
የኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነት ከ120 ዐመት በላይ አስቆጥሯል። በተለይ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ የወዳጅነቱ መሰረት የተጣለበት ነበር። በዚህም ኢትዮጵያ በወታደራዊ፣ በትምህርት፣ በግብርና፣ በጤና… ትርጉም ያለው ድጋፍ አግኝታለች።
የፋሽስት ጣሊያን የአምስት ዐመት ወረራ በ1933 ዓ.ም በአርበኞች ከተቀለበሰ በኋላ፤ አንዳንድ አገራት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማዳከም ያደረጉትን ሙከራ፣ የዐፄው መንግሥት የአሜሪካንን አጋርነት በመጠቀም ማክሸፉም ይታወሳል። ይህ የውጭ ጉዳይ ባህል፣ ሌሎች ነፃነታቸውን ጠብቀው የኖሩ አገራት የተጠቀሙበት ቢሆንም፤ የአሜሪካንን አጋርነት አጉልቶ ያሳየ ነበር። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ መስራች ብትሆንም፤ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእርዳታና የማቋቋሚያ አስተዳደር ተጠቃሚ መሆን የቻለችውም በአሜሪካ አጋርነት ነበር።
ኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ ፀረ-አፓርታይድ እና ፀረ-ቅኝ አገዛዝ የትግል ታሪክ የነበራት ተሳትፎና ተጽእኖ ከአህጉሩም ተሻግሮ፤ ለሌሎች አገራት በአርአያነት ይጠቀሳል። ይህንን የታሪክ ሀዲድ አስጠብቃ መጓዝ በመቻሏም ነበር፣ በኮሪያ ዘመቻ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከአሜሪካና ሌሎች የተባበሩት ኃይሎች ጋር ለኮሪያውያን ነፃነት የተዋደቁት። ይህ ገድል፣ በተራ የፖለቲካ ኃይሎች አሰላለፍ የተፈጠረ ሳይሆን፤ ለዓለም ሕዝቦች የነፃነት ተምሳሌት የመሆን የታሪክ አስገዳጅነት ያመጣው ዕድል ነበር። በርግጥም ይህ የነፃነት ጥብቅና ነው፣ የኢትየጵያና የአሜሪካ ወታደሮችን ከጥምር ጦሩ ጋር በአንድ ምሽግ አውሎ-ያሳደረው።
Be the first to comment