አርግቦተ-ብሔረተኝነት (ዲ-ኤቲኒሳይዜሽን) – ኦሃድ ቤንአሚ

“ጠላት በሕዝቡ ውስጥ የቀበረው፣ የዘራውና የበተነው ብዙ መቅሰፍት አለ። አንዳንዱን መዋቅራዊ አድርጎታል፤ አንዳንዱን የሕግ ቅርጽ ሰጥቶታል፤ ለአንዳንዱ ሥርዐት ሠርቶለታል፤ ሌላውን በትምህርት ሥርዐቱ ውስጥ አካትቶታል፤ ለአንዳንዱ በዓል ሰይሞለታል፤ ለሌላው ሚዲያ አዘጋጅቶለታል። ለአንዳንዱ ተቋም አቁሞለታል። አንዳንዱ የሕዝቡ ትርክት ሆኗል፤ ሌላው በዘፈን ውስጥ ገብቷል፣ ሌላውም የፓርቲ ፕሮግራም ሆኗል። ይሄን ሁሉ ዱካ በዱካ እየተከተልን የዕዳ ደብደቤውን መደምሰስ ይጠበቅብናል።” – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ግንቦት 1983 ዓ.ም፣ ቦታው አለማያ ዩኒቨርሲቲ ነው፤ ኢሕአዴግ አዲስ አበባ ከገባ ከጥቂት ቀናት በኋላ ተራ-በተራ ከተሞችን እየተቆጣጠረና ዓላማውን እያራመደ ነው፤ ያን ቀን ተራው የአለማያ ዩኒቨርሲቲ በመሆኑ፣ ተማሪዎች ወደ አዳራሽ እንዲገቡ ስለተነገራቸው፣ ግራ እየተጋቡ መጥተዋል፤ ምን እንዳሰበና ምን ይዞ እንደመጣላቸው ወይም እንደመጣባቸው የሚያውቁት ነገር የለም። የወጣቶችን የማወቅ ፍላጎት ሊያሟላና ነገን ፍንትው አድርጎ ሊያሳይ የሚችል ማብራሪያ መጠየቅ የሚጠበቅ ነው፤ አዳራሹ ውጥረት ሰፍኖበታል፤ መድረኩ ላይ ከተዘጋጀላቸው አግዳሚ ጠረጴዛ ጀርባ ፊልድ ጃኬትና ካኪ ኮት የለበሱ ሦስት ካድሬዎች ተቀምጠዋል፤ አንገታቸው በዥጉርጉሩ ሽርጣቸው ተከብቧል፤ በርግጥ፣ የውጥረቱ መነሾ ፊልድ ጃኬታቸውና ሽርጣቸው አይደለም፤ በጠረጴዛው ግራ እና ቀኝ ወደ ተማሪዎቹ የተደገኑት መትረየሶች እንጂ። አንዳች የተቃውሞ ድምጽ ከተሰማ እሳት አርከፍክፈው፣ ሞት ሊተፉ የቸኮሉ ይመስላሉ።

ካድሬዎቹ መድረኩ ላይ ተሰይመው ወደ አዳራሹ በሚገቡ ወጣቶች ላይ ዓይኖቻቸውን ተክለዋል፤ መምህራኑ ከፊት፣ ተማሪዎቹ ከኋላ በረድፍ ተቀምጠዋል፤ ወንበሮች በመሙላታቸውም መረማመጃ ቦታዎች ላይ ተኮልኩለው ቆመዋል፤ የአዳራሹ ሙቀት ውጥረቱን አክብዶታል።

ካድሬዎቹ እየተቀባበሉ በስሜት የታጨቀ፣ በበቀል የተለበለበ፣ በበረሃ የደለበ ክፋትን ያዘለና በጥላቻ የተጠመቀ ንግግር አደረጉ። አለማያ ኦሮሞ ተማሪዎች እንደሚበዙበት ታሳቢ ያደረገው ቅስቀሳቸው ጥቅል ዓላማ፣ የኦሮሞ ወጣቶችን ሥነ-ልቦና በአሉታዊ ቃላቶች በመለኮስ ጥላቻን መመገብ ነበር። ከካድሬዎቹ አንደበት ለጽሑፍ የማይመቹ በርካታ የጥላቻ ሃረጎች ተተኩሰዋል። አንዱ ብሔር በዳይ፣ ሌላው ተበዳይ ሆነው ለጆሮ በሚከብዱና ወጣቶቹ ሊቋቋሟቸው በማይችሉት መርዛማ ቃላቶች ተቀምመው ወደ አእምሮአቸው እንዲሰርጉ ካአደረጉ በኋላ፣ ስብሰባው አለቀ። “ለማንኛውም” በሚል ይመስላል፣ ታጋዮቹ ወደ መትረየሶቹ ጠጋ-ጠጋ ብለው ቆሙ። ወጣቱም በስጋት ወደኋላው እየተገላመጠ ወጣ። ረበሸ ቀርቶ፣ ትንፍሽ ያለ አልነበረም። መትረየስ ደግነው ጥላቻን ግተዋቸውና ስብዕናቸውን ተዳፍረው ወጡ። ከዩኒቨርስቲ የእውቀት ቅብብሎሽ መርህ ባፈነገጠና የተለየ ሃሳብን ላለመቀበል ባስረገጠ አደፍራሽ መልዕክት “እንኳን ደህና መጣችሁ!” ያልተባሉት በረኸኞቹ፡- ‹ወደዳችሁም ጠላችሁም መንገዳችን የሄ ነው›፤ ሲሉ ፎከሩ። “ለምን ይሄን ትነግሩናላችሁ? ያላችሁት ሁሉ ትክክል አይመስለንም፤ ብዙ ግድፈቶች አሉበት፤ ለምን ስለወገኖቻችን ክፉ ነገሮችን ትነግሩናላችሁ? የሚያጣሉንን ከምትነግሩን፣ ነገን የተሻለ የሚያደርግ ይዛችሁ ከመጣችሁ እሱን ንገሩን፤” የሚል ቢኖር ምላሽ የሚሰጡት መትረየሶች ይሆኑ ነበር? ብዬ ዛሬ ድረስ አውጠነጥናለሁ።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*