ቀይ ባህር… ቀይ መቀስ | ሙሉዓለም ገ/መድኀን

የሲ.አይ.ኤ የመረጃ ሰው የነበረው ፖል ሄንዝ በኢትዮጵያ ጉዳይ “Layers of Time: A Histo­ry of Ethiopia” (2000) በሚል ርዕስ ባሰናዳው መጽሐፉ፣ በሦስተኛው ክፍለ-ዘመን የነበረውን “ማኒ” የተባለ የፋርስ ነቢይን ጠቅሶ እንዲህ ይላል፡-

‹‹በዓለም ላይ አራት ትላልቅ ንግሥናዎች አሉ። የመጀመሪያው የባቢሎንና የፋርስ ንግሥና ነው፤ ሁለተኛው የሮም ንግሥና ነው፤ ሦስተኛው የአክሱማውያን ንግሥና ሲሆን፤ አራተኛው ደግሞ የቻይናውያን ነው።››

አራቱም ትላልቅ ንግሥናዎች የኃያልነታቸው መነሻ የሚቆጣጠሩት የተንጣለለው ባህር ስለመሆኑ ታሪካቸው ያስረግጣል።

‹የአክሱም ሥልጣኔ ያበበበት ወርቃማ ዘመን› ተብሎ የሚጠቀሰው ከሦስተኛው እስከ ሰባተኛው ክፍለ ዘመን ያለው ጊዜ፣ ከግብጽና ከሮማ ኢምፓየር ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነቱ የጠነከረበት ነበር። ስርገው ሀብለ ሥላሴም፣ በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነጉሥ የነበረው ኤዛና የተወውን የድንጋይ ላይ ጽሑፍ ተንተርሰው፣ በዚያ ዘመን የአክሱም ግዛት ሰፊ እንደነበረ ዘግበዋል። ስርገው “Ancient and Medieval Ethio­pian History to 1270-1972” በሚለው ዘመን ተሻጋሪ የታሪክ ድርሳናቸው፣ በአክሱም ይወከል የነበረው የኢትዮጵያ ግዛት፣ የአሁኗን ኤርትራን ጨምሮ፤ ከደቡብ ዐረቢያ እስከ ምስራቅ ሱዳን ያካልል እንደነበረ ያትታሉ። በዚህ ሁሉ የታሪክ ሂደት የአክሱም ዕድገትና የሥልጣኔ መሠረት ከሆኑ ምክንያቶች አንዱና ዋነኛው፣ ምዕራባዊና ምስራቃዊ የቀይ ባህር ዳርቻዎችን መቆጣጠር መቻሉ መሆኑንም ያሰምሩበታል፤ (በነገራችን ላይ፣ ‹አክሱም የብቻ ሥልጣኔችን ነው› የሚሉ ጠርዘኛ የትግራይ ልሂቃን፣ በዘመኑ ትግርኛ ቋንቋ ስለመኖሩ የድንጋይ ላይ ጽሑፍም ሆነ ሌላ የታሪክ ማስረጃ ማቅረብ እንደማይችሉ ልብ ይሏል።)

ከባይዘንታይን ግዛት የመጡት የመጀመሪያው ÍÍስ ፍሬምናጦስ፣ ንጉሥ ኢዛናን ክርስትና ካጠመቁበት ከአራተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የአክሱም ሥልጣኔ መሠረቱ ግዕዝ ስለመሆኑ አያሌ የታሪክ ሰነዶች አሉ። የአክሱም ዘመንን ከግዕዝ ስልጣኔ ጋር የሚያዛምዱት እንደ ፕሮፌሰር ተሻለ ጥበቡ ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎችም ‹‹The trinity of the Geʽez civilization (የግዕዝ ሥልጣኔ ሦስቱ ሥላሴ)›› በሚል ዐማራ፣ አገው እና ትግሬ የሥልጣኔው መሰረት እንደሆኑ በጥናታቸው ይገልፃሉ። በርግጥም ግዕዝ፣ ከኢትዮጵያ የሥልጣኔ መሰረቶች ቀዳሚው ስለመሆኑ ነጋሪ አያሻውምና፤ “አክሱም…” ስንል አቢሲኒያ/ኢትዮጵያ እያልን ስለመሆኑ እያሰላሰልን፣ ወደ ቀይ ባህራ እናማትር።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*