ንጉሥ ወይስ አፈ-ንጉሥ | በተመስገን ደሳለኝ

ኢትዮጵያ በተራዘመ ታሪኳ የበዙ መንገራገጮችን ተሻግራለች። አስጨናቂ ሾለቆዎችንም አቋርጣለች። የሥርዐት ለውጥን ተንተርሰው በመጡ መደነቃቀፎች ደግሞ፣ ክቡድ ዋጋ ከፍላለች። ከቅርቡ፣ ከድኀረ-ዘውዱ ብንቆጥር እንኳ፣ አያሌ የመቃብር ጉድጓዶችን እንጋፈጣለን።

በዚህ ዐውድ፣ ከነገ በስቲያ የሚመጣው፣ የዛሬው የብልጽግና መንግሥት፣ ከቀዳሚዎቹ የሚጋራቸውን መለዮዎችና ያጨለማቸውን የተስፋ ቃሎች በወፍ-በረር እናያለን። ኢትዮጵያ-ጠሉን ሕወሓት እንዳልተፈጠረ ቆጥረን፤ በሁለቱ ኮሎኔሎች የመጀመሪያ ሰሞናት ምስስሎሽ እንደረደራለን፤ (በመጋቢት 2013 ዓ.ም “ሕዝባዊ መንግሥት” በሚል ርዕስ ካሰናዳሁት የተበደርኳቸው ማሳያዎች መካተታቸውንም ልብ ይሏል።)

ከግማሽ ክፍል ዘመን በላይ የተቀነቀነው የ‹ሕዝባዊ መንግሥት› ጥያቄ፣ ወድቆ-እየተነሳ ለዛሬ መደረሱ ርግጥ ነው። ጉልበታም ገዥዎች የዐደባባይ ጩኸቱን እሪ-በከንቱ ማድረጋቸውንም ሆነ የለውጥን ፉርጎ ከሀዲዱ ነጥለው ማክሸፋቸውን መዘንጋቱ አይቻለንም። በዓማላይ ሽንገላዎችና በማይጨበጡ ተስፋዎች ሥልጣናቸውን አጠናክረው ሲያበቁ፤ ለዜጎች የክብር ሥፍራ የሌለው መንግሥት ማንብርን ተላምደውታልና። የክስተቱ መደጋገም ደግሞ “ታሪክ ታኮ-የለሽ ነው” የሚል ጥቅስ ወዳነበብንበት ገጽ ይወስደናል።

1966

ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ ሥልጣን በመጡባቸው የመጀመሪያ ሁለት ዐመት በታላቅ ‹ትህትና› ምክር ጠያቂ፣ የአስተዳደራቸው አሳታፊ፣ የሕዝባዊ መንግሥት ተቆርቋሪ፣ የዴሞክራሲ መብቶች ሰባኪ… ገጸ-ባህሪን ተላብሰው መተወናቸው፣ የገዛ ጓዶቻቸውንም ሳይቀር ወደ መሰቀያቸው እስኪገፈተሩ ድረስ አደንዝዟቸዋል። በህይወት የተረፈትም ቢሆኑ፣ በመንጌ “ንጉሠ-ነገሥትነት” ታምነው፣ ለተደለደሉበት የሥልጣን ቦታ ካዳሚ ከመሆን የተለየ ዕጣ-ፈንታ አልነበራቸውም።

በርግጥ ጓድ መንግሥቱ ያመከኑት ዕድል፣ ሕዝባዊ መንግሥት ለመመስረት፣ ቢያንስ በሁለት ነገር ከእነ መለስ ዜናዊ የተሻለና ለትግበራም የቀረበ ነበር። የመጀመሪያው ወደሥልጣን የተስፈነጠሩት በተበታተነ መልክ የተካሄደ የከተማ ተቃውሞን ጠልፈው እንጂ፤ የተደራጀ የፖለቲካ ኃይል ፈጥረው ወይም በትጥቅ ትግል አለመሆኑ ነው። ሁለተኛው አራት ኪሎን ከመርገጣቸው በፊት፣ “መንግሥት እሆናለሁ” በሚል ያዘጋጁት ፍኖተ- ካርታ አለመኖሩ ነው። እናም የፖለቲካው ሳይንስ እነዚህን ጉዳዮች “ጉድለት” ብሎ መንቀፉ እንደተጠበቀ፤ ሁሉን ዐቀፍ አሳታፊ የሽግግር መንግሥት ለመመስረትና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ መደላድል ለማበጀት አመቺነቱ ግን አያከራክርም። “የተሰዋንለት”፣ “የወከለን ሕዝብ የሰጠን አደራ”፣ “ድርጅቴ…” ቅብጥርሶ ከሚሉ አነታራኪ አጀንዳዎች፣ ብዙ ኪሎ ሜትር የራቀ ነውና።

Continue reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*