መክሸፍ እንደ ብአዴን/ብልፅግና | ከቀድሞ የአመራር አባል አንዱ

(የብአዴን የአድር-ባይነት ስሪት፣ የግለሰቦች ሚና እና የድል ተነጣቂነት በዐማራ ሕዝብ ላይ ያደረሰው መዘዝ!)

ህብረ-ብሔራዊ ስያሜ የነበረው ኢሕዴን፣ የብሔር መልክ ወዳለው የብአዴን አደረጃጀት ከተቀየረ ወዲህ፣ የዐማራን ሕዝብ ጥቅም በተመለከተ ፖለቲካዊ በሆነ መንገድ በማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባ ላይ በግላጭ የተከራከረው በ2001 ዓ.ም ነው። የዚህ ገፊ-ምክንያቱ ደግሞ፣ ሕወሓት፣ የአርማጭሆ በሆኑት፡- የግጨው እና የማርዘነብ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶች ላይ፣ ዐዳዲስ ሰዎችን አምጥቶ ማስፈሩን የአካባቢው ሕዝብ በመቃወሙ እና ጠንካራ ግፊት በማደረጉ ነበር። ይህን ተከትሎም፣ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ከፍተኛ ክርክር ተነሳ።

የክርክሩ ሂደት በሁለት የተከፈል ነበር። አንደኛው ክፍል፡- በአቶ ገዱ አንዳረጋቸው፣ ዮሃንስ ቧያለው፣ ተስፋዬ ጌታቸው እና ተፈራ ደርበው የሚመራ ሲሆን፤ ሌሎች የዐማራ ልጆችም ደግፈውታል። የዚህ ቡድን ዋንኛው የመከራከሪያ ጭብጥ፡- “ሕወሓት የመሬት ማስፋፋትና ወረራ እየፈፀመ ነው፤ ሁልጊዜ ተገፍተንና ሸሽተን የት ልንደርስ ነው? ግጨው እና ማርዘነብ ብቻ አይደለም፤ ሁመራም የእኛ መሬት ለመሆኑ የታሪክ ማስረጃዎች በገፍ አሉ፤ ዐማራን እያስደፈርን እና መሬቱን እያስወሰድን እስከ መቼ ልንኖር ነው?!” በሚል ጠንካራ ሃሳብ ላይ የተመረኮዘ ነበር።

ሁለተኛው ክፍል፣ በአቶ በረከት ስምዖን የሚመራ ሲሆን፤ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ከበደ ጫኔ፣ ህላዊ ዮሴፍ እና ታደሰ ካሳን ይዟል። የዚህ ቡድን ዋንኛ የመከራከሪያ ጭብጥ፡- “የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አተያይ መሬት ሳይሆን፣ ሕዝብ ነው፤ መሬትን ከሕዝብ ለይቶ ማየት መረን-የለቀቀ የጨቋኝነትና የገዥነት ባህሪ ያለው ከመሆኑ በላይ፤ ሕዝብን ወደ ጎን በመተው፣ ለመሬት የሚታገል አጉራ-ዘለል የሆነ ገደብ-የለሽ ትምክህተኝነት ነው፤ በትምክህት ተባይ የተወረረ ጭንቅላት መሬትን አግዝፎ፣ ክቡር የሆነውን ሰው አሳንሶ የሚመለከት ስለሆነ፣ እይታችን ሁሉ የተንሸዋረረ ነው፤ የዐማራ ክልል መሪዎች ይልቁንም ስለ ግጨው እና ማርዘነብ ቁራጭ መሬት ከምትንገበገቡና ከምታለቅሱ፡- የመተማን፣ የቋራን እና የደንቢያን መሬት ለምን አታለሙትም? ከጎንህ ያለን መሬት ሳታለማና ምንም ምርት ሳትጨምርበት፣ ከሩቅ ባለው ቁራጭ መሬት ላይ ‹የተፈናቀሉ ሰዎች ሊሰፍሩበት ነው› ብለህ ታቅራራለህ፤ (በወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት አያሌው ጎበዜ ስለነበረ) አያሌው ጎበዜ ችሎታው ካለህ፣ ብቃቱ ካለህ ‹ግጨው የእኛ መሬት ነው አሉ› እያልክ ከምታንሾካሹክ፣ በእጅህ ያለውን መሬት መጀመሪያ አልማበት…” የሚል ሸንቋጭና ዛቻ-አዘል መከራከሪያ እንደነበረ የመድረኩ ተሳታፊዎች ያስታውሱታል። በዚህ መልክ፣ በሁለት ተከፍሎ የተጧጧፈው ክርክር በሃሳብ መሸናነፍ ስለተሳነው፣ “ግጭው እና ማርዘነብ ላይ ሕወሓት ታስፍርበት ወይስ አታስፍርበት?” በሚለው ላይ ድምፅ እንዲሰጥ ተወሰነ። በወቅቱ በመድረኩ የተገኙት 54 የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትም ድምፅ ሰጡ። በውጤቱም፡- “መሬት ችግራችን አይደለም፣ ሕወሓት ያስፍርበት!” የሚለው ቡድን 28 ድምፅ ሲያገኝ፤ “በመሬታችን ላይ ማንም ሊያሰፍርበት አይገባም፣ ኢ-ፍትሐዊ ነው!” የሚለው ደግሞ 26 ድምፅ አገኘ። በዚህም፣ “መሬቱ ይሰጥ” የሚለው የብአዴን አንዱ ጎራ በ2 ድምፅ በመበለጡ፣ ሕወሓት የግጨውን እና የማርዘነብን መሬት ከመከላከያ የቀነሳቸውን የትግራይ ተወላጆች የሠራዊቱ አባላትን እና ከሱዳን የተመለሱ ስደተኞችን ያለ ከልካይ አሰፈረ።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*