
የቅርስ ምንነትና ፋይዳ
የፍጥረተ-ዓለም መነሻና የሰው ዘር መገኛ ተብላ የምትታወቀው ኢትዮጵያ፣ ከብዙ ሺሕ ዐመታት በላይ የተሻገረና ያልተቋረጠ የመንግሥትነት ታሪክ ያላትና ይህንኑ ዕውነታ የሚመሰክሩ የበርካታ ባሕላዊና ታሪካዊ ቅርሶች ባለቤት ናት። ከሰማንያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪ ማኅበረሰቦችም በደምና አጥንት ተዋህደው፣ በልዩ ልዩ ባሕላዊ፣ ማኀበራዊ፣ መንፈሳዊና ምጣኔ-ሀብታዊ መስተጋብሮች ተዛምደው የሚገኙባት አገር በመሆኗ፣ የበርካታ ድንቅ ቅርሶች ማኅደርነትን ታድላለች። የክርስትና፣ እስልምና እና የአይሁድ እምነትን (ሦስቱ አብርሐማዊ ሃይማኖቶችን) ከጥንት ይዛ የተገኘት መንፈሳዊት ምድር መሆኗም፣ የአኩሪ ታሪክ ባለቤትና የአያሌ ግሩም ቅርሶች መገኛ ትሆን ዘንድ አስተዋጽኦ አድርጎላታል።
ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን በከፈሉት የመስዋዕትነት ተጋድሎ፣ አገራችን ነፃነቷን አስከብራ ለዘመናት የኖረች ብቸኛዋ አፍሪካዊት አገር በመሆኗም፤ በሌሎች አገሮች ከታየው በተለየ መልኩ፣ ቅርሶቿ ከቅኝ ገዥዎችና የውጭ ወራሪዎች ተርፈው ዘመን ተሻጋሪ ለመሆን በቅተዋል። በእነዚህ ድንቅ ቅርሶቿ አምባሳደርነትም በዓለም ዐደባባይ በክብር እንድትወከልና ከፍ ብላ እንድትታይ ተደርጋለች። ለዚህ አንዱ ማሳያ፣ ዐሥራ ሦስት ቅርሶችን በዓለም ዐቀፉ መዝገብ በማስፈር፣ በአፍሪካ የቀዳሚነት ቦታ መያዟ ነው። ከዚህም በላይ፣ የላቀ ሁለንተናዊ እሴትነት ያላቸውና የዓለም ቅርስ ለመሆን መስፈርቱን የሚያሟሉ ገና እጅግ ብዙ ቅርሶች አሏት። ከሁለት ሺሕ ዐመት በላይ የዘለቀ የራሷ ፊደልና አኀዝ ባለቤትነቷም፣ በአፍሪካ ብቸኛዋ አገር ዐሥራ ሁለት የጽሑፍ መዛግብትን በዓለም ዐቀፍ ቅርስነት ያስመዝገበች አድርጓታል። ለአብነት ያህል እነዚህን አነሳን እንጂ፤ በአራቱም አቅጣጫ የሚገኙ ቅርሶች ብዛትና ዐይነት የት-የለሌ ነው።
ይህም ሆኖ ግን፣ ቅርሶቻችን ተገቢው አገራዊና መንግሥታዊ ትኩረት ተሰጥቷቸዋል ተብሎ አይታሰብም። ለዚህም ዋናው ምክንያት፣ የቅርስን ምንነትና ያለውን ዘርፈ ብዙ ፋይዳ በቅጡ ካለመረዳት የመነጭ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ቅርሶች በተለያዩ ዘመናት የነበሩ የማኅበረሰብ አካላት የሥራና የፈጠራ ውጤቶች ቢሆኑም፤ አንዱ ከሌላው ጋር በሚኖራቸው ማኀበራዊ፣ ባሕላዊ፣ መንፈሳዊ፣ ምጣኔ- ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ ግንኙነቶቻቸውና ልውውጦች የዳበሩ የባሕልና የታሪክ መዘክሮች ናቸው። በሌላ አገላለጽ ቅርሶች ሕዝቦች በየዘመናቸው መሰረታዊ ኑሯቸውን ለማሟላት፣ መንፈሳዊ አእምሯቸውን ለማርካትና ሥነ-ልቦናዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት ሲሉ እርስ-በርስና ከአካባቢያቸው ጋር በነበራቸው መስተጋብር የተገኙ የሥራና የፈጠራ ፍሬዎች ናቸው።
Be the first to comment