
ከአገራዊ ለውጡ በኋላ በሶማሌ ክልል ለሚታየው ሰላም የርዕሰ መስተዳደሩ አቶ ሙስጠፋ መሐመድ አመራር መጠንከርን አመላክቷል። ክልሉ ባለፉት ዓመታት በከፍተኛ የፀጥታ ችግር ውስጥ በነበረበት ወቅት፣ የሕይወት መስዋዕትነት በመክፈል የምስራቅ ዕዝ የሠራዊት አመራር እና አባላት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማድረጉን አቶ ሙስጠፋ ሙሐመድ ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙሃን ገለጻ ሰጥተዋል።
ከለውጡ በኋላም በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው የፀጥታ ችግርን በፍጥነት በመቆጣጠር ሕዝባዊነቱን ያስመሰከረ ተግባር መፈፀሙን ተናግረዋል። ‹‹በዚህም ክልሉ ላይ ይደርስ የነበረውን ኪሳራ መቀነስ የተቻለ ሲሆን፣ በተፈጠረው አስተማማኝ ሰላም እና ለውጥ አማካኝነት በርካታ ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ ለመሳብ ተችሏል›› ብለዋል።
በርግጥ፣ ክልሉ ከነበረው የፀጥታ ችግር አኳያ ባለሀብቶች አይፈልጉትም ነበር። የመሰረተ ልማት ግንባታ ችግርም ሌላኛው የክልሉ ፈተና የነበረ ሲሆን፣ አቶ ሙስጠፌ ይህንን መሰረታዊ ችግር ለመቅረፍ ጥረት ሲያደርጉ ታይቷል። ከለውጡ በፊት በተወሰኑ ሰዎች ተይዞ የነበረው የኢንቨስትመንት እና የንግድ ሥራ በክልሉ በተፈጠረው ለውጥ አማካኝነት እንደተቀረፈ እና ሁሉም በተቻለው መጠን በክልሉ ሀብቱን ማፍሰስ ይችላል ተብሏል።
በዚህ ላይ ከዚህ በፊት ኢንቨስት ለማድረግ ቀርቶ ከመሃል አገር የታሸገ ውሃን ለማስመጣት በክልሉ ከነበረው አመራር ፍቃድ ላይ የተመሰረተ እንደነበረ ገልፀው፤ አሁን ላይ የክልሉ መንግሥት በፈጠረው ለውጥ ማንኛውም ሰው በነፃነት በፈለጉት የኢንቨስት መስክ መሳተፍ ይችላሉ ብለዋል።
የክልሉ ወጣቶችም በክልሉ ባለው የሥራ እና የኢንቨስትመንት ዕድሎች በመጠቀም እንዲለወጡ መክረዋል። ከላይ የተጠቀሰው ለውጥ ከሌሎች የኢትዮጵያ ክልሎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ ቢሆንም፤ ‹‹በክልሉ ሥር የሰደዱ ችግሮች ተጀመሩ እንጂ ገና አልተነኩም›› የሚሉ አስተያየት ሰጭዎች አሉ። በተለይም በአፋር ክልል በኩል ያለው ግጭት እስካሁንም ድረስ መፍትሔ ማጣቱ በአሳሳቢነት ተጠቅሷል።
በጉዳዩ ላይ የሁለቱ ክልል አመራሮች ተመወያይተው ችግሩን በዘላቂነት ከመቅረፍ ይልቅ፤ በመወቃቀስ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ከዚህ ቀደም ባቀረቧቸው መግለጫዎች መታዘብ ተችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ከዝናብ ዕጥረት ጋር ተያይዞ ክልሉ በድርቅ ሥጋት ውስጥ መሆኑ ተጠቁሟል። ችግሩ በቶሎ መፍትሔ ካላገኘ ለተለያዩ ልማቶች ይውላል የተባለውን በጀት እስከማጠፍ የሚጠይቅ ሥጋት መሆኑን የመረጃ ምንጮች ይጠቁማሉ።
በቅርቡ በሶማሌ ክልል የበልግ ዝናብ አናሳ ሊሆን እንዲሚችል ተነግሮ እንደነበር ይታወሳል። ይህን ችግር አስቀድሞ የጠቆመው የሶማሌ እና አጎራባች ክልሎች ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል ነበር። ማዕከሉ ያለፈውን የበጋ ወራት የአየር ሁኔታ እና የቀጣይ የበልግ ወራት ትንበያ ዳሰሳን ለሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት አመላክቶ ነበር። የባለፈው ዓመት የዝናብ ወቅትን መሰረት በማድረግ በተያዘው 2013 ዓ.ም የበጋ ወራት የአየር ንብረት እና የዝናብ ስርጭት የነበረበትን ሁኔታ፣ እና በቀጣይ በሶማሌ ክልል የተለያዩ ዞኖች ላይ የሚኖረውን የዝናብ ሰርጭት መጠን እና የአየር ፀባይ ሙቀት ትንበያ ዳሰሳን በመመልከት፤ የሚመለከታቸው አካላት ማደረግ የሚገባቸውን ቅድመ ዝግጅት አሳስቦ ነበር። በመሆኑም፣ የክልሉ መንግሥት ይህን ችግር ሳይዘነጋ የጀመረውን ለውጥ እንያጠናክር ተጠይቋል።
Be the first to comment