
የሰሜኑ ጦርነት ከተቀሰቀሰ ጀምሮ፣ በተለይ በፌደራሉ እና በዐማራ ክልላዊ መንግሥታት በኩል እጅግ አደገኛ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ክፍተቶች እና ተቃርኖዎች በስፋት እየተስተዋሉ ነው። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ፣ ሽብርተኛው ቡድን፣ በተሻለ ቁመና እና አፈጻጸም የጥፋት እቅዱን መተግበር አላዳገተውም። ይህም ነው፣ አደጋውን የከፋ ያደርገው።
የአገሪቱን የሰው ኃይል፣ ሪሶርስ እና መንግሥታዊ መዋቅሮችን የሚጠቀሙ አካላት፣ ጦርነቱን በተመለከተ የሚከተሉት ስልትን ጨምሮ፤ ፕሮፓጋንዳውን እና መሰል ሁኔታዎች ላይ የረባ ዝግጅት እንደማያደርጉ፣ በየዐወደ ውጊያው የሚታዩ መራራ እውነቶች በገሃድ ይመስክራሉ። ሌላው ቀርቱ የፌደራሉ እና የክልል ልዩ ኃይሎች ግዳጆችን በተናበበ ሁኔታ መከወን ተስኖቿው የታዩበት ግንባሮች ጥቂት አይደሉም።
በግልባጩ የሕወሓት የሽብር ቡድን በዚህ ደረጃ እየተፈጠረ ያለውን ክፍተት ለ“አጥፍቶ መጥፋት” ሰይጣናዊ ዘመቻው እየተጠቀመበት፣ ከቀን ወደ ቀን ይዞታውን እና የውድመት አድማሱን አስፍቷል። ሰዋዊ እና ቁሳዊ ኪሳራውም የበዛ ሆኗል፤ (በነገራችን ላይ፣ የመከላከሉንም ሆነ የመደምሰሱን ውጊያ እያከሸፉ ያሉ ትርምስምሶችን፣ በዚህ ዐውድ ለመዘርዘር ያልወደድነው፣ የሚበዙት ከወታደራዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ በመሆናቸው ‹ጊዜው አይደለም› በሚል ድምዳሜ መሆኑን ልብ ይሏል።)
የሆነው ሆኖ፣ በመሰዋትነት የተገኘው ድል፣ በፖለቲካ ውሳኔ ተቀልብሶ፣ የትግራይ ክልል ለዚህ የጥፋት ኃይል ተለቅቆ ሲወጣ፣ በቀጣይ ሊከሰቱ ወይም ሊመጡ የሚችሉ አደጋዎችን በመተንተንና ለመከላከል የሚያስችሉ እቅዶችን በማዘጋጀት አለመሆኑ የችግሮቹ ጥቅል መነሾ ነው። በተለይ የቡድኑ የበቀል ብትር ያረፈባቸው ዐማራ እና አፋር ክልሎች ቢያንስ “የቢሆን ሃሳብ”ን ተንተርሰው ቅደመ ዝግጅት አድርገው ራሳቸውን የሚከላከሉበት ሁኔታ እንዲፈጠር አልመመቻቸቱ፣ በክልሎቹ እና በፌደራል መንግሥቱ መሃል ያለውን አለመናበብም ሆነ ክፍተት ያስረገጠ ነው። ይህ ችግር ገፋ ሲል በሕዝብ ውስጥ ጥርጣሬ እንዲኖር ማደረጉንም ታዝበናል። የ“ተከዳን” ስሜት በስፋት የሚንጸባረቀውም ከዚህ አኳያ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
በአናቱ፣ ሕግ የማስከበር ዘመቻው ወደ ህልውና ዘመቻ ከተቀየረ በኋላ ክተት መታወጁን የሚጻረሩ አስተያየቶች ከጠቅላይ ሚንስትሩ አንደበት ጭምር መደመጣቸው ሌላው ችግር ሆኗል። ፌደራል መንግሥቱ በሚቆጣጠራቸውም ሆነ በክልል ሚዲያዎች “መቼም የትም ለአገሬ እዘምታለሁ” የሚል ክተት ታውጆ፣ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ ወጣቶች ከመላው ኢትዮጵያ ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ገብተው ሲያበቁ፤ ጦርነቱ እንደተጠናቀቀ የሚያስመስሉ መግለጫዎችን መስጠት፣ ጠላትን ከማገዝ አይለይም። በአሁኑ ወቅት፣ እነዚህ ወጣቶች ስልጠናቸውን ይጨርሱ-አይጨርሱ በግልጽ ባይታወቅም (ወይም ወታደራዊ ምስጢር ሊሆን ቢችልም)፤ ጦርነቱ ሳይቋጭ ጠቅላይ ሚንስትሩ የታወጀውን ክተት በዐደባባይ ማጣጣላቸው ትልቅ ጥፋት ነው። በዚህ አፍራሽ እና የውጊያ ተነሳሽነትን በሚገድብ ንግግር የተበረታታው ሕወሓትም ይዞታውን ወደ ደቡብ ወሎ አስፍቶ ከባድ ጥፋት እያደረሰ ነው።
ሌላው ጉዳይ፣ ሕወሓት በጦርነቱ ብልጫ እየወሰደ ያለው በውጊያ ብቃቱ ሳይሆን፤ በሚያጠቃቸው አካባቢዎች በሚኖረው ሕዝብ፣ በመከለከያ ሠራዊቱ እና ልዩ ኃይሎች ላይ በሚነዛው የሃሰት ሽብር ከመሆኑ ጋር ይያያዛል። በተለይ በማኀበረሰቡ ላይ መንግሥት ግዴለሽ እና ዐቅመ-ቢስ እንደሆነ በመስበክ፤ እንዲሁም ያልተቆጣጠራቸውን ከተሞች እንደተቆጣጠረ አስመስሎ በማደናገር መካኑ በዚህ ጦርነት በሚገባ ጠቅሞታል። ከሩብ ክፍል ዘመን ፈቀቅ ላላ ጊዜ፣ የማዕከላዊ መንግሥቱን “በከፋፍል ግዛ” ፖሊሲ ተቆጣጥሮ የቆየበት ልምዱን፣ በዐውደ ውጊያ እየተገበረው በሕዝብ እና በመንግሥት፣ በመከላከያ ሠራዊቱ እና በክልል ልዩ ኃይል መሃል አለመተማመን እንዲኖር እያደረገ ነውና።
በጥቅሉ፣ አሁንም ቢሆን ከሕወሓት ፕሮፓጋንዳ ባሻገር፤ በዋናነት የፌደራል፣ የዐማራ እና የአፋር ክልል መንግሥታት፣ ጠላት በሚያቅዳቸው መስመሮች ብቻ እየተጓዙ መስዋትነት ከመክፍል ወጥተው፣ (ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግረው)፤ በራሳቸው እቅድ እና የተናበበ አፈጻጸም ላይ ሊያተኩሩ እንደሚገባ ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። በተለይ የሽብር ቡድኑ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የትግራይ ወጣቶችን፣ ህፃናትን እና ጎልማሶችን በፍቃደኝነትም ይሁን በኃይል አሰልፎ አገሪቱን ለማፍረስ የሚያደርገውን ጥረት የሚመጥን ዝግጅትና መናበብ ከመቼውም በላይ የግድ ይላል። ምክንያቱም ጦርነቱ በሕወሓት የበላይነት የሚጠናቀቅበት እድል እጅግ የጠበበ ቢሆንም፤ ከዚህ በኋላ ለተወሰኑ ወራት እንኳ በጥፋት ተግባሩ መቆየት ከቻለ፣ አገሪቱ ወደማትወጣው ኪሳራ ውስጥ የመግባቷ አይቀሬነት አጠያያቂ አይደለም።
ሌላው እዚህ ጋ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጦርነቱ የእርስ- በርስ ከመሆኑ አኳያ ለሽብር ቡድኑ መረጃ የሚሰበሰቡ በርካታ ሰዎች በየቦታው መኖራቸው እና ሰርገው እየገቡ እንደሆነ ከግምት ከትቶ የመሥራቱ ወሳኝነት ነው። ይህ ሲባል ግን፣ የዓይኑ ከለር ያላማረውን ሁሉ በደቦ ፍርድ መቅጣት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል።
ድል ለኢትዮጵያ
Be the first to comment