
ለዚህ ተከታታይ ጽሑፍ መነሻ የሆነን የተሻሻለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና እሱን ተከትሎ እየታዩ ያሉ ለውጦችን ጨምሮ፤ የአካባቢው እንቅስቃሴዎች፣ ከኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጋር የሚገናኙ በመሆኑ ነው። በሥራ ላይ ያለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንም ከቀይ ባህር ጂኦ-ፖለቲካ አኳያ የሚከተላቸው አቅጣጫዎች፣ ቀጣይ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ፖለቲካ ማጠንጠኛ መሆኑ አይቀሬ ይመስላል።
በዚህ ተጠየቅ፣ ኢትዮጵያ የቀይ ባህር ተዋናይ ለመሆን በምታደርጋቸው እንቅስቃሴዎች ዙሪያ፣ አካባቢያዊና ዓለም ዐቀፋዊ ገች ሁኔታዎችንም ሆነ መውጫ ስትራቴጂዎችን በጨረፍታ ተመልክተን ርዕሰ- ጉዳያችንን እናሳርጋለን።
የቀይ ባህር፣ ገች ሁኔታዎች፡–
ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር ስትመለስ የተዋናይነት መደላድሎቿ የጋራ ወደብ ልማት፣ የባሕር ኃይል እና የባሕር ላይ ደህንነት ጉዳዮች ቀዳሚዎቹ ናቸው። እነዚህን መደላድሎች ሊያደናቅፉ ከሚችሉ ጭብጦች ውስጥም፣ ከዐምዱ ውስንነት አኳያ አራት ነጥቦች ላይ ብቻ እናተኩራለን።
፩
የገልፍ መንግሥታት ወደቦችን በሙሉ የመቆጣጠር ፍላጎት
የቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ተዋሳኝ የአፍሪቃ ቀንድ አገራት የአብዛኛዎቹ የወደብ ልማት በገልፍ መንግሥታት እጅ እየወደቀ መምጣቱ እሙን ነው። ለአብነትም፣ ከኤርትራ አሰብ (በኤምሬቶች DP World)፣ ከሶማሊያ ሞቃዲሾ (በቱርክ Albayrak) እና ሆብዮ (ኳታር Mwani)፣ ከሶማሌ-ላንድ በርበራ (በኤምሬቶች)፣ ከፑንት ላንድ ቦሳሶ (በኤምሬቶች)፣ ከሱዳን ፖርት-ሱዳን (በመንግሥት ያለ) እና ሱዋኪን (ቱርክ እና ኳታር)፣ ከጅቡቲ (ከኤምሬቶች ወደ ቻይና የዞረ በማሪታይም ሲልክ ሮድ ፕሮጀክት የተያዘ)… ተጠቃሽ ናቸው።
Be the first to comment