
ሕወሓት፣ ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የበዛ የሰው ኃይል እና መሳሪያ የታጠቀውን ሰሜን ዕዝን ለመደምሰስ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ የተቀሰቀሰው ጦርነት፣ መልክና ቅርፁን እየቀያየረ ቀጥሏል። ለዚህ ደግሞ ዋንኛ መነሾ የሆኑት፣ ከውጊያው ግንባር የሚወጡ መረጃዎች፣ በንፁሃን ላይ የደረሱ እልቂቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የተመለከቱ ጉዳዮች፣ አራምባና ቆቦ መሆናቸው ነው። ይህ ሁኔታ፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘለለ፤ ዓለም ዐቀፍ ማኀበረሰቡም ተደናግሮ፣ የተሳሳተ አቋም እንዲይዝ ገፊ-ምክንያት ሆኗል።
እንዲህ ዐይነት ጉዳዮችን የማረቅና ትክክለኛውን መረጃ በመስጠት፣ የተዛባውን የማረም ትልቁ ግዳጅ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መሆኑ እሙን ነው። ይሁንና፣ ተቋሙ አሁን ባለበት ደረጃ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያስችለው ቁመና ላይ አለመሆኑ፣ ልክርክር የሚቀርብ አይደለም።
ኢትዮጵያ፣ በዓለም መድረክ ሃቅን ይዘው፣ ከኃያላኖቹ ፊት በአሸናፊነት እንድትቆም ያደረጉ እነ አክሊሉ ሀብተወልድ፣ ከተማ ይፍሩ፣ ሚናስ ኃይሌ፣ ብርሃኑ ድንቄን… በመሳሳሉ ታላላቅ ሰዎች የተወከለችበት ዘመን፣ በአልቦ-ተተኪ ወደ ታሪክነት ተቀይሯል።
በደርግ መንግሥትም ጎሹ ወልዴን እና ክፍሌ ወዳጆን በመሳሰሉ ሰዎች ተወክሎ ስኬታማ ሥራ መሥራቱ አይዘነጋም።
የበረህኞች ስብስብ ኢሕአዴግም ቢሆን፣ ለተቋሙ የሚመጥን ሚንስትር የመመደብ ፍላጎት ባይኖረውም፤ ዐቅምና ልምድ ያላቸውን እነ ተቀዳ አለሙ፣ ቆንጂት ስነ ጊዮርጊስ፣ ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ምንሊክ አለሙን የመሳሰሉ ባለ-ሙያዎችን በመጠቀም፣ ውጤታማ መሆን መቻሉ የቅርብ ትውሳታችን ነው። ሌላው ቀርቶ፣ የኢትዮ-ኤርትራን የድንበር ግጭት የተመለከተው ዓለም ዐቀፉ የድንበር ግልግል ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ ላለመተግበር በያዘው አቋም ፀንቶ መቀጠሉም ሆነ ኤርትራን ከዓለም ማኀበረሰብ ነጥሎ ማዳከም መቻሉ፣ የዲፕሎማሲው ስኬት ማሳያ ነው።
ከ2010ሩ ለውጥ በኋላ በውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት ተሾመው የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው አንድም ተጠቃሽ ሥራ ሳይሠሩ፣ የጦርነቱን መጀመር ተከትሎ በድንገት ተሽረዋል። አስገራሚው ደግሞ፣ ከቦታቸው ስለመነሳታቸውን የሚያውቁት ነገር አለመኖሩ ነው። ገዱ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ላለመወጣታቸው ገፊ- ምክንያቶች ተብለው ሊጠቀሱ ከሚችሉት ውስጥ፣ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የመስሪያ ቤቱን ሥልጣን የመደረባቸው ፍላጎት እና ዘር-ተኮር የምደባ ሽሚያ ከፊት ይቀድማሉ። ይህ ሁኔታ ተቋሙን ምን ያህል እንዳዳከመው ያጋለጠው ደግሞ የጦርነቱ መጀመር ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በእነ ቴዎድሮስ አዳህኖም፣ ማህሪ ታደለ ማሩ፣ ሰናይት ፍሰሃ፣ ስዬ አብራሃ እና በመሳሰሉት በሚመራው የሕወሓት የውጭ ግንኙነት፣ በዓለም ፊት ተበልጦ ለትዝብት ተዳርጓል። ከተባበሩት መንግሥታት እስከ ቡፌት እና ጌትስ ፋውንዴሽ ጀምሮ፣ አያሌ ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን በማሳሳት፣ በመጠምዘዝና በወሳኝ ኃላፊነት የተቀመጡ ግለሰቦችን በመግዛት፣ ኢትዮጵያን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት ወጥሮ መሥራቱ ተሳክቶላቸዋል። ዓለም ዐቀፍ ሚዲያዎችንም የድምጸ- ወያኔን ያህል ተቆጣጥረው ከእውነታው ያፈነገጡ ዘገባዎችን ለማሰራጨት አልተቸገሩም።
እዚህ ጋ የሚነሳው ዋንኛ ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በዚህ ደረጃ ሲሸነፉ፣ ያ ሁሉ ዲፕሎማት የት ነበረ? የሚል ነው። ለጥያቄው አጥጋቢ ምላሽ መስጠት እስካልተቻለ ድረስም፣ ተቋሙን ከተዘረረበት ‹ሪንግ› አውጥቶ፣ የአገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም አስከባሪ ማድረጉ አዳጋች እንደሆነ መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
ጦርነቱ በተጀመረ ማግስት በአቶ ገዱ የተተኩት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ደመቀ መኮንን ይህንን መስቀል የመሸከም ትልቅ ኃላፊነት እንደወደቀባቸው አይዘነጉም ተብሎ ይታመናል። ለዚህ ደግሞ ቀዳሚው የቤት ሥራ በብሔር ኮታ የተሞላውን ተቋም እንደገና በባለሙያ ማደረጃት ነው። ከዚህ ጎን ለጎንም፣ የአማካሪዎች ቡድን አዋቅሮ፣ የሚሰጣቸውን ምክል በአግባቡ የመተግበር ቁርጠኝነት ይጠበቅባቸዋል። ምናልባትም፣ ከበቂ በላይ ልምድ እያላቸው በጡረታም ሆነ በተለያየ ሰበብ ከኃላፊነታቸው የተነሱ ባለሙያዎችን ወደ ቦታቸው መልሶ መጠቀሙ፣ የአጭር ጊዜ አዋጭ መፍትሄ ሊሆን ይችላል። ግልፅና የተብራራ ስትራቴጂ ነድፎ መንቀሳቀስም የሥራው መጀመሪያ ነው። ዛሬ የገጠመንን ዐይነት አገራዊ ጉዳዮች ሲፈጠሩ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥባቸው በጥናት ተዘጋጅተው የተቀመጡ አቅጣጫዎች መኖራቸው የግድ እንደሆነም አለመርሳቱ ይመከራል።
በሌላ በኩል፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ሥልጣን የጨበጠው የብልፅግና ፓርቲ ሸሪክ የሆነው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የተሳሳቱ መረጃዎችን ለአፈንጋጩ የሕወሓት የዲፕሎማሲ ቡድን በግልፅም በስውረም ከሚያሰራጭበት የአገር ክህደት ተግባሩ እንዲታቀብ ማድረጉ ተገቢ ነው። እንዲሁም ከትላንት በስቲያ የክልሉ የአስቸኳያ ጊዜ አዋጅ ዋና ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ሌ/ጄ ዮሃንስ ገ/መስቀል በቅርብ ጓደኞቻቸውና ዘመዶቻቸው በሚመራው የሕወሓት ሽምቅ ተዋጊ ላይ ጨክነው ‹እርምጃ ይወስዳሉ› ብሎ ማሰብ፣ በተከፈለው መስዋትነት ላይ መሳለቅ ነው። መንግሥት፣ ጄነራሉን በዚህ ዐይነቱ ከባድ ኃላፊነት ላይ ማስቀመጡ፣ የመታነቂያ ገመዱን በገዛ ፍቃዱ ማቀበል መሆኑን በማስታወስ፣ ስህተቱን በፍጥነት እንዲያርም አበክረን እንጠይቃለን። በነገራችን ላይ፣ ለረጅም ጊዜ የመከላከያ መረጃ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ጄነራል ዮሀንስ፣ ባለፉት ሃያ ሰባት ዐመት ሕወሓት የፈፀመውን ወንጀል በሙሉ የሚጋሩና በሕግ የሚያስጠይቃቸው መረጃዎች እንዳሉ ይታወቃል። በተቀረ፣ “የአገሩን ሰርዶ፣ በአገሩ በሬ!” ዐይነቱ ቁማር ለሕወሓት ሰዎች ሠርቶ አለማወቁን፣ ከድርጅቱ የ46 ዐመት ታሪክ መረዳት ብልህነት ነው።
በመጨረሻም፣ ያንኪዎችም ሆኑ እንግሊዝ እና ተቀጥላ አገራቶች አንድም ከሕወሓት-መራሹ መንግሥት ጋር በነበራቸው የጥቅም ትስስር፣ ሁለትም በኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ሰዎቻቸው በገንዘብ እየተደለሉ፣ ሉዓላዊነትን በግላጭ የሚንድ ትዕዛዝ ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡም ሆነ ኢትዮጵያን እና ሕዝቧን እንዲያከብሩ ማስገደድ የሚቻለው፣ በዲፕሎማሲው መስክ ጠንክሮ በመሥራት ብቻ ነው።
በዕርዳታ የበለፀገ አገር እንደሌለው ሁሉ፣ ዕርዳታ ባለማግኘቱ ከምድረ-ገጽ የጠፋ አገር የለም። የትኛውም ማባበያ፣ የትኛውም ዐይነት ማዕቀብና ማስፈራሪያ ከሉዓላዊነት አይበልጥም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!
Be the first to comment