የ“ፍትሕ መጽሔት” እና የምርጫ ማስታወሻ!

ትሕ መጽሔት” ከምስረታዋ ጀምሮ፣ አገራዊ ኃላፊነትን በመወጣት፣ ሕዝባችን ትክክለኛ መረጃ እንዲደርሰው በማድረግ፣ የምርመራ ሪፖርቶችን በማጠናቀር፣ ድምጽ ለሌላቸው ግፉዓን ወገኖች ድምጽ በመሆን፣ የባሕልና ሥነ-ጽሑፍ ዕድገት እንዲያብብ ደራሲያንን በማበረታታት፤ እንዲሁም ለሌሎች ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሰፊ ትኩረት ሰጥታ ዛሬ ድረስ እያገለገለች መሆኗ ይታወቃል።

መጽሔታችን በየሕትመቷ ጉድለቷን እያረመች እና የማሻሻያ እርምጃዎችን እየወሰደች ራሷን ለማደስ የነበራት እቅድ፣ በወረቀት ዋጋ መናር እና ኮቪድ-19 በፈጠረው መቀዛቀዝ ምክንያት መሳካት ባለመቻሉ፤ አንባቢያንን ይቅርታ እንጠይቃለን።

በቅርቡ መጠነኛ የዋጋ ማስተካከያ በማድረግ፣ ዐዳዲስ ምዕራፎችን እና ገጾችን ለመጨመር እየሠራች እንደሆነ በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን። መጽሔታችንን ለማሻሻል የተነደፍውን እቅድ ለመተግበር፣ በሚዲያው ኢንዱስትሪ እንደተለመደው ከማስታወቂያ ገቢ ለመሸፈን ያደረግነው ጥረት አለመሳካቱም፣ ሌላኛው አገራዊ ተግዳሮት ነው። የዚህ ኹነት ገፊ-ምክንያት ሕወሓት-መራሹ መንግሥት በንግድ ድርጅቶች ባለቤቶች እና አስተዳዳሪዎች ላይ ያሰረገው ስር- ሰደድ ፍርሃት ዛሬም በመቀጠሉ፣ ምርቶቻቸውንም ሆነ አገልግሎታቸውን በ“ፍትሕ መጽሔት” ላይ ለማስተዋወቅ አለመድፈራቸው ነው።

የመንግሥት ድርጅቶችም ማስታወቂያዎቻውን የሚሰጡበት መመዘኛ፣ ልክ እንደ ትላንቱ ይዘትን እንጂ፣ ሥርጭትን ታሳቢ ያላደረገ ሆኖ ቀጥሏል። ይህም ብቸኛው አማራጭ መጽሔቱ ላይ የታቀደው ‹‹ሪፎርም›› ሲተገበር፣ የዋጋ ማሻሻያ ማድረግ እንዲሆን አስገድዷል።

እስከዚያው፣ ከዛሬ ጀምሮ ባሉ የፍትሕ ህትመቶች ላይ ከ“ቀያይ መስመሮች” እና “መልከዐ-ኢትዮጵያ” በተጨማሪ፤ “የምርጫ ገጾች” የሚል ዐዲስ ክፍል መካተቱን እና እስከ ድኀረ-ምርጫው ድረስ እንደሚቀርብ ስንገልጽ በደስታ ነው። በዐዲሱ ክፍል የፖለቲካ ፓርቲ የአመራር አባላት፣ የተወዳዳሪዎች፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች… ቃለ-መጠይቆች እና ከምርጫው ጋር የተያያዙ ዘገባዎች ይቀርቡበታል።

በዚህ አጋጣሚ፣ በተቻለ አቅም ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች የዐምዱ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ለማድረግ እንደምንጥር ከወዲሁ ቃል እንገባለን።

ሌላ አጀንዳ፡-

ቀጣዩ አገር ዐቀፍ ምርጫ ከፊቱ በርካታ ተግዳሮቶች የተደቀኑበት ቢሆንም፤ ሁሉም መብቱን ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም ካሳየ፣ ምርጫው እውነተኛ መሸጋገሪያ የማድረጉን ሥራ ሊያቀልለው እንደሚችል ግልጽ ነው። በተለይ የ“ለውጥ ኃይል ነኝ” የሚለው ብልፅግና በታሪክም በሕግም ተጠያቂ የሚሆንበትን ኃላፊነት ከመጨበጡ አኳያ፣ ሚናው የጎላ እንደሆነ አይጠፋውም ተብሎ ይታመናል።

ስለዚህም፣ ምርጫው ፍፁም ሰለማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ እና ተዓማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ የሚወስዳቸው እርምጃዎች እና የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች በሙሉ፣ የበዛውን ዕዳ መሸከሙን ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ማስታወሱ ተገቢ ነው።

ባልደራስ እና ኢዜማ በአዲስ አበባ፤ ኦነግ እና ኦፌኮ በኦሮሚያ ሕዝባዊ ስብሰባም ሆነ ሰለማዊ ሰልፍ እንዳያደርጉ የተከለከሉበት የአፈና ድርጊት፣ ከዚህ በኋላ ‘ሙሉ በሙሉ ይቀረፋል!’ ተብሎ ሲጠበቅ፤ ያውም የምርጫ ቅስቀሳ በይፋ በሚጀመርበት የዋዜማ ምሽት በኦሮሚያ የኢዜማ የአደአ ወረዳ ምርጫ አስፈጻሚ ወጣት ግርማ ሞገስ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ ግድያ፣ ‘ምርጫው ወደ ነበረበት አረንቋ ሊመለስ ይሆን!?’ የሚል ሥጋት የሚያንር ነው። ይህ ግድያ፣ በተለይ ኦፌኮ በኦሮሚያ በመንግሥት ታጣቂዎች ጫና እየደረሰበት እንደሆነ እና ቢሮዎቹም እንደተዘጉበት በተለያየ ጊዜ ሲያወጣቸው የነበሩ መግለጫዎች ቅጥያ ሊሆን እንደሚችልም ይገመታል።

ኹኔታውን የሚያከፋው ደግሞ፣ ሥልጣን ላይ ያለው ብልፅግና “ወጥ ፓርቲ ነኝ” ከማለቱ እና በየክልሎቹ ያሉት ቅርንጫፎቹ እንደሆኑ ከማወጁ አኳያ፤ በኦሮሚያ የሚፈጸመው መንግሥታዊ አፈና ወደ ሌሎች ክልሎችም መተላለፉን አይቀሬ ማድረጉ ነው። ምክንያቱም የእስከዛሬዎቹ ግድያዎች እና አፈናዎች ላይ የመንግሥት እጅ ካለበት፣ የዕዝ ጠገጉ አንድ ስለሚሆን፤ ሌሎች ክልሎች ውስጥም ተመሳሳዩ ክስተት የማይፈጠርበት አመክንዮ አይኖርም።

ሌላው የምርጫው ከፍተኛ ሥጋት በሁሉም አካባቢ ጠርዝ-የረገጠው ዘረኝነት ነው። ባለፉት ሦስት ዐሥርታት ሥራ ላይ የነበረው የፖለቲካ ሥርዐት ዛሬም ከስም የዘለለ፣ ቅያሪ አለማካሄዱ ችግሩን ተራዛሚ አድርጎታል። በተለይ ከአገሪቱ ሕዝብ አብላጫ ቁጥር የሚይዙት ወጣቶች በተሳሰተ ትርክት መገራታቸው፣ ብሔር ተጋሪያቸው ላልሆነ ፓርቲ ወይም ተወዳዳሪ የሚያንፀባርቁት የጥላቻ ስሜትም ሆነ የኃይል እርምጃዎች ምርጫውን ማደናቀፉ አይቀርም። ይህን ጥርጣሬ የሚያጎነው፣ የመንጋ ፍርድን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በቂ ምልክቶች መታየታቸው ነው።

ኦሮሚያ እና ቤንሻንጉልን በመሳሰሉ ክልሎች ደግሞ የታጠቁ ኃይሎች መኖራቸው፣ አደጋውን እንደሚያበዛው ተገማች ነው። ይሄ እንግዲህ፣ አዲስ አበባን በመሳሰሉ ከተሞች፣ ገዥው ፓርቲ የመታወቂያ ወረቀት ያደለበት (አሁንም እያደለ ለመሆኑ ጥቆማዎች አሉ) ሕገ-ወጥ ድርጊቶች፣ ምርጫውን ኢ-ፍትሐዊ እንደሚያደርጉት ሳንዘነጋ ነው። ሌላው መጠቀስ ያለበት፣ የመታወቂያ ወረቀትም ሆነ የመራጭ ካርድ ለመውሰድ አንዳንድ ቀበሌዎች ላይ የሚታየው የቢሮክራሲ ማነቆ እና የመታወቂያ ወረቀት ማውጫ ብር መናር ምርጫን ለማጭበርበር ከማሴር ጋር ግንኙነት ሊኖረው የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩ ነው።

እነዚህ ሁሉ ገጸ-ብዙ ችግሮች፣ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ የሚፈቱ ካለመሆናቸው በዘለለ፤ ከችግሮቹ የሚበዙት ከቦርዱ ሥልጣንና ኃላፊነት ጋር በፍፁም የማይገናኙ እንደሆኑ ይታወቃል።

ስለዚህም፣ ምርጫው ከደም አፋሳሽነት ወደ ችግር ፈቺነት፣ ከመንጋ ፍርድ ወደ ዴሞክራሲያዊ ብያኔ፣ ከብሔር የበላይነት ወደ ሕግ የበላይነት… የምንሸጋገርበት ይሆን ዘንድ፣ መንግሥት የአንበሳውን ድርሻ የመጫወት ሚናውን በሕግ እና በመርህ ብቻ መወጣት ይጠበቅበታል።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከፀብ አጫሪ ቅስቀሳዎች ራሳቸውን ገርተው፣ የምርጫ ቦርድን ደንብ አክብረው ኃላፊነታቸውን ሊከውኑ ይገባል። ሚዲያዎች አልቦ- አድሎ አገልግሎት የመስጠት ግዴታቸውን በመወጣት፣ ሁሉንም በእኩል ዓይን ያዩ ዘንድ ይመከራል። አክቲቪስቶችም አፍራሽ ከሆኑ የጥላቻ መልዕክቶች እና ከሀሰተኛ ዜናዎች ራሳቸውን አርቀው፣ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ገንቢ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ማስታወሱ ተገቢ ነው።

በመጨረሻም፣ ዕድሜው ለመምረጥ የደረሰ በሙሉ፣ የምርጫ ካርድ መውሰድ እንዳለበት እንዳይዘነጋ ለማስታወስ እንወዳለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*