
ወዳጄ ሙሉዓለም ገ/መድኀን ‹‹ቀይ ባህር… ቀይ መቀስ›› በሚል ርዕስ ተከታታይ ጽሑፍ እያስነበበን ነው። በተለይ የጽሑፉ ሁለተኛ ክፍል፣ ለዚህ መጣጥፍ መነሻ እንደሆነኝ በማስታወስ ወደ አጀንዳዬ እሻገራለሁ።
የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር መስመር የዓለም ኃያላን የስትራቴጂክ ጂኦ-ፖለቲካዊ ቁጥጥር የፉክክር አውድማ ሆኗል። በቀጠናው ላይ የኃይል ሚዛን ብልጫ ለመያዝ የሚያደርጉት ፉክክርና ትብብር፣ በቀጠናው የባሕር ዳርቻዎች የጦር ሠፈር በመመስረት ብቻ የሚገታ አይደለም። ቀጠናዊ ሚናቸውን ለማሳደግና የኃይል ሚዛን ብልጫ ለመያዝ ወዳጅ አገራትንም ከጎን ማሰለፍ የግድ ነውና።
ይሄ የቀጠናው ተፎካካሪዎች ፍላጎት ደግሞ፣ የአፍሪካ ቀንድ አገራት በቀጠናው የሚኖራቸውን ተሳትፎና ሚና ከኃይል ሚዛኑ ጋር የሚያወዛውዝ፣ አልፎም በውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዝ አጣብቂኝ ነው። ኢትዮጵያም በቀይ ባህር ቀጠና የሚኖራትን ጥቅም ለማስከበር እና ከቀጠናው ተፎካካሪ ኃይሎች መካከል የሚኖራት አሰላለፍም ሆነ ተፎካካሪዎች ኢትዮጵያን ከጎናቸው ለማሰለፍ የሚከተሉት ፖሊሲና የሚወስዱት አቋም ወሳኝ ነው።
በቀይ ባሕር ቀጠና ጂኦ-ፖለቲካዊ ፉክክር እያደረጉ የሚገኙትን አገራት በዋናነት ከሁለት ጎራ የሚሰለፉ ናቸው። በአንድ በኩል የቀድሞው የቀዝቃዛ ጦርነት ትዝታን የሚያስታውሰው የምዕራባውያን ጎራን የያዘው፡ – የእነ አሜሪካ፣ አውሮፓ ህብረት እና አባላቱ ሲሆን፤ በሌላኛው ጠርዝ ደግሞ፣ በምስራቅ የምዕራባውያን ስትራቴጂያዊ ተፎካካሪዎች የሆኑት፡- ቻይና፣ ሩሲያ እና አጋሮቻቸው አሉ።
እነዚህ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባሕር ቀጠና ተፎካካሪ የኃያላን ቡድን፣ በቀጠናው የተለያዩ ፍላጎቶች እንዳላቸውም ይታወቃል።
- አሜሪካ Vs ቻይና፣
- አሜሪካ Vs ሩስያ፣
- አውሮፓ ህብረት Vs ቻይና፣
በቀጠናው የኃይል ሚዛንና ተፅዕኖ ብልጫ ፉክክር እያደረጉ ያሉ ናቸው። አገራቱ በቀይ ባሕር እና አፍሪካ ቀንድ ጥብቅ ስትራጂያዊ ጥቅም እንዳላቸውም አይዘነጋም። ከፍተኛው የዓለማችን የባሕር ትራንስፖርት መተላለፊያ እና ታላቁ ስትራቴጂካዊ ቀጠና ነው። እናም ተፎካካሪ አገራቱ የጦር ሠፈሮችን መስርተዋል፣ በቀጠናው ያሉ አገራትን ከጎናቸው ለማሰለፍም ‹ጨንገር› እና ‹ካሮት› ይዘው እየሠሩም እያሴሩም ነው።
በሁለተኛው የቀጠናው ተፎካካሪዎች ምድብ፣ የቅርብና መካከለኛው ምስራቅ አገሮች ጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶች አሰላለፍን የያዘው ነው።
Be the first to comment