
ለሁለት ተከፍሎ የነበረውን የሲኖዶሱን አንድነት ለመመለስ በተደረገው ጥረት፣ ብልጽግና ድጋፍ ማድረጉ እውነት ነው። “ቤተ-ክርስቲያን አገር ናት” እስከማለት የደረሰ ምስክርነት መስጠቱም እውነት ነው። ታዲያ፣ ይህን ላስተዋለ፣ ዛሬ በቤተ-ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለው ፖለቲካዊ ጫና የጠበቀው ባይሆን አይፈረድበትም። ርግጥ፣ ብልጽግና፣ የሃይማኖት እና የመንግሥትን መለያየት በተመለከተ ያለው አረዳድ፣ የሕወሓትን “ክፉ ውርስ” እንደወረደ መተግበር መሆኑ ዘግይቶ ተገልጧል። ባፈጠጠ ጣልቃ-ገብነት ቤተ-ክርስቲያኗን የማኮስመን ቅብብሎሽ አስፋፍቶ አስቀጥሎታልና። ነገሩን ለጥጠን ካየነው ደግሞ፣ በ“ብልጽግና” ሽፋን የአንድ እምነት አስተምህሮ እና ፖለቲካን አዛነቆ የማስኬድ ኀቡዕ ስልት ሊሆን ይችላል።
በዚህ ዐውድ፣ ይቺ “ጥበብ” ከየት ናት? ከቀኝ ወይስ ከግራ? ብልጽግና ቤተ-ክርስቲያኗን የሚመለከትበት የፖለቲካ ንጻሬ (perspective) ስረ-ነገር ከየት ነኝ ይላል? ማሳያዎችስ አሉት ወይ? የሚሉትን ጥያቄዎች በጨረፍታ እንመለከታለን።
የዘውግ–ፖለቲካ ቁልቁለት የመጨረሻው መጀመሪያ
ግራ-ዘመሙ የዘውግ-ፖለቲካ በርዕዮተ-ዓለም እና በሀሳብ ድርቀት ከገረጣ ሰንብቷል። ሕወሓት፣ ኢትዮጵያን በራሱ ርዕዮተ-ዓለም አምሳል ለመግራት የሄደበት ርቀት ለማይታረም ስህተት ሲዳርገው፤ ወራሹን ብልጽግናን ደግሞ መንታ መንገድ ላይ አንቀዋልሎታል። ይህም ሆኖ፣ ከገባበት ቅርቃር ለመውጣት ሁለት አማራጭ አለው። አንደኛው፣ አገሪቱ በሕወሓት ባቡር፣ ሃዲድ የሳተችበትን ቁልቁለት የሚቀለብስ አቅጣጫ ቀያሪና ስር-ነቀል ለውጥ ማድረግ ነው። ለዚህም ከሕገ-መንግሥታዊና መዋቅራዊ ማሻሻያ በተጨማሪ፤ የተዛባውን ትርክት አስተካክሎ፣ በሕዝብ ለሕዝብ መግባባትና ማዋለድ ላይ መቃኘት ይቀድማል። ሁለተኛው፣ የአክራሪ ዘውገኞችን መስመር በማጥበቅ፣ በተያያዘው ቁልቁለት ተንደርድሮ የሕወሓትን ጎምዛዛ ጽዋ መጎንጨት ነው። ይህ እንዳይሆን ምኞቴ ነው።
Be the first to comment