አባ ተኛ

አብዮት አሃዶች፣ ከሥርዐታዊ ለውጥ አማጪነታቸው ባሸገር፤ ማኀበራዊ ፍዘትንም፣ የማነቃቃት ጉልበት አላቸው። በአገር ጉዳይ ‘ምን አገባኝ’ የሚል ህብረተሰብን፣ ንቁ ተሳታፊ ያደርጋሉ። ይህ ብያኔ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ “ሠርቷል” ማለት ግን ይቸግራል። በ1960ዎቹ የተቀነቀኑ ጥያቄዎች፣ ዛሬም ጠረጴዛው ላይ ናቸው። ኃይለሥላሴን እና መንግሥቱ ኃይለማርያምን የተቃወሙት እነ ዳውድ ኢብሳ፣ ዛሬም ተቃዋሚ ናቸው። ደርግን የታገሉት እነ ጄነራል ጻድቃን፣ ዛሬም ብልፅግናን እየታገሉ ነው።

በግርድፉ፣ በ“ያ ትውልድ” እና በእዚህ ትውልድ መሀል ያለው ሽግግር፣ ከየካቲት ወደ መጋቢት ነው ማለት ይቻላል። ከተለምዷዊው የቀን አቆጣጠር በቀር፣ የረባ ለውጥ አልታየበትም። በየካቲት አብዮት እነ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደ አራት ኪሎ ሲንደረደሩ፤ በመጋቢቱ የኢሕአዴግ ስንጥቃት እነ ኮሎኔል ዐቢይ አሕመድ አራት ኪሎ ደርሰዋል። የክስተቱን ቆይታ ለማስላታም፣ ግማሽ ክፍለ ዘመን ከተቆጠረበት ካላንደር ይልቅ፤ ወጥተው-የወረዱት ያሳኩትን እና ያጎደሉትን የኦዲት ሪፖርት መፈተሹ የተሻለ እውነት ነው።

ይህም ሆኖ፣ ለከሸፉት ወርቃማ ዕድሎች፣ በየዘመኑ “ቀራኒዮ” ዋጋ የከፈለው ግልቱው ሕዝብ ራሱ የማይናቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለደመ-ቀዝቃዛ አምባ-ገነኖች በአድፋጭነቱም ሆነ በአጨብጫቢነቱ መደላድል ፈጥሯል። የትላንቱን ስህተት ዛሬ እየደገመ፣ የገዛ ንጋቱን ስለማጨለሙም ደጋግመን ቆዝመናል።

ምን ማለት ነው? በኢትዮጵያ ፖለቲካ “አባ ብላ” ይነግሥ ዘንድ፣ “አባ ተኛ”ም ድርሻ አለው። የወደቁትን ትተን፣ የቆመውን ብንገመግም እንኳ፣ ያለፉት ሦስት ዐመት በምንግዴ የታለፉ አገራዊ አጀንዳዎች፣ ስለሕዝባዊ ድባቴውም ሆነ ስለሥር-ሰደዱ አድርባይነት በበቂ ይነግሩናል።

ከቡራዩ እስከ ከረዩ፣ ከጭልጋ እስከ ወለጋ፣ ከጉራ ፈርዳ እስከ ኮዬ ፈጬ፣ ከባሌ እስከ ኮፈሌ፣ ከሐረር እስከ ሙገር፣ ከጌዶ እስከ ደንቢዶሎ፣ ከቤንሻንጉል እስከ አጣዬ፣ ከአዳማ እስከ ሲዳማ… የፈሰሰው ደም፣ የተፈናቀለው ሕዝብ ‘ፍትሕ አገኘ ወይ?’ ብሎ የጠየቀ ስለመኖሩ አልሰማሁም። በችግሮቹ መነሾ ላይም በምልዓት አለመስማማቱ እንደ ተራራ ገዝፎ ቀጥሏል። የአንድ ወቅት የጠቅላዩ አፈ-ንጉሥ፣ ንጉሡ ጥላሁን በደንቢዶሎ ከታገቱት ተማሪዎች የተወሰኑትን ማስለቃቀቸውን ጠቅሶ፣ ቀሪዎቹም በአጭር ጊዜ ነፃ እንደሚወጡ መናገሩን፤ ዛሬ፣ የእገታው መፈጸም ከእነ- አካቴው ከመካዱ ጋር ስንደምረው፣ አልተግባብቶው ከባቢሎናውያንም የከረረ መሆኑን እንረዳለን። አያሌ ግድያዎች ተፈጽመው፣ በመቶ ሺዎች ተፈናቅለው፤ “የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት” በሚባል ብሽቅ መድረክ እንዲሳለቁብንም፣ ፈቅደን ከተንጋለልን ሰንብተናል።

Continue Reading

Be the first to comment

Leave a Reply

Your email address will not be published.


*