ቤዛ ኩሉ እና ቀራኒዮ | ተመስገን ደሳለኝ

አሃዛብነቱም፣ ልማዳዊ እምነቱም፣ ኦሪቱም፣ ክርስትናውም፣ እስልምናውም የተጫናት ኢትዮጵያችን፣ እንደ ዘመናዮቹ አገራት፣ ‘መንግሥትና ሃይማኖት’ መለያየታቸውን ብትደነግግም፤ በ‘ስብሐት ለአብ’ ጀምሮ፣ በ‘ስብሓት ነጋ’ መጨረስን መፍቀዷ የቅርብ ትውስታ ነው። ሕግጋቶቿም ሆኑ ድንጋጌዎቿ ‘አቡኑ’ን፣ ከ‘አቦይ’ እንዳላራቁ ሁሉ፤ ከ‘ኦቦ’ ለመነጠል ዐቅም-የለሽ ናቸው። በመጂሊስና በመንግሥት መሃል ዐጥሩ ፈርሷል። በቆብ የከሸፈውን፣ በቄሮ መሞከር የትግል ስልት ነው። ከ‘ንዋየ-ክርስቶስ’፣ የ‘መወዓለ-ንዋይ’ ተከታይ ብዙ ሺሕ አስከንድቷል። ፓስተሩ፣ ፓርቲውንም አገሩንም ይዘውታል። ሰማያዊነት ነጥፎ፣ ዓለማዊነት ገንኗል። መንፈሳዊነት ተነቅሎ፣ መናፍስቱ ተተክለዋል።

የሮማው ፖፕ ፍራንሲስ ይመስከሩ! እ.ኤ.አ. በታኀሣሥ 1936 ዓ.ም በአርጀንቲና ዋና ከተማ፣ ቦነስ አይረስ በድኾች መንደር የተወለዱት 266ኛው የካቶሊካ ቤተ-ክርስቲያን መሪ፣ በዓለም ዙሪያ ባሉ የእምነቱ ተከታዮች ከተመረጡ ስምንት ዐመት ዐልፏቸዋል። እኒህ የ85 ዐመት አዛውንት በቫቲካን ላይ የተሾሙ የመጀመሪያው ላቲን አሜሪካዊ መሆናቸው በታሪክ ተመዝግቧል። ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ አስተዳደርን ቀላቅለው የሚመሩት ተቋም፣ የተባበሩት መንግሥታትን ጭምር ዘቅዝቆ የሚያይ ከበርቴ ቢሆንም፤ ‘ወርሃዊ ደመወዛቸው 2,500 ዩሮ ብቻ ነው’ የሚለው የጣሊያኑ “La Stampa” ጋዜጣ ነው። ዓለማዊ ኑሯቸውም በወንጌሉ እንድምታ ስለመበየኑ መእምናኑ ምስክረዋል። ጥቂት የማይባሉ አገራት በ‘ካሮትና ብትር’ የገበሩለትን የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻንም፣ በምዕራቡ ‘ጂኦግራፊ’ እና ሤራ እምብርት ላይ ተደላድለው፣ “የዲያብሎስ ሥራ፣” ብለው ያወገዙበት ድፍረት፣ እኒያን ተጋፋጭ የብሉይ ነብያት አስታውሷል። እ.አ.ኤ በ2019 በጄኔቫ በተካሄደው የ‘ዓለም ቤተ-ክርስቲያን ካውንስል’ መድረክም፣ በሃይማኖት መሪዎች ዘንድ መንፈሳዊነት መንጠፉን አክርረው ሲገስጹ ተመልክተናል፦

“…ሁላችንም እንደ ክርስቶስ ደቀ-መዝሙርነታችን ዐብረን መፀለይ፣ ዐብረን መስበክና ዐብረን ማገልገል እንችላለን። በእኛ በክርስቲያኖች መሃል ልዩነት የመጣው ከሥር-ከመሠረታችን ዓለማዊ ጥያቄዎች ሠርገውብን ስለገቡ ነው። ራስ-ወዳድነት ለክርስቶስ ከመታምን በፊት ቀድሟል። ለዚህም ነው፣ ሰይጣን እኛን ለመለያየት የቀለለው። […] እነሆ፣ ክርስቶስ ከውስጣችን ሆኖ በር እያንኳኳ ነው፣ ወደ ውጭ እንድናስወጣው። ራሷን ብቻ የምትመለከት ቤተ-ክርስቲያን ግን ክርስቶስን እውስጥዋ በር ቆልፋበት አላስወጣም ብለዋለች። የቅድስና በሽታችን ምንጭ የቤተ-ክርስቲያኗ በራስ መጠመድ ነው። ‘እኔ አልፋም፣ ኦሜጋ ነኝ’ በማለቷም፣ በደጀ-ሰላሟ መንፈሳዊ-ዓለማዊነት ተንሰራፍቷል። የአገልጋዮቿ ሥራም ለዝና መኖር ሆኗል። […] ክርስቶስን መከተል በአብዛኛው በዘርና በፓርቲ ለተተበተቡ ግለሰባዊ ስብስቦች ቦታ የለውም።”

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*