
ከሁለት ሳምንት በፊት በተነበበው ዳሰሳችን ቀይ ባህርን ከታሪክ አንጻር አብዝተን መመልከታችን ራሱን የቻለ ምክንያት ነበረው። የወደብ ጉዳይም ሆነ የቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲካና የኢትዮጵያን ግንኙነት በተመለከተ፣ በኢትዮጵያዊያን ላይ ላለፉት ሠላሳ ዐመታት ‹የአዕምሮ እጥበት› ሲሰራበት የቆየ ከመሆኑ ጋር ይያያዛል። ምንም እንኳ ዕድሜቸው ከ40 በላይ የሆኑ ኢትዮጵያዊያን በጉዳዩ ላይ መረዳት፣ ልዩ ትውስታና ቁጭት ቢኖራቸውም፤ የአዕምሮ እጥበቱ ያስከተለው ዝንጋዔ በቀላሉ የሚታይ አይደለምና፤ ምልሰቱን ከቅስቀሳ መጀመሩ አስፈላጊ በመሆኑ ነበር፣ በቅድሚያ ከታሪክ አንጻር የተመለከትነው።
ርግጥ ነው፣ እዚህ ጋ ፈረንጆች “በድልድዩ ስር ብዙ ውሃ ፈሷል፤ (So much water has passed under the bridge)” የሚሉትን አባባል ይዘው፣ ‹በተለወጠ ዓለም የታሪክ ሙግት ዋጋ የለውም› የሚሉ ሊኖሩ እንደሚችሉ ይገመታል። መልሳችን ‹በተለወጠ ዓለም፣ ያልተለወጠ አካባቢ ውስጥ እንደምንኖር› በማስታወስ፣ የቅኝ ግዛት ውርሶችን ለመሻገር መትጋት ይኖርብናል። ከጂኦ- ፖለቲካው አኳያ የሚኖረን የሠላምና ልማት ትብብርንም ሆነ ትስስር ለጋራ ጥቅም በጋራ የምንገነባው ካልሆነ፤ በግጭቶቻችን መነገድ የለመዱ ‹ኒዮ-ኮሎኒያሊስቶች› የሚፈጥሩት ቅራኔዎች እየተባዙ መጠቃቃቱ ይቀጥላል። ዕጣ-ፈንታችን አንድ ስለመሆኑ ለማመን ከዚህ ዘመን በላይ አስረጅ ምሳሌ ያለ አይመስልምና።
ከሕግ ይልቅ፣ የኃይል ሚዛን ላይ የተመሠረተ፣ በፉክክርና በግጭት የታጀበ ፖለቲካ በሚራገብበት የአፍሪቃ ቀንድ፣ አገራቱ በሕብረት ከመቆም ውጭ የተናጠል ሩጫቸው ቀጣናው በመሠረተ-ልማት ሳይሆን፤ በሽብርና ግጭት አስተሳስሮ የእልቂት ማዕከል ከማድረግ የዘለለ አይፈይድም። አንዱ የሌላው ጠላት አስታጣቂና ድህነት ጠባቂ መሆኑ ሊቆም የሚችለው፣ ቀጣናዊ ሕብረትን በላቀ የመተማመን መንፈስ በማሳደግ ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ውህደትን መፍጠር ሲቻል ነው። ለዚህ ደግሞ፣ በቅድሚያ የጋራ ደህንነት ጉዳዮችን፣ በጋራ መልክ ማስያዝ ይጠይቃል። የቀይ ባህርን ቀይ መቀስ መስበር የሚቻለው በጋራ ዐቅም ነውና!
Be the first to comment