ሰሜን ወሎን በጨረፍታ | ምስጋን ዝናቤ ተሜ

የተናጠል ተኩስ አቁም ፖለቲካው በሕወሓት አፈር-ልሶ መነሳት እና በፌደራል መንግሥት ‹ድንገተኛ› ውሳኔ ያተኮረ ነው። እውነታው በፖለቲከኞች መርህ ተሸሽጎ የጦር ሜዳው ወደ ዐማራ ክልል ከተሞች ተጠጋ። ከሐምሌ 14 እስከ 16/2013 ዓ.ም ባሉት ቀናት ቆቦ በሕወሓት መልሶ ማጥቃት ማሟሻ ተወረረ። ለወትሮው በልጅ አገረዶች ‹ሶለል› የሚደምቀው አሸንዳም ሆነ የእረኞች ጅራፍ ጨዋታ ተስተጓጉሎ ሕዝብ የክረምት ሽሽት ገጠመው።

በነገራችን ላይ ቆቦን ለመያዝ ከተደረገው ጦርነት በኋላ ያለው መንገድ ለሕወሓት አልጋ-በአልጋ የሆነ ያህል ክፍተት መፈጠሩ ዋጋ አስከፍሏል። ከሮቢት እስከ ወልዲያ መደዳውን ያሉ ከተሞች በዋናነት በሽብር ወሬ የተያዙ ናቸው። ስልታዊ ማፈግፈጉ እንዳለ ሆኖ፣ አንዳንድ የቆቦ እና የመከላከያ አመራሮች፣ ‹‹ሰብራችሁ ውጡ ስለተባልን ጁንታው እንዳይፈጃችሁ…›› በሚል ዛቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ወደ ወልዲያ እንዲሸሹ ማደናገጣቸውን፣ በኋላ ጉዳዩን ተንተርሰው የወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ።

ለወቅቱ ሁኔታውን የሚጠቁም ትዝብቴን ጠቅሼ ልለፍ። ቆቦ በተያዘ ሦስተኛው ቀን አካባቢ (ሐምሌ 19 ማለት ነው) ከቢሮ መልስ ለቅዱስ ገብርኤል ዝክር ተጠርቼ ከጓደኛ ቤት ነበርኩ። በዕለቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ የእጅ ስልኬ ጠራ፤ አነሳሁት፡-

‹‹ልጄ…›› የሚል ድምጽ ወደ ጆሬዮ ተንቆረቆረ፤ እናቴ ናት። ኔቶዎርክ ተቆራረጠባት መሰለኝ በቅጡ ሳንሰማማ ስልኩ ተዘጋ። ልቤ ግን፣ ያለ ወትሮው ራደ፤ ባለሁበት የጨው አምድ መስዬ እናቴ ስላለችበት ሁኔታ ማንሰለሳል ያዝኩ።

ምን ሆና ይሆን? መልሼ መላልሼ ራሴን ጠየቅኩ፤ መልሼ መላልሼም የስልክ ቁጥሯን ቀጠቀጥኩ። ‹‹የደወሉላቸውን ደንበኛ አሁን ማግኘት አይችሉም፤›› የሚለው የኦፕሬተሯ ተስፋ አስቆራጭ ምልእክትም ተደጋገመብኝ። ሥጋቴ ከሰዓቴ ጋር ይቆጥር ጀመር። ወደ ጎረቤት ስልክ ሞከርኩ፤ አይሠራም። የ‹ኔትዎርክ› ችግር መሆኑን ገምቼ ለመረጋጋት ብጥርም፣ ልቤ የእናቴን ሆኗል። በርግጥ፣ ወሮ-በላው ሕወሓት በተቆጣጠራቸው ከተሞች ስልክ አለመሥራቱን ለማወቅ አልዘገየሁም። ወልዲያ በዚያ ቅጽበት ባትያዝም፣ ከመብራት መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ይሁን ወይም የኔትዎርክ ችግር አልፎ አልፎ ነበር። ከጥቂት ቆይታ በኋላ እናቴ መልሳ ደወለች።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*