠና ወደ መሆን መቀየሩ ለዚህ ሁሉ ችግሮች ዋንኛው መንስኤ ነው።
ሕወሓት፣ ከባህር ዳር እና ጎንደር በተጨማሪ፤ የኤርትራን ዋና ከተማ አስመራን በሮኬት መደብደቡን ምክንያት ያደረገው የኤርትራ ሠራዊት፣ ድንበር ተሻግሮ በመግባት ከኢትዮጵያ ጦር እና ከዐማራ ልዩ ኃይል ጎን ተሰልፎ በውጊያው ለመሳተፈ የተገደደበት ሁኔታ መፈጠሩ ደግሞ ችግሩን አለቅጥ አንሮታል።
የሆነ ሆኖ በተዋጊዎቹ ላይ የሚደርሰው ሰዋዊ ጉዳት እንደተጠበቀ፤ አብዛኛው የዐውደ ውጊያ ሜዳ በትግራይ መሬቶች ላይ በመሆኑ፤ በሰላማዊ ዜጎች ላይ እስከ አሁን በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ጉዳት መድረሱን የተመለከቱ ሪፖርቶች እየወጡ መሆኑን፤ እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ አስገድዶ ደፈራ፣ ዘረፋዎች እና የመሳሰሉት ወንጀሎች በብዛት መከሰታቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች የዜና ሽፋን ሰጥተው የዘገቡት ጉዳይ ነው።
በትግራይ የተከሰተውን ችግር የከፋ የሚያደርገው ደግሞ አብዛኛው ሕዝብ የሴፍቲኔት ተጠቃሚ ከመሆኑ አኳያ፣ የምግብ እጥረት መፈጠሩ ሳይታለም የተፈታ መሆኑ ነው። በዚህ ላይ በአሁኑ ወቅት ክልሉን የተጠቆጣጠረው ኃይል ሕዝብን ሊቀልብ ቀርቶ፣ ራሱም የእርዳታ ስንዴ እየዘረፈ እዚህ መድረሱ ሲታሰብ፣ ነገሩ ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ የተጋነነ እልቂት፣ አስከፊ የምግብ እጥረት እና ሥርዐት-አልበኝነት ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ሰፊ እንደሆነ ይጠቁማል። ይህ ሁኔታም ከትግራይ አልፎ አጎራባች ክልሎችን እና ጎረቤት አገራትንም በተለየያ መንገድ የችግሩ ተጠቂ ሊያርግ ይችላል።
ለዚህም ነው፣ የፌደራል መንግሥቱ ‹ሕዝቡ ከወንበዴው ጋር አብሮ ከኋላ ስለወጋኝ ወጥቻለሁና፣ ከዚህ በኋላ እዛ ክልል የሚፈጠር ችግር አይመለከተኝም› ስላለ ብቻ፤ ‹እውነትም አይመለከተውም› ተብሎ የሚተው የማይሆነው። ምንም ተፈጠረ ምን፣ ትግራይ የአገሪቱ አካል እስከ ሆነች ድረስ በደንብ ሊመለከተው እንደሚችል ግልጽ ነው። እንዲህ ዐይነቱ ንግግርም የክልሉን ሕዝብ ባይተዋር ከማድረጉ በዘለለ፤ ወደ መነጠል የሚገፋ በመሆኑ፣ የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጡ አካላት በሚሰጧቸው መግለጫዎችም ሆነ በሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል።
በጥቅሉ የመከላከያ ሠራዊቱ ትግራይን ለቅቆ ከወጣ በኋላ፤ የሕወሓት ዐማጺ ኃይል ተተክቶ የተቆጣጠረው በመሆኑ ብቻ፣ የፌደራል መንግሥቱ ኃላፊነት የለበትም ማለት አይደለም።
“ፍትሕ መጽሔት” እዚህ ውሳኔ ላይ የተደረሰው አርሶ ዐደሩን ታሳቢ በማድረግ እስከ ሆነ ድረስ፣ የተፈለገው ዓላማ ግቡን ይመታ ዘንድ፣ የፌደራል መንግሥቱ አሁንም ሕዝባዊ ግዴታውን ከመወጣት ቸል ማለት እንደሌለበት አጽንኦት ሰጥታ ታሳስባለች።
Be the first to comment