
በዓባይ ጉዳይ ላይ ዋጋ እንዳንከፍል መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ታሪካዊው አደራ አንዴ ከእጃችን ከወጣ ድጋሚ አናገኘውም። የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የመጣበት መንገድ አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ እንድንገባ አድርጎናል። በጉዳዩ ላይ ከባለሞያዎች ጋር በቂ ምክክር አለማድረግ፣ ከቴክኒክ ኃላፊዎች ይልቅ ፖለቲከኞች በግድቡ ዙሪያ ብቸኛ ወሳኝ መሆናቸው፣ በግብፅ ጋባዥነት አሜሪካ ወደ አደራዳሪነት ስትገባ በቸልተኝነት መፈቀዱ፣ ለሶስተኛ ወገን የመስማሚያ ሀሳብ እጅ መሰጠቱ፣ ገንዘብ አበዳሪ ሀገራትና ተቋማትን ላለማስቀየም የሚደረግ ከልክ ያለፈ ትዕግስተኝነት… ወዘተ በዓባይ ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ ባለው ድርድር ላይ የታዩ ችግሮቻችን ናቸው። የተዘረዘሩት መንግሥታዊ ስህተቶች ብሔራዊ ምልክት እየሆነ የመጣውን ግድብ እንዳያሳጣን ያሰጋናል።
ግብፆች በየጊዜው አዳዲስ የመደራደሪያ ሃሳብ እያመጡ ማደናገር የለመዱት ነው። ከዚህ ቀደም በ1929ኙ እና በ1959ኙ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበት የቅኝ ግዛት ውል ካልተዳደርን የሚል መከራከሪያ ነበራቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህን ሙግት ዘንግተው የውሃ ሙሌቱ ጊዜ መራዘምንና የድርቅ ጊዜ ማካካሻን የሚመለከት የሚል አዲስ የድርድር ነጥብ ይዘው መጥተዋል። ይህ ብቻም አይደለም። ከዚህ ቀደም፣ በሦስቱ የተፋሰሱ ሀገራት ማለትም በግብፅ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ውይይት ብቻ እንዲደረግ በጋራ የተስማሙበትን ውል አፍርሰው አሜሪካና ዓለም ባንክ አደራዳሪ እንዲሆኑ ግብፅ ያቀረበችው ሀሳብ ተቀባይነት አግኝቷል። ይህ ሲሆን እኛ መፍቀዳችን የኋላ ኋላ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ከትቶናል። ዲፕሎማሲያዊ ኪሳራ ይዞብን እንደሚመጣ ከወዲሁ መገመት እምብዛም አይከብድም። ከዚህ ለመውጣት ፖለቲካዊ ብልሀት ይጠይቃል። ጥልቅ የቴክኒክ ዕውቀት ያላቸውን ባለሞያዎች የጉዳዩ ባለቤት እንዲሆኑ ማድረግም ለነገ የሚተው የቤት ሥራ አይደለም። የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት የሰራውን አደገኛ ስህተት አርሞ ከድርድሩ መውጣቱ የቀረው ብቸኛ አማራጭ ነበር። ከታሪክና ከመጪው ትውልድ ወቀሳ የሚድነው የግድቡ ባለቤት እኛ መሆናችንን በዓለም ፊት ሲያረጋግጥልን ነው። ምንም አይመጣም በሚል ችኩል ውሳኔ የገባንበት የዋሽንግተኑ ድርድር ነገ ይዞብን የሚመጣው ችግር ካለ ከጠ/ሚኒስትሩና ከመንግሥታቸው ውጪ የሚጠየቅ አይኖርም።
ከቀናት በፊት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መግለጫ በመንግስት በኩል ተሰጥቷል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውና የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ስለሺ በቀለ መንግሥትን ወክለው ማብራሪያ የሰጡት ባለሥልጣናት ናቸው። “በጫናም ሆነ በተፅዕኖ የሚሆን ነገር የለም”፣ “እነዚህ ወገኖች ከታዛቢነት አልፎ አርቅቆ የማቅረብ ፍላጎት አላቸው”፣ “የአሜሪካ መግለጫ በፍፁም ተቀባይነት የለውም”፣ “ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈን አንሰጥም” የሚሉ ተከላካይ አረፍተ-ነገሮች የተደመጡበት መግለጫ ነበር ማለት ይቻላል። አሜሪካም ሆነች የዓለም ባንክ እናሸማግል ሲሉ ከፈቀድን በኋላ ዛሬ እንዲህ ማለቱ ያረፈደ ምላሽ ስለመሆኑ የመንግሥት ኃላፊዎቹ ሊረዱት ይገባል። በዚህ ዘመን ይህን ቀላል ስሌት መስራት የሚችል ዲፕሎማት ማጣታችን በርግጥም አሳፋሪ ነው። በዓባይ ጉዳይ ላይ የሚመራመሩ የቴክኒክ ባለሞያዎቻችንና የፖለቲካ አዋቂዎቻችን ከግብፅ አንፃር ሲመዘኑ የአቅም ማነስ የሚታይባቸው መሆኑም አሳሳቢ ነው። የወንዙ ባለቤት የመሆናችንን የበላይነት ዘንግተን በጠሩን ቦታ የምንገኝ ተሸናፊ ልንሆን አይገባም።
አሁን የድርድሩን መልክ የምንገለብጥበት ወቅት ሊሆን ይገባል። የመካከለኛው ዘመን ነገስታት የሚፈስሰውን ውሃ እንገድባለን በማለት ግብፅን ያስፈራሩበት እንደነበር ታሪክ ይነግረናል። እርግጥ ነው፣ እነርሱ እኛን መፍራት እንጂ በግልባጩ እኛ እነርሱን ልንፈራ ባልተገባ ነበር። የተፈጥሮ ምንጩ መነሻ ኢትዮጵያ ነች። ግብፅ አይደለችም። የዓለም ተሞክሮ እንደሚነግረን ደግሞ የወንዙ ባለቤት የሆኑ ሀገራት የመጀመሪያ ባለድርሻ መሆናቸውን ነው።
አሜሪካ ከሜክሲኮ ጋር፣ ቱርክ ከእነ ኢራቅና ኢራን ጋር፣ ቻይናም ከጎረቤቶቿ ጋር በሀገር ተሻጋሪ ወንዞች ምክንያት ለድርድር ለበርካታ ጊዜ ሲቀመጡ ተስተውሏል። ሆኖም፣ የሥነ-ልቦናም የሞራልም የይዞታም የበላይነት ያላቸው ሀገራት ይዘው የሚቀርቡት መከራከሪያ ቀዳሚ ተሰሚ ነው። የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ሳይጎዱ ባለቤቶቹ የሚጠቀሙበት የስምምነት ማዕቀፍ ይዘጋጃል። ለእኛ የቀረበልን ግን በተቃራኒው ነው። ባለቤቱ ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም ለሌላው ሲል አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያስገድድ ስምምነት እንድንፈርም በዓለም ኃያሏ ሀገር ግፊት እየተደረገብን ነው። የአስዋን ግድብ እንዲጠግብ የዓባይ ግድብ ጦሙን ይደር እንደማለት የሚቆጠር ስሌት ይመስላል። ይህም ብቻ ሳይሆን ጥናት ተደርጓል በሚል ምክንያት የግድቡ የማመንጨት ኃይል ከ6450 ሜጋዋት ላይ 1,300 ያህል እንዲቀንስ መደረጉን በድጋሚ መጠየቅ የሚኖርብን ጊዜ አሁን ይሆናል።
በአጠቃላይ፣ የግብፅ ሰሞነኛ ጉዳይ ጥብቅ ክትትል የሚፈልግ ሆኗል። መንግሥት ተዘናግቶ በፈጠረው ክፍተት ግብፆች ያገኙት ዲፕሎማሲያዊ ድል ትልቅ ትምህርት ሊሰጠን ይገባል። ተወደደም ተጠላም ባለፉት አራት ወራት የገጠመንን ኪሳራ ተቀብለን ልንገመግም ይገባናል። ያለፈውን መገምገም ብቻም ሳይሆን ነገ ይዘን የምንቀርበውን የጠሩ መደራደሪያ ነጥቦች ልናዘጋጅ ያስፈልጋል። በዓባይ ጉዳይ ይዘን የቆየነውን የበላይነት በፖለቲካ ዕውቀት ችግር ምክንያት ልናጣው አይገባም።
Be the first to comment