መክሸፍ እንደ ዐማራ-ብልፅግና ፪ | ከቀድሞ የአመራር አባል አንዱ

ያኔ፣ ሕገ-ደንብና ፕሮግራም አዘጋጅቶ በረሃ ቢገባም፣ እስከ 1981 ዓ.ም ክረምት ድረስ ጫካ-ለጫካ ከመሽሎክሎክ ባለፈ፤ የረባ- መሬት ማስለቀቅ ሳይችል ቆይቷል። ይሁንና፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን በዐዲስ መልክ ገምግሞ ሲያቃ፤ ‹በዐማራ ሕዝብ ዐቅም ተጠቅመን መንቀሳቀስ ካልቻልን በቀር፣ ትግራይን ነፃ በማውጣት የሕዝባችንን እጣ-ፈንታ መወሰን አንችልም› የሚል መደምደሚያ ላይ ደረሰ። ይህን ተከትሎም፣ በ1981 ዓ.ም የመጨረሻ ወር ከሕብረ- ብሔሩ ኢሕዴን ጋር የነበረውን ትብብር ወደ ግንባር ቀይሮ ኢሕአዴግን መሰረተ። ከዚህ በኋላ ነው፣ በአንድ ዐመት ውስጥ፡- ሙሉ ትግራይን፣ ዋግኽምራን፣ ሰሜን ወሎን፣ አብዛኛው የደቡብ ወሎ አካባቢ፣ በከፊል የደቡብ እና ሰሜን ጎንደር አካባቢዎችን ከደርግ አገዛዝ ነፃ ማውጣት የተቻለው።

ትሕነግ ወደ 17 ዐመት በሚጠጋ በረህኝነቱ ያላገኘውን ድል፣ በአንድ ዐመት ማግኘቱን ተንተርሶ ባካሄደው ግምገማም፣ የግንባሩ መፈጠር ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ስላረጋገጠለት፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ደርግን ለመጣል ያለውን ምቹ ሁኔታና መልካም አጋጣሚዎች መጠቀም የሚያስችል እቅድ ነድፏል። እግረ-መንገዱንም የዐማራን ሕዝብ ሥነ-ልቦና አብሮ እየኖረ ከማጥናት አለተዘናጋም። ምክንያቱም፣ የመጨረሻውን ድል ለመቀዳጀት ዐቅም የሚሆነውን የወጣት ኃይል፣ ስንቅና ትጥቅ ነፃ ከወጡት የዐማራ አካባቢዎች በበቂ ማግኘት እንደሚችል በግምገማው አረጋግጧል። አዎ፣ ግምገማው ልክ ነበር። በነዚህ የገጠር አካባቢዎች የነበሩትን የፖለቲካ ‹ሀሁ…› የማያውቁ ወጣቶችን በየዋሻውና ጫካው እየሰበሰበ፣ የደርግን አስከፊነት በራሳቸውና በወላጆቻቸው ላይ ሲያደርግ የነበረውን ግፍና መከራ እየዘረዘረ፣ በብሶትና ጥላቻ ቅስቀሳ ማነሳሳት ጀመረ። በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችም ሰምተውትና አይተውት የማያውቁትን የወያኔን ፕሮፓጋንዳ እንደተረጋገጠ እውነት አምነው በመቀበል፣ ለዓላማው ማስፈጸሚያነት በሁለት ክንፍ ተደራጅተው ተሰማሩ። አንደኛው፣ “ክፍለ-ሕዝብ” በሚል ስያሜ በካድሬነት ሰልጥኖ እንዲቀሰቅስና እንዲያደራጅ የተመደበው ሲሆን፤ በአጭር ጊዜም የሕዝቡን ባህል፣ ልማድና ወግ የሚያውቁ፣ ህብረተሰቡን በራሱ ቋንቋ የሚቀሰቅሱ ካድሬዎች መፍጠር ችሏል። ሁለተኛው፣ እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር ያለው ወጣት ተዋጊ ሠራዊቱን መቀላቀሉ ነው። ይህ ግዙፍ ኃይል፣ በራሱ በዐማራ ሕዝብ ስንቅና ትጥቅ አቅራቢነት በአንድ ጊዜ እንዲሰለጥን ከተደረገ በኋላ፣ በክፍለ ጦር ተደራጅቶ ወደ ውጊያ ተሰማራ። ነፃ በወጡት በወሎና ጎንደር አካባቢዎች የተሰለፈው የሰው ኃይል፣ የተሰባሰበው ስንቅና ትጥቅ ተደማምረው፣ ወያኔ ደርግን በመደምሰስ አራት ኪሎን እንደሚቆጣጠር እርግጠኛ የሆነበትን የሞራል ዘውድ ጫነለት።

ድርጅቱ፣ በዚህ የተስፈኝነት ማማ ከተደላደለ በኋላ፣ በፈጣን ሁኔታ በርካታ ሥራዎችን ከመሥራቱ በተጨማሪ፤ አገሪቱ እጁ ላይ መውደቋን እያማተረ፡ – የሽግግር መንግሥት ቻርተር፣ የክልል አስተዳደሮች የአከላለል ካርታ እና በታሪክዊ ጠላትነት የፈረጀውን ዐማራን የሚበትንበትን ስትራቴጅክ ጉዳዮች በዝርዝር እያጠናና እየቀመረ ወደ አዲስ አበባ ገሰገሰ። አንድ ዐመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥም በሁለቱ ዋና ዋና አቅጣጫዎች፡ – በጎንደር ግንባር በጎጃም ወደ ምዕራብ ሸዋ “ቢሉስማ ውልቂጡማ” በሚል ዘመቻ በአምቦ አልፎ አዲስ አበባን እንዲከብ ሲደረግ፤ በወሎ ግንባር፡- ሰሜን ሸዋን ከጫፍ- ጫፍ ከቦ አፋርን ጨምሮ አዋሽን በመቁረጥ፣ አዲስ አበባን ዙርያ-ገባዋን ቀለበት ውስጥ ከተታት። የኢሕድሪ መንግሥትም ሊከላከለው በማይችል ሁኔታ የመፍረስ አደጋ ስለተደቀነበት፣ ለከባድ ፍርሃትና ጭንቀት በመጋለጡ፤ ተገማች ባልሆነ ሁኔታ በራሱ ጊዜ ሟሙቶ፣ ወያኔ አዲስ አበባን ያለ ቶክስ የሚረከብበት በለስ ቀናው። ከዚህ በኋላ፣ በሌላው የአገሪቱ ክፍል የሰፈር ሽፍታን ከማባረር ያለፈ ችግር ሳይገጥመው፣ በአጭር ጊዜ ዐማራን ምርኩዝ አድርጎ በትረ-ሥልጣኑን ጠቀለለ።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*