
ካለፉት አሥራ አምስት ቀናት ጀምሮ ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን በደቡብ ወሎ አካባቢዎች መጠነ-ሰፊ ዘመቻ መክፈቱ ይታወቃል። ይህን ተከትሎ፣ የአመራር አባላቱ፣ የሚቆጣጠሯቸው ሚዲያዎች፣ ዲጂታል ወያኔ እና አክቲቪስቶቻቸው መሬት ላይ ካለው ሃቅ በእጅጉ የሚቃረን፣ ሃሰት-ወለድ የድል ዜና በማሰራጨት ተጠምደዋል። ከትላንት በስቲያ የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል የሰጠው መግለጫ እንኳ፣ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በኩብለላቸው ዋዜማ ትምህርት እና ሥራ አዘግተው በቀጥታ የቴሊቪዥን ሥርጭት ያስተላለፉትን የስንበት መግለጫ ከማስታወስ ያለፈ፣ ቁም ነገር አልነበረውም።
በጥቅሉ ግን፣ ሕወሓት በውሸት ፕሮፓጋንዳ መካኑ የታወቀ ቢሆንም፤ በዐማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ወረራ ከፈጸመ በኋላ የሚያናፍሰውን ተራ ፕሮፓጋንዳ፣ በዐውደ-ውጊያው የተሰለፉት የመከላከያ ሠራዊት፣ የየክልሉ ልዩ ኃይሎች፣ ፋኖ እና ሚሊሻ ባይቀበሉትም፤ በቢሮክራሲው የተሰገሰጉ ሌቦች ‹የሽብር ቡድኑ ከነገ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባል› በሚል ቀቢፀ-ተስፋ በተጋነነ ሙስና ውስጥ እንዲዘፈቁ ገፊ-ምክንያት እየሆነ ነው። በተለይ አዲስ አበባን ጨምሮ፤ በኦሮሚያ እና ዐማራ ክልሎች እየበዛ መሆኑን ታዝበናል።
በርግጥ፣ የመንግሥትን መዋቅር ተገን አድርጎ ሙስና መፈጸም ባለፉት ሠላሳ ዐመት ገሀድ የወጣና እንደ ባህል የተለደመ ነው። ይሁንና፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እጅግ ባጣም መናሩን መደበቅ አይቻልም። በተለይም፡ – ከኢሚግሬሽን ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ ሰነድ አልባውን የመሬት ቅርምት በሕጋዊ ካርታ ለማጽናት እና የመታወቂያ ወረቅት ለማግኘት የሚፈጸመው ወንጀል፤ እንዲሁም ለጦርነቱ በሚደረገው ሃብት አሰባሰብ እና በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ እጅግ በጣም ከፍቷል።
በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች መሬት በወረራ እየያዙ፣ በሙስና ካርታ ማግኘት ሙዝ የመላጥ ያህል እየቀለለ መሄዱ የዐደባባይ ምስጢር ነው። ከትናንሾቹ እስከ ግዙፎቹ የንግድ ተቋማትም ሆነ ቤት ለቤት እየተዞረ ‹ለውጊያው ገንዘብ አዋጡ› የሚባልበት አሠራር፣ ለሌባ ካድሬ እና ለቀማኛ የመንግሥት ሠራተኛ ምቹ መደላድል ፈጥሯል። የሽብር ቡድኑ ለአገሪቱ ስጋት እንዳይሆን እየተደረገ ባለው ዘመቻ ዜጎች በሚችሉት ዐቅም ሁሉ የመሳተፍ ግዴታ እንዳለባቸው ቢታወቅም፤ ይህንን ተገን አድርጎ ለመዝረፍ መሞከሩ ከአገር ክህደት ተለይቶ የሚታይ ወንጀል አይደለም። የኢምግሬሽን ባለሥልጣን መስሪያ ቤትን በተመለከተም ቢሆን፤ ከአራት ቀን በፊት ዐሥር የተቋሙ ባልደረቦች ገንዘብ ተቀብለው ለአደገኛ ወንጀለኞች ጭምር ፓስፖርት ሲሰጡ መቆየታቸው ተገልጾ፣ በቁጥጥር ስር መዋላቸው የነገረ-ዐውዱ አስረጂ ነው።
ለ“ፍትሕ መጽሔት” በስፋት እየደረሱ ካሉ ጥቆማዎች ውስጥ በኦሮሚያ እና ዐማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች፣ ዜጎች የቀበሌ መታወቂያ ለማግኘት በግልጽ አምስት መቶ ብር ጉቦ እንዲከፍሉ እየተደረገ መሆኑን ያስረግጣል። ይህንን ወንጀል ከበፊቱ የሚለየው፣ በአካባቢው ነዋሪ መሆናቸው የሚታወቁ ሰዎችም ሰለባ መሆናቸው ነው። አገልግሎት የመስጠት ኃላፊነት ያለባቸው ሠራተኞች በሥራ ሰዓት ቢሮ ሳይገቡ፣ በአቅራቢው ባሉ ካፍቴሪያዎች መሽገው፣ ባሰማሯቸው ደላሎች ከባለጉዳዮች አምስት አምስት መቶ ብር ጉቦ እየተቀበሉ እንደሚያስተናግዱ ያሰባሰብናቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የትራንስፖርት ዘርፉንም በተመለከተ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች በሦስት የሚመደቡ ናቸው። የመጀመሪያው የአስተዳደሩ ድክምት ነው። ይኸውም ለአገልግሎት ዝግጁ የሆኑ መኪናዎችን በአግባቡ ካለመመደብ እና የተመደቡትንም ካለመቆጣጠር ጋር ይያያዛል። ሁለተኛው ስምሪቱ በሙስና መተብተቡ ነው። በሦስተኛነት የሚጠቀሰው ደግሞ፣ ሆን ተብሎ በመንግሥት እና በሕዝብ መሃል መንፈራቀቅ ለመፍጠር የሚደረግ ለመሆኑ ምልክቶች መኖራቸው ነው። ይህ ችግር፣ በተለይ ከአዲስ አበባ ቅርብ ወዳሉ ከተሞች (ደብረ ዘይትን በመሳሰሉት ላይ) ባልተለመደ ሁኔታ ጎልቶ መውጣቱን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል።
በጥቅሉ፣ በአገሪቱ የተንሰራፋው ሙስና በሕግ የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ በግላጭ የሚፈጸም ከመሆኑ በዘለለ፤ በርካታ መንግሥታዊ ተቋማትን እያጥለቀለቀ ነው። ርዕሰ ጉዳዩን በዚህ ዐውድ ለማንሳት ያስገደደው፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ በከፍተኛ ሥልጣን ባሉ ሹማምንቶች ከሚፈጸሙ ሙስናዎች በተጨማሪ፤ የክፍል ከተማ እና ቀበሌ ኃላፊዎች (ሠራተኞች) ተርታውን ዜጋ ወደ ማራቆት ማዘንበላቸው ነው።
“ፍትሕ መጽሔት”፣ ከታችኛው እስከ ላይኛው መዋቅር ድረስ የተንሰራፋው ሙስና በጊዜ መፍትሄ ካልተበጀለት፣ መንግሥትን ለውድቀት፣ አገርን ለፍርሰት ወደሚዳርግ ደረጃ መሸጋገሩ አይቀሬ እንደሆነ አጽንኦት ሰጥታ ታሳስባለች።
መንግሥት ከሰሜኑ ጦርነት በተጨማሪ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ከፍተኛ ችግር የተፈጠረበት ቢሆንም፤ በመዋቅሩ የተሰገሰጉ ሌቦችን በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ የሚችልበትን መላ መዘየድ ግዴታው እንደሆነ መዘንጋት የለበትም። መቼም ‘የሽብር ቡድኑ አሸንፎ አራት ኪሎን ይቆጣጠራል’ በሚል ቀቢፀ ተስፋ የናወዙ አባላቱን፣ በቢሮክራሲው የተደበቁ ሌቦችን እና ለጠላት በአምስተኛ ረድፍ ተሰልፈው እየቦጠቦጡ ያሉ ካህዲዎችን ካልተቆጣጠረ፣ ወደማይታረም ስህተት መገፋቱ የጊዜ ጉዳይ ብቻ እንደሆነ አይጠፋውም።
Be the first to comment