
ይህንን ጽሑፍ ለማዘጋጀት የተነሳሳሁት በሁለት ምክንያቶች ነው።
አንደኛ፣ በሐምሌ ወር መጨረሻ ላይ “ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያን እንዳትሆን ያሠጋል፤ (እንደውም) ትሆናለች” የሚለው አመለካከት ለስንተኛ ጊዜ እንደገና ነፍስ ዘርቶ ሲደጋገም ሰነበተ። ሌሎች “ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያ አይደለችም” እያሉ አመለካከቱን ሲያፋልሱ ከረሙ። ኢትዮጵያ እና ዩጎዝላቪያ ምን እና ምን ናቸው? የሚለውን ጥያቄ ጫረብኝ። ስለዚህም፣ የዩጎዝላቪያ መንግሥት አመሠራረት፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት አመሠራረት እና ታሪክ ጋር ያለውን ልዩነት ለማስታወስ ያህል ብቻ፣ ስለ ዩጎዝላቪያ መንግሥት አመሠራረት ክንዋኔ ባጭሩ ለመከለስ አሰብኩ።
ሁለተኛ፣ በቤልጂየም የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አምባሳደር ሂሩት ዘመነ፣ ዝቅ ሲል በማነሳው ጽሑፋቸው ለአንድ ባሮኔስ አርሚንካ ሄሊች ለተባሉት ሴትዮ ሲመልሱ “የተሳሳት አመለካከት በፅንሰ–ሃስብ ረግድም ሆን ተብሎ እየተለጠጠ ይሠራጫል” ብለው ያሉት ቁም ነገር፤ የኢትዮጵያ የፖለቲካ (የሥልጣን) ልሂቃንስ! በፖለቲካ ሳይንስ የፅንሰ–ሃሳብ ልጠጣ (concept stretchingወይንም straining) እየተባለ በሚገለፀው ምልከታ እየተጧጧዙ በሥርዐት ለመወያየት እንኳን የተቸገሩ ፍጡራን አይደሉም ወይ? የሚለውን ጥያቄ ጫረብኝ። በጥቂቱ ልመለስበት አሰብኩ።
“ኢትዮጵያ ዩጎዝላቪያን እንዳትሆን ያሠጋል፤ (እንደውም) ትሆናለች” የሚለው አመለካከት፣ በኢሕአዴግ አገዛዝ ላይ ጠጠር ያለ ተቃውሞ በተነሳ ቁጥር አንዳንድ የድርጅቱ አመራሮቹ ሲደጋግሙት የነበረ አመለካከት ነው። መለስ ዜናዊ በ2004 ዓ.ም ሲያርፉም፣ “ተተንብዮ” ነበር። ኢሕአዴግ በ2010 ዓ.ም ከሥልጣን ሲወርድም፣ ሰሞነኛ ሆኖ ነበር። ፍሎራልን ብሬበር እና ወንድምአገኝ ታደሰ ገብሩ የተባሉ ግለሰቦችም፣ የውጭ ፖሊሲ (Foreign Policy) በሚባለው የአሜሪካ መጽሔት ላይ በጥር 7/2011 (January 15/2019) “ኢትዮጵያ የሚቀጥለው ዩጎዝላቪያ እንዳትሆን ተከላከሉ” እያሉ አንድ የማስጠንቀቂያ ጥሪ አዘል ጽሑፍ አሳትመው ነበር። (https://foreignpolicy.com/2019/01/15/dont-let-ethiopia-become-the-next-yugoslavia-abiy-ahmed-balkans-milosevic-ethnic-conflict-federalism/)
Be the first to comment