ትግራይ የመከራ ደሴት… | ኦሃድ ቤንአሚ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ሥራ-አስፈፃሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እና የክልሉ የማኀበራዊ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብራሃ ደስታ፣ በዐማራ እና ትግራይ መካከል ውዝግብ የፈጠሩትን መሬቶች በተመለከተ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ “አንድ ኢንች እንኳን ብትወሰድ!?” የሚሉ ማስጠንቀቂያዎችን አስተላፈዋል።

ይህ ቀጣይ ኹነት…

በሕዝባዊ የተዓማኒነት ጥያቄዎችና ቁጣ ወደ መቃብሩ የተገፋው ሕወሓት፣ በአገዛዝ ዘመኑ ዐሥር ጊዜ እያሰፋ ያመጣው ካርታም ሆነ የወሰን ጉዳይ፣ በዐማራ እና ትግራይ ክልል ሕዝቦች መካከል በቀላሉ ሊፈታ ያልቻለ የቅራኔ ውርስ (ሌጋሲ) ትቶላቸው ማለፉ፣ መከራውን ተራዛሚ አድርጎታል።

ዛሬ ስለ ሕወሓት ሲሰሙ የሚሰቀጥጣቸው ኢትዮጵያውያን ብዙ ናቸው። በርግጥም ትግራይ ውስጥ ካሉት ከንፈር መጣጮቹ በቀር፤ አስገድዶ ወደ ሥልጣን እንደመጣው ሁሉ፣ ተገዶ የወረደውን ፓርቲ ግብዓተ- መሬት ማየት ለሚሊዮኖች ኢትዮጵያውያን ትልቅ እፎይታ ነው። ጎረቤት አገራትም እንኳ ከባድ ሸክም እንደወረደላቸው ደጋግመው ገልጸዋል። ይህም ሆኖ፣ ነገሮችን በውይይትና በሰላማዊ መንገዶች የመፍታት ባሕል ፈጽሞ ሳያዳብር ሞት የቀደመው ሕወሓት፣ በርካታ የቤት ሥራዎችን ትቶልናል ሄዷል። ዋንኛው፣ በመሬትና በወሰን የሚናቆሩ ክልሎችን እንደ ሰዓት ፈንጅ ማጥመዱ ሲሆን፤ ቅራኔዎቹ ከፓርቲው ወደ ሕዝቡ እንዲሰርጉ ማድረጉ ደግሞ አደጋውን የበዛ ያደርገዋል።

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጋሩ፣ ከሕወሓት ሌጋሲዎች ከወረሷቸው አሉታዊ ነገሮች መካከል፣ የመጀመሪያው ዐማራ-ጠልነት ነው። ይህ አመለካከትም በሂደት እያደገ ሄዶ የፓርቲው ጀምበር መጥለቅ ስትጀምር ወደ ኢትዮጵያ-ጠልነት ተሸጋግሯል። ለዚህም ነው፣ የሦስተኛው ወያኔ ትውልድ (“ሳልሳዊ ወያኔ”) አባል የሆነውና የትግራይ ሚዲያ ሃውስ (TMH) ጋዜጠኛ ስታሊን ገ/እግዚአብሔር፡-

‹‹የእኔ ትውልድ የሚኮራበት አንዱ ነገር፣ ኢትዮጵያ ስትፈርስ በዐይኔ ማየቴ ነው፤ ዝም ብሎ በፕሮፖጋንዳ ምናምን አይደለም፤ በተግባር ነው ስትፈርስ ያየኋት። ይህ ያኮራኛል፤›› ሲል በአደባባይ ለመናገር የደፈረው።

በትግራይ እና በኢትዮጵያ ጉዳይ ትልቁ ክፍተት በርካታ ተጋሩ ችግሩን እንደ ችግር ያለመመልከታቸው አባዜ ነው። በተለይ ደግሞ “ልሂቃኖቹ” ሙያዊ፣ አካዳሚያዊና ፖለቲካዊ ልምዳቸውን ተጠቅመው፣ እነዚህን ሁለት የሕወሓት ውርሶችን ምንነት ፈትሸው ለማየት ፍላጎቱም፣ ድፍረቱም እንደሌላቸው በበቂ ታዝበናል። ዛሬ፣ ትግራይ የመከራ ደሴት ሆና የመገኘቷ ምስጢርም ይኼው ነው። ልሂቃኑ፣ ሕወሓትን እንደ ፓርቲ፡- የፖለቲካ ባሕሉን፣ አመራሩን፣ የአመራር ብቃቱን፣ የሞራል ደረጃውን፣ የሥነ-ምግባር ጥንካሬውንና ተዛማጅ ጉዳዮችን መዝኖ፤ ሕዝብን መምራት የሚያስችለው መሆኑ-አለመሆኑን የመመርመር ፈቃደኛነቱ ፈጽሞ የላቸውም።

በሌላም በኩል፣ እውን የትግራይ ሕዝብ፣ የመከራ ደሴት አድርጎት የሄደው ፓርቲ ይመጥነዋል ወይ? የሚለውን ጥያቄ የማንሳት አብርሆቱም ነጥፎባቸዋል።

ፓርቲው ራሱ ለ25 ዐመታት በተቆጣጠረው የፖለቲካ መዋቅር ውስጥ ሆኖ፣ እነዚህን ነገሮች የማረም ፍላጎት አልነበረውም። በተቃራኒው፣ ሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎችንም የዚህ ልክፍት ሰለባ አድርጓቸው ነው ያለፈው። ነገሩን ቧልት የሚደርገው ደግሞ ፖለቲካዊ ፍልስፍናው፣ ራሱ ሕወሓትን እንኳ ከቆሞ-ቀርነትም ሆነ ከአሳዛኝ አሟሟቱ እንዳልታደገው እያዩ፤ ዛሬም በእዛው እሳቤ መከንተራቸው ነው።

የብራው መብረቅ…

የሕወሓት ድንገት ባልታሰበና ባልተጠበቀ ፍጥነት ከምስራቅ አፍሪቃ የተጽዕኖ አምባ ወድቆ፣ በተከዜ በረሃ ሸለቆዎች ተሰባብሮ መውድቅ ለኢትዮጵያውያን ግርምት የፈጠረ ጉዳይ ሲሆን፤ በየዕለቱ ስለ ሕወሓት ገድል መስማት ለማይሰለቻቸው ደጋፊዎቹ ደግሞ እስካሁን ያልነቁበት ድንጋጤ ውስጥ የነከራቸው መብረቃዊ ዱብ- እዳ ሆኗል። በርግጥ የመሐል አገር ሰዎችም ‹ሕወሓት ተመልሶ ሊመጣ ይችላል› በሚል ሥጋት፣ እውነቱን ለመቀበል በርካታ ወራቶችን እንደፈጀባቸው የማይረሳ ትዝታ ነው።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*