
ከሦስት ዐመት በፊት በሕዝብ ትግል የተከፈተው የለውጥ ዕድል በብዙዎች ዘንድ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። የዐመታት የትግል ልምድ ያላቸው ፖለቲከኞች ሳይቀሩ ‹የኢትዮጵያ የትግል ታሪክ የፈገግታ ምዕራፍ ተጀመረ!› የሚል ተስፋ ለመሰነቅ አልዘገዩም ነበር። ኹነቱ ግን፣ ከተቋማዊና መዋቅራዊ ለውጥ ይልቅ፤ ግለሰብ ላይ በመንጠልጠሉ፣ በበጎ-መንፈስ የተጀመረው የሽግግሩ ምዕራፍ ሀዲድ ለመሳት ወራት አልፈጀበትም። ዘውጌ- ብሔርተኝነት በነገሠበት ዐውድ የፖለቲካ ሽግግር ፈተናው የበዛ ቢሆንም፤ በኢትዮጵያ የታየው እጅግ የተለየ ነው።
በአንድ በኩል፣ የአገር ምስረታ ሂደቱን እንደዘላቂ የቅራኔ ምንጭ በመቁጠር፣ የ‹‹ጨቋኝ›› Vs ‹‹ተጨቋኝ›› ትርክትን የሚያቀነቅኑ ተቸካዮች፣ ኢትዮጵያን ወደ 1983ቱ ለውጥ ሊመልሷት መጣራቸው፤ በሌላኛው ጫፍ፣ የተነጠቀውን ሥልጣን በቀውስ መልሶ ለመጨበጥ የሞከረው የትሕነግ የጥፋት መስመር፣ ሽግግሩን ከሀዲዱ በማስወጣቱ-ረገድ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳሉ። የዚህ ተቃርኖ ፊት- አውራሪና ለውጡን ተከትሎ፣ በናረ ጉጉት (Rising Expectations) የተጠለፈው ‹ተረኛ ነኝ› ባዩ ኃይል፣ ከመዋቅራዊ ማሻሻያዎች ይልቅ፣ መዋቅራዊ ወረራን መርጧል። በእኩልነት የመቆም ፍርሃቱም፣ ከእኩል ዕድል ይልቅ፤ በልዩ ጥቅምና የብልጫ አስተሳሰብ ኢትዮጵያን መመራት መፈለጉ እንደ አገር ዋጋ እያስከፈለ ነው።
በዚህም፣ ‘ሕዝብ ከህልውና አደጋ ተጠብቆ የልማት፣ የእኩልነትና የነፃነት ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት ገለልተኛና ብቃትን የተመረኮዘ ተቋማዊ አደረጃጀት መገንባት ይቀድማል’ ብለው የሚያምኑና ብልፅግና እንዲመሰረት በብርቱ የታገሉ የ“ለውጡ ተስፈኞች”፣ የረፈደ ጸጸት ይሰማቸው ጀምሯል።
ራሱን “የአቻዎች አውራ” አድርጎ የሰየመው ኃይል ከቤተ-ኢትዮጵያ ይልቅ፤ ኦሮሙማ መደበቂያ ምሽጉ ሆኗል። ትላንት ያልነበረውን ጥያቄ፣ አሁን እየወለደ፤ ዛሬ የሌለውን፣ ለነገ እያማጠ መሄዱ ደግሞ፣ አገሪቱን ወደ ፍርሰት-ጠርዝ ገፍቷታል።
የትሕነግን መገፍተር ተከትሎ፣ በውጭ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎችም ሆኑ በኤርትራ የመሸጉት፡- ኦነግ፣ ኦብነግ፣ ግንቦት ሰባት፣ አዴኃን፣ ደምሒት፣ ጋሕነን፣ አርዱፍ፣ ቤሕነንን የመሳሰሉ ሸማቂ ድርጅቶች ብረታቸውን ሰቅለው አገር ቤት መግባታቸው ይታወሳል። ከእነዚህ ውስጥ ግንቦት ሰባት በውህደት ኢዜማን ሲፈጥር፤ ኦብነግና አዴኃን በፓርቲ-ፖለቲካ ቀጥለዋል። ጋሕነንና አርዱፍ ከይፋዊ የፖለቲካ ተሳትፎ በመታቀባቸው፣ ዛሬ በምን ሁኔታ እንደሚገኙ አይታወቅም። ደምሒትና ቤሕነን ደግሞ ወደሞከሩት የኃይል አማራጭ ተመልሰው “ኢ-መንግሥታዊ ተዋናይ (Non-State Actor)” በመሆን፣ የቀድሞ አሳዳጃቸውን ትሕነግ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።
እንደ አሜባ በመበጣጠስ ራሱን የሚያባዘው ኦነግ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ክንፍ ፈጥሮ ዛሬም ለብይን ቢያስቸግርም፤ “ኦነግ-ሸኔ” በሚል ስያሜ የወለጋ፣ ጉጂና ቦረና ዞኖችን ምሽግ ካደረጋቸው ሦስተኛውን የጸደይ ወራት እያሳለፍን ነው። “አባ ቶርቤ” የሚባለው ኀቡዕ ቡድንም የኦነግ-ሸኔ የከተሞች ወታደራዊ ክንፉ እንደሆነ ልብ ይሏል።
በዚህ ሁሉ ምስቅልቅ፣ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ የ“መደመር” መንገድ፣ “የአደባባይ ፍቱን መድሃኒት” ተብሎ በጅምላ ታዝዞ ነበር። በርግጥ መደመር አገር-በቀል እሳቤ ቢሆንም፤ በሕግም ሆነ በሞራል የመዳኘት ተፈጥሯዊ ባህሪ የሌለውን ትሕነግ ‘ከጥፋት መንገዱ ይመልሰዋል’ በሚል ዕድል መሰጠቱ ከጥፋቶች ሁሉ የከፋው ሆኖ ተመዘግቧል። በተለይ ከሰኔ 16/2010 ዓ.ም የቦንብ ጥቃት በኋላ፣ ያለማቋረጥ የተፈጸሙ የሽብር ድርጊቶቹ ዐቢይ ማሳያዎች ናቸው። የጠቅላዩ የቀውስ ፖለቲካ አያያዝ ውጤትም ኢትዮጵያን አምሳለ-ሶሪያ ለማድረግ ማገዶ አልፈጀም። መሰረታዊው የዜጎች ሰላምና ደህንነት ማስከበርም እንደ ኒዩክለር ሳይንስ ከመጠጠሩ በዘለለ፤ አገሪቱ በዘመናዊ ሰርጎ-ገብ ጦርነት ትታመስ ዘንድ አመቻችቶ አቀብሏል።
Be the first to comment