የአገራዊ ስጋት ተግዳሮቶች | ርእስ አንቀጽ

ኢትዮጵያ ፖለቲካ ከቀን ወደ ቀን ከመሻሻል ይልቅ፤ እየደፈረሰ ነው። በየጊዜው ዐዳዲስ ችግሮችም እየተቀፈቀፉ፣ ነገሩን “ከድጡ ወደ ማጡ” አድርገውታል። መንግሥትም ችግሮችን ለመፍታት ከመጣር ይልቅ፤ ሲያወሳስበው ታዝበናል።

በርግጥ፣ ዛሬ አገሪቱ ለተጋፈጠቻቸው መከራዎች፡- ለ27 ዐመት ቢሮክራሲውን፣ ኢኮኖሚውን፣ የመከላከያ ሠራዊቱን፣ የደህንነት መስሪያ ቤቱን፣ የፌደራል ፖሊስን፣ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎችን እና የተለያዩ ወሳኝ ተቋማትን በብቸኝነት ተቆጣጥሮ የነበረው ሕወሓት ከሥልጣን ከተባረረ በኋላ፣ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ያበጀውን መዋቅር ተጠቅሞ የፈጸማቸው አሻጥሮች ዋንኛዎቹ ናቸው።

በብልፅግና ስም “አንድነት ፈጥረናል” ብለው የተሳበሰቡት ቡድኖች መሀል ያለው የፍላጎት አለመጣጣም እና ስግብግበነትም፣ ለችግሮቹ መናር ግዘፍ-የሚነሳ አስተዋጽኦ አድርጓል።

የኢሕአዴግ ስንጥቃትን ተንተርሶ የተፈጠረው የሥልጣን ክፍተትም ለችግሮቹ መባባስ የማናቅ አስተዋጽኦ እንዳለው መካድ አይቻልም።

ሕወሓት፣ ሰሜን ዕዝ ላይ በሰነዘረው አገር አፍራሽ ጥቃት የተቀሰቀሰው የትግራዩ ጦርነት ካደረሰው የከፋ ሰዋዊ እና ቁሳዊ ውድመት ሌላ፤ ዓለም ዐቀፍ አጀንዳ ሆኖ፣ የብሔራዊ አደጋ ስጋት ማንበሩ ደግሞ፣ ችግሮቹንና ልዩነቶቹን ወደ መጨረሻው ጫፍ እየለጠጠ ነው። ይህንን ተከትሎ፣ በንግድና በጥቅመኝነት መርሆች የተገሩት አሜሪካ እና ተቀጽላዎቿ በትግራይ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ለተፈጸሙ የሰበዓዊ መብት ጥሰቶች መፍትሔ ከመሆን ይልቅ፤ አጀንዳውን ተገን አድርገው የእብድ ገላጋይ ሚናን ወደ መምረጥ ማዘንበላቸው፣ መላ አገሪቱን ወደ ፍርሰት- ጠርዝ የመግፋት ሂደቱን አጠናክሮታል።

ሦስት ዐሥርታት ያስቆጠረው ዘር-ተኮር ፌደራሊዝም ተዛብቶ የተተገበረበት ዐውድም፣ ለሕዝባዊው መንፈራቀቁ ትልቅ ድርሻ አለው። ኢትዮጵያውያን እንደ ዜጋ ከመተማመን ይለቅ፤ በጠላትነትና በጥርጣሬ እንዲተያዩ አድርጓል። በ“ቀበሮ ሽንት” በተከለሉ “ድንበሮች” ለእርስ- በርስ ግጭት ቢላ መሳሳል ከጀመሩም ይሰንብቱ ዘንድ አስገድዷል።

ከሦስት ሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የሚካሄደው አገር ዐቀፉ ምርጫም እንደ አጀማመሩ ሁሉ፣ አጨራረሱም በውዝግብ የሚታጀብ ይመስላል። ከቀን ወደ ቀን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆኑ መራጩ ሕዝብ ሂደቱን በበላይነት በሚመራው ቦርድ ላይ ያሳደረውን እምነት የሚሸረሽሩ ጉዳዮች በስፋት እየታዩ ነው። ይህ ከስተት፣ የትኛውን ሰይጠን እንደሚቀሰቅሰው ባይታወቅም ቅሉ፤ አገሪቱ ከምትጋፈጣቸው ፈተናዎች ዋንኛው መሆኑ አይቀሬ ነው።

ኢኮኖሚያው ድቀቱ እና ማባሪያ ያጣው የዋጋ ጭማሪም አገሪቱን ወደ ትርምስና ሥርዐት-አልበኝነት ከሚገፉ ችግሮች ግዘፍ-የሚነሱ ናቸው። በትግራይ፣ ከትግራይ እና ከሱዳን በሚዋሰኑ የዐማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች፣ በሰሜን ሸዋ፣ በመተከል፣ በወለጋ እና በመሳሰሉት የአገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው የሰላም መደፍረስ፣ አርሶ ዐደሩን ከሥራ ውጪ ከማድረጉ በዘለለ፤ የንግድ እንቅስቃሴውን ገትቶታል። ይህም፣ ድህነትን፣ ሥራ-አጥነትን እና የወደቀውን ኢኮኖሚ ይበልጥ አድቅቆ ፈተናውን ያከብደዋል።

ዓለም ዐቀፉ የኮሮና ወረርሽም በአገሪቱ ላይ የፈጠረው ሁለንተናዊ ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

ጎረቤት አገር ሱዳን፣ የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ የፈጸመችው ወረራም ሆነ ከህዳሴ ግድብ ጋር በተያያዘ፣ ከግብፅ ጋር የፈጠሩት ፀረ-ኢትዮጵያ ጥምረት፣ በቀላሉ የሚታለፍ አይደለም።

የአገሪቱ ታሪካዊ ጠላት የሆነችው ግብፅ፣ ከኬኒያ ጋር የፈጸመችው ሰሞነኛ ወታደራዊ ስምምነትም፣ ኢትዮጵያንም ሆነ ቀጠናውን ስጋት ላይ የሚጥል እንደሆነ ግለጽ ነው። እነዚህ የውጭ አገራት ትንኮሰዎች እና ተጨባጭ እንቅስቃሴዎች ደግሞ ሕወሓትን ጨምሮ፤ በተለያየ የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱ ዐማጺያን እልል በቅምጤ ናቸው።

በአጠቃላይ ወቅቱ ኢትዮጵያ፣ ከሁለተኛው የጣሊያን ወረራ በኋላ፣ ከውስጥም ከውጪም ከባድ ፈተና ፊት የቆመችበት ሆኗል።

ይህም ሆኖ፣ የፌደራሉን እና የክልል መንግሥታትን ሥልጣን የጨበጠው ብልፅግና የተፈጠሩትን ችግሮች የሚመጥን የመፍትሔ አመራጭ ማምጣት ተስኖታል። የተደቀኑትን ስጋቶችም ሊቀርፍ የሚችል አቅጣጫ የመቀመር ዐቅሙም ሆነ ፍላጎቱ ያለው አይመስልም። የፓርቲው ዋንኛ ትኩረት፣ ቀጣዮቹን አምስት ዐመት በሥልጣን ለመቆየት፣ ምርጫውን በባሌም በቦሌም ማሸነፍ ላይ ብቻ ሆኗል። በዚህ ሁሉ ምስቅልቅሎሽ ውስጥ አዲስ አበባን በኦሮሙሟ የማጠመቅ ሩጫውንም አጥብቆ ይዞታል። “ሕገ-መንግሥት በጠረባ” የሆነው “የፊንፊኔ ፍርድ ቤት” መቋቋም ዋንኛው ማሳያ ነው።

“ፍትሕ መጽሔት”፣ ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ በላይ፣ በከፋ ሁኔታ የተጋረጡባትን ውጫዊ ስጋቶች በጥበብ ለማለፍ፣ በቅድሚያ በውስጥ ለተከሰቱ ግጭቶችና አለመግባበቶች የፖለቲካ መፍትሔ መስጠት ያለባት መሆኑ ብቸኛው አመራጭ እንደሆነ በጽኑ ታምናለች። የትኛውም አገር፣ የውጭ ጠላቶች ሊበረቱበት የሚችሉት፣ በውስጥ ጉዳይ ሲዳከምና ሲከፋፈል እንደሆነ ይታወቃል። በዛሪይቷ ኢትዮጵያ ደግሞ፣ ሁለቱም ችግሮች ክሱት ሆነዋል። እናም፣ ገዥው ፓርቲ ከምርጫው ጎን ለጎን ሁሉንም ወገን ሊያስማማ የሚችል ፍኖተ-ካርታ ሊዘጋጅ የሚችልበትን ዕድል መፍጠር ቀዳሚ የቤት ሥራው እንደሆነ ለማስታወስ እንወዳለን።

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*