
ይህን ጽሑፍ እንዳሰናዳ ገፊ-ምክንያት የሆነኝ በቅርቡ ያነበብኩትና በታሪክ ተመራማሪው እንግሊዛዊ IAN CAMPBELL የተዘጋጀው“THE ADDIS ABABA MASSACRE – Italy’s National shame” የተሰኘው መጽሐፍ ነው። ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርራ አዲስ አበባን በያዘች ዘጠነኛው ወር፣ (ከየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም ጀምሮ) በነበሩት ተከታታይ ሦስት ቀናት በከተማይቱ ነዋሪዎች ላይ ያደረሰችውን እጅግ ዘግናኝና አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ በጥልቀት ይተነትናል።
በዚህ መጽፍ ላይ ከ84 ዐመት በፊት እንደተፈጸሙ የተዘረዘሩት የፋሺስት ወራሪ የጭካኔ ወንጀሎች፣ ዛሬ የሕወሓት የሽብር ቡድን ከሚፈጽማቸው ዘግናኝ ጭፍጨፋዎች ጋር እጅግ ተመሳሳይ እና በቀጥታ የተቀዱ መሆኑን ለመረዳት፣ መጽሐፉን ማንበብ ብቻ በቂ ነው። ጉዳዩን የአብዛኛዎቹ የሕወሓት መስራች እና ከፍተኛ አመራር አባቶች፣ በፋሺስቱ ወረራ ወቅት አገራቸውን ክደው ለጣሊያን ያደሩ ባንዳዎች ከነበሩበት ዐውድ አኳያ ስናየው ደግሞ፣ ተመሳስሎሹን የበለጠ ያጎላዋል።
መነሻ
በፋሺስት ጣሊያን ንጉሥ ስም “የኢትዮጵያ ገዥ (viceroy)” ሆኖ የተሾመው ሩዶልፎ ግራዚያኒ፣ የአንድ ጣሊያናዊ ልዑል መወለድን አስመልክቶ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በአዲስ አበባው ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት ንግግር እንደሚያደርግ እና ለከተማው ነዳያን ምፅዋት እንደሚሰጥ አስታወቀ። ይህን ተከትሎም፣ ወደ ሦስት ሺሕ የሚጠጉ ኢትዮጵያዊያን በቤተ-መንግሥቱ ቅጽር ተገኙ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በወቅቱ የዐደዋውን ድል ያስቀጠሉ አርበኞች በዱር-ገደሉ ከወራሪው ሠራዊት እና ካሰለፋቸው ባዳዎች ጋር እየተዋደቁ መሆኑ ይታወቃል። ይህ የነፃነት ትግል በአዲስ አበባ ውስጥም በኀቡዕ መካሄድ ከጀመረ ሰንብቷል። አብርሃ ደቦጭ እና ሞገስ አስግዶም የተባሉ ወጣቶችም የእንቅስቃሴው ምስጢራዊ አባል ናቸው። እነዚህ ጀግኖች አጋጣሚውን እንደዋዛ ማለፍ አልፈለጉም። እናም ከሕዝቡ ጋር ተቀላቅለው ገነተ ልዑል ቤተ-መንግሥት ተገኙ።
Be the first to comment