ትግሬ እና ዐማራን የማፋለሙ ቁማር (ተረኝነት ወይስ ዘጭ-እንቦጭ?)

(ያለፈው ሳምንት ትርክት በይደር የቆየው፣ ታዬ “የሕዝብ-ሙስሊም መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ” አባል ኡስታዝ ኑሩ ቱርኪን በመጥረቢያ መቶት ነው።)

…“ኃይል የእግዚአብሔር ነው!” እየተባሉ ያደጉበትን አማናዊ፡- “መስመር ነው ኃይል!” በሚል ኑፋቄ የቀየሩ ሕወሓቶች፣ የሙስሊሙን መሪዎች ወደ መሰዊያው ገፍትረዋቸው፣ አላሃ አትርፏቸዋል። እንደተደገሰለት ኑሩ ቱርኪ ወይም አዲስ አበባ ከታሰሩት አንዳቸው አልፈው ቢሆን፣ ፀፀቱ አይጣል ነበር። በተረፈ፣ ዋጋ የከፈሉለት ትግል፣ በሕዝብ ዘንድ የክብር ስፍራ ቢኖረውም፤ በጥያቄው ልክ ውጤት ማስገኘቱን አላውቅም። በድኀረ-ፍቺውም የኮሚቴው አባላት በቡድን ሲሠሩ ብዙ አላገጠመኝም። ወይም ኮሚቴው ሥራውን ጨርሶ ስለመበተኑ አልሰማሁም።

በነገራችን ላይ፣ ሐምሌ 11/2004 ዓ.ም “ፍትሕ ጋዜጣ”ን ከሠላሳ ሺሕ ኮፒ ጋር ያቃጠላት ፍርደ-ገምድል፡- የአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈትን ጨምሮ፤ ኡስታዝ አቡበክር አህመድ እና ኡስታዝ አህመዲን ጀበል በታሰሩበት ዋዜማ ያደረገችላቸው ቃለ-መጠይቅ፣ እንዳይታተም መንግሥት ያቀረበውን ጥያቄ ባለመቀበሏ ነው። አስታውሳለሁ፣ በዕለቱ ዝግጅት ክፍሉ በማያውቀው ምክንያት ባለመውጣቷ፣ ብርሃናና ሰላም ማተሚያ ቤት አመራን። ዋና ሥራ-አስፈጻሚዋ ወ/ሮ ማዕዛ በደህነነት መስሪያ ቤት እና በፍትሕ ሚንስቴር ተወካዮች ታጅበው እየጠበቁን ነው። ከአንድ ሰዓት በላይ ብንወያይም ልንስማማ አልቻልንም። ከሰዓት በኋላ ደግሞ፣ የፍትሕ ሚኒስቴር ፈላጭ-ቆራጭ የነበረው አቶ ሚኬሌ፣ ጋዜጣው ከሚዘጋ ሁለቱ ዘገባዎች ባይታተሙ የተሻለ ስለመሆኑ ለማሳመን ሞክሮ አልተሳካለትም።

ይህ ክስተት እዚህ ጋ የተነሳበት መግፍኤ የሕዝበ[1]ሙስሊሙ ትግል፣ ከእምነቱ ተከታዮች በተጨማሪ፤ አያሌ ኢትዮጵያዊያንም ዋጋ የከፈሉበት በመሆኑ፡- ምን ዐይነት ምላሽ አስገኘ? ብሎ የመጠየቅ ሞራል ስላላቸው ነው። በወቅቱ፣ ከሙስሊሙ ጎን መቆምን ያስገደደው አመክንዮም፣ መስኪድ ውስጥ ያለ ‘injustice’፣ ለቤተ[1]ክርስቲያን ‘justice’ ባለመሆኑ እንደነበረ ማስታወሱ፣ ለመርህ መገዛትን ያበረታታል።

በወሽመጥ ስናወራ ደግሞ፣ የ2010ሩ ለውጥ ጥያቄውን ጥሎ፣ ጥቂት ተወካዮቹን አንጠልጥሎ አጀንዳውን ማምከኑ ያብሰለስለናል። ያ ሁሉ ህማማትም ከፎቶ[1]ግራፍ ባሻገር፤ መጅሊሱን ተቋማዊ ማድረግ ስለምን ተሰናው? የሕዝባዊ መንግሥት ጥያቄስ እንዴት ተጠለፈ? ብሎ መምከሩ፣ ከዳግም ስህተት ይታደግ ይሆናል። ጉድ እኮ ነው! ዐዲሱ ኢሕአዴግ በሰንበት ክርስቲያን፣ በጁማ ሙስሊም እየመሰለ ስንቱን አሳተው?! አሁን ደግሞ የ“ኢየሱስ ወታደር” ነው። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ፣ ለእነ አቦይ ስብሃት የእስር ቤቱን በር እንዲከፍቱ ጌታ እንዳዘዛቸው “አብስረውናል”። ከንቲባ አዳነች አበቤም የመንግሥት ሚዲያዎችን አስከትላ፣ ለዐደባባይ አምልኮ የመክፈቻ ንግግር ትሽቀዳደማለች። የኦሮሚያ ፖሊስ ደግሞ፣ ‘እኔ ያልወደድኩትን ለብሳችኋል’ የሚል ቀይ ሽብር አውጇል። ታዳጊዎቹ ግን፣ ደመ-ከልብ ሆነው ቀሩ ማለት ነው?!

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*